አብዱላሂ ዩሱፍ
አብዱላሂ ዩሱፍ፣ በመጋቢት 26 ቀን 1934 ዓ.ም. በሐረርጌ ክፍለ hገር ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በድሬደዋ ከተማ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በሐረር ከተማ መድኅኔ ዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማር ከጀመረ በኋላ ትምህርቱን አቋርጦ፣ በኤርትራ በኩል ወደ ሱዳን በመሻገር የስደት ሕይወትን ተያያዘው። በ1959 ዓ.ም. በስደተኝነት ስዊድን ገባ።
በ1960 ዓ.ም. በሉንድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ቀጥሎ በ1964 ዓ.ም. በፖለቲካል ሳይንስ እና በኢኮኖሚክስ የባችለር ኦፍ አርትስ ዲግሪውን በማግኘት ተመረቀ። በስዊዲን ቆይታውም በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ነበረው። በነሐሴ 1960 ዓ.ም. የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ከተመሠረተ በኋላ፣ አብዱላሂ በአባልነት ድርጀቱን ተቀላቀለ።
ከስዊድን ሉንድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ መኖሪያውን ወደ ምዕራብ ጀርመን አዛውሮ በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት አፋን ኦሮሞ አስተማረ። ቆይቶም ወደ አገሩ ተመልሶ መኢሶን በመደበው ሥራ ሁሉ ማገልገል ጀመረ።
በ1968 ዓ.ም. የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲመሠረት የድርጅቱ የሐረርጌ ክፍለ አገር ኃላፊ በመሆን ማገልገል ጀመረ። በ1969 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የሶማሌ ጦር እና ሰርጎ ገቦች ወደ ሐረርጌ እና ባሌ ክፍለ ሀገሮች ደጋማ አካባቢዎች እየገቡ መሆናቸውን አስታውቆ፣ አርሶ አደሩ በጊዜ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ በማሳሰቡ በክፍለ አገሩ የደርግ አባልና የመንግሥት ተወካዮች ጥርስ ውስጥ ገባ። በዚህም ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት አንዲሠራ ተደርገ። ይህም ሆኖ እንኳን ሕይወቱን ከሞት አደጋ ማትረፍ አልተቻለም።
አብዱላሂ፣ ሐምሌ 1969 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከሚያስተምርበት ከየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ወጥቶ መኪናውን እያሽከረከረ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ሲደርስ፣ የደርግ ነፍሰ ገዳዮች በመኪና ተከታትለው በጥይት እሩምታ ገደሉት። ከገደሉትም በኋላ በግልጽ እየታዩ የደርግ ጽ/ቤት ወደ ነበረበት ታላቁ ቤተ መንግሥት መኪናቸውን እያሽከረከሩ ገቡ።
የአብዱላሂ ዩሱፍ በዚህ አኳኋን መገደል፣ መኢሶን ከአራት ወራት ቀደም ሲል በመጋቢት 1969 ዓ.ም. የወሰነውን የኅቡዕ መግባት ውስኔ በጥድፊያ ሥራ ላይ እንዲያውል አንዱ ምክንያት ሆነ።