መስፍን ካሱ
መስፍን ካሱ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ አታለለች ዘሪሁን እና ከአባቱ ከአቶ ካሱ ሃብተ ገብረኤል ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ይጠራ በነበረው ክፍለ አገር፣ በጀመጀም አውራጃ፣ ይርባ ሙዳ በተባለች ከተማ ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በተወለደባት ይርባ ሙዳና አገረ ሰላም ከተማ አጠናቀቀ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአመርቂ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ታዋቂ በነበረው በጄነራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤት ቆይታውም ቺንዲት በመባል ትታወቅ በነበረችው የተማሪዎች መጽሔት የተለያዩ መጣጥፎችን በማበርከት እና እንዲሁም ሄድ ቦይ በመባል የተማሪዎች አለቃ ሆኖ በማገልገሉ ብዙዎች ያስታውሱታል።
በ1957 ዓ.ም. የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ። መስፍን የመረጠውም የትምህርት ዘርፍ ኢኮኖሚክስ ነበር። በ1961 ዓ.ም. በባችለር ኦፍ አርትስ ዲግሪ ተመረቀ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው መስፍን ካሱ በተማሪው እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሳታፊና መሪ በመሆን ይታወቃል። በተለያዩ ግቢዎች ያሉትን ተማሪዎች በመላ ያስተባብር የነበረውን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብሔራዊ ማህበርን (NUEUS) በሊቀ መንበርነት መርቷል።
በተማሪነቱ በሚያደርገው ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎም በዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለተደጋጋሚ እስራት ተዳርጎ ነበር። በዚያን ወቅት ነበር የተማሪዎች ማህበር “መሬት ላራሹ” የመሳሰሉትን መሰረታዊ ለውጥን ይጠይቁ የነበሩ መፈክሮችን በአደባባይ አንግቦ መታገል የጀመረው።
በ1960 ዓ.ም. መስፍን ካሱ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብሔራዊ ማህበር ለቀመንበር ሆኖ በሚያገለግልበት ወቅት ሊየዥ ከተማ (ቤልጅግ) በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር መመሥረቻ ጉባኤ ላይ ተካፍሏል። በነሐሴ 1960 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን ሀምቡርግ ከተማ የተመሠረተው የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መሥራችና የጠቅላይ ኮሚቴው አባል ነበር።
በ1961 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ሥራ የጀመረው ሲታገልለት ለነበረው ከ”መሬት ላራሹ” መፈክር ጋር ቀጥታ ተያያዥነት በነበረው የመሬት ይዞታ እና አስተዳደር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ነበር። በዚህም ተቋም ውስጥ ጥቂት ካገለገለ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊስኮንሲን – ማዲሰን የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ተከታትሎ በ1967 ዓ.ም. የማስትሬት ዲግሪውን አግኝቶ ወደ አገሩ በመመለስ ቀድሞ ይሠራበት በነበረበት በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በማገልገል የመሬት ዓዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን የድርሻውን አበርክቷል። በ1968 ዓ.ም. የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲመሠረት ከመሬት ይዞታና የሕዝብ ማስፈር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በመዛወር የጽህፈት ቤቱ ዋና ጸሃፊ በመሆን አገልግሏል።
በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ጊዜያዊ ትብብር አቋርጦ ኅቡዕ ሲገባ ወደ ሲዳሞ ክፍለ አገር በመሄድ በአካባቢው የነበረውን የድርጅቱን እንቅስቃሴ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በመሆን ሲመራ ቆይቶ በሚያዚያ ወር 1970 ዓ.ም. በደርግ ወታደሮች ተይዞ ታሰረ። የድርጅቱም አመራር አባል ስለነበር የደርግ መርማሪዎች ስለድርጅቱ የሚያውቀውን ምስጢር እንዲያወጣ ዘግናኝ የአካል ስቃይ አደረሱበት። መስፍን ካሱ ይህ ሁሉ አካላዊ ስቃይ ቢደርስበትም መርማሪዎቹን ጭምር ባስገረመ ጽናቱ ምንም ምስጢር ሳያወጣ የሞትን ጽዋ ተጎነጨ።
መስፍን ካሱ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር።