ጀማል አባስ
ጀማል አባስ ከእናቱ ከወ/ሮ ዘሀራ አብዱላሂ እና ከአባቱ ከሼክ አባስ ቶሻ በ1946 ዓ.ም. ምሥራቅ ሐረርጌ ግራዋ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ግራዋ ካጠናቀቀ በኋላ እስከ 10ኛ ክፍል ሐረር መድኀኔ ዓለም ትምህርት ቤት ተምሮ በመጨረሻም ከደብረ ብርሃን መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመረቀ። ከዚያም ድሬዳዋ ጀዲዳ በሚባል ትምህርት ቤት በመምህርነት ማገልገል ጀመረ።
ጀማል መኢሶንን ገና በለጋ እድሜያቸው ከተቀላቀሉት ወጣቶች መሃል አንዱ ነው። መኢሶንን ከተቀላቀለ በኋላ በሐረርጌ ክፍለ አገር ወጣቶችንና ገበሪዎችን በማንቃትና በማደራጀት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ያደረገ ታጋይ ነበር።
ነሐሴ 1969 መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ፣ ጀማልም ከሐረርጌ አዲስ አበባ መጥቶ ስውር ድርጅታዊ ተግባሮችን እንዲያከናውን ተመደበ። ይህንንም የተሰጠውን ኃላፊነት እያከናወነ ሳለ ከሌላ የመኢሶን ጓድ፣ ከዮሐንስ መስፍን ጋር በአንድነት በደርግ የጸጥታ ሰዎች ተያዘ። በደርግ ግቢ እስር ቤት ብዙ እንግልት ከደረሰበት በኋላ አራተኛ ክፍለ ጦር ወደአለው እስር ቤት ተዛወረ። እዚያም ለጥቂት ሳምንታት ከቆየ በኋላ፣ አስከፊ አካላዊ ስቃይ ከተፈጸመበት በኋላ ያለ ምንም ፍርድ በደርግ ተገደለ።
ጀማል አባስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የ24 ዓመት ወጣት ነበር።