ንግሥት አዳነ (ዶ/ር)

ዶክተር ንግሥት አዳነ ነሐሴ 1937 ዓ.ም. ሓረቆ፣ ትግራይ ተወለደች። አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን መቀሌ አፄ ዮሐንስ ት/ቤትና ሲዳሞ፣ ይርጋዓለም ራስ ደስታ ዳምጠው ት/ቤት ተከታተለች። ሁለተኛ ደረጃ ተምህርቷን ደግሞ በአዲስ አበባ እቴጌ መነን ት/ቤት አጠናቀቀች። ንግሥት ከክፍሏ ሁልጊዜ አንደኛ ትወጣ የነበረች ጎበዝ ተማሪ ነበረች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ በዚያን ጊዜ ሶቪየት ህብረት ተብላ በምትታወቀው ሩሲያ በሕክምና ሙያ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቃለች። 

ሩሲያ በነበረችበት ጊዜያት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ነበራት። ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ  ስፔሻላይዝ በአደረገችበት የሕጻናት ሕክምና ሙያዋ አገልግላለች።

ንግሥት ከ1968 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የሕዝብ ድርጀት ጊዜያዊ ጽ/ቤት አባል፣ እንዲሁም የካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት መምህር ሆናም ሠርታለች። የመኢሶን ጠቅላይ ኮሚቴ አባልና የመኢሶን የሴቶች ክንፍ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢሴአን) መሥራችና መሪም ነበረች።

በ1968 ዓ.ም. ዶክተር ንግሥት ሴቶችና የሕብረተሰብ እድገት’ በሚል ርዕስ በተለያዩ የህብረተሰብ ሥርዓቶች ውስጥ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና የሚተነትን ጥናታዊ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች።

መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ በኅቡዕ መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ በኅቡዕ በተሠማራችበት በሃዲያ አውራጃ በደርግ ወታደሮች ተይዛ ታሰረች። ከዚያም ሐምሌ 5 ቀን 1971 ዓ.ም. ደርግ ንግሥትን ከታሰረችበት እስር ቤት አውጥቶ ከኃይሌ ፊዳ፣ ሃይሉ ገርባባ፣ ቆንጂት ከበደና ከባለቤቷ ከደስታ ታደሰ ጋር ያለ ምንም ፍርድ በድብቅ ገደላት።

ንግሥት ከሰው ጋር ተግባቢና ለሰዎች ደህንነት የምትጨነቅ ነበረች። እንዲሁም እጀግ የተወሳሰበ ሁኔታን ቀለል ባለ መልክ አስረድታ ሰውን ማሳመን የምትችልና በአካባቢዋ ያሉትን ሁሉ የምታስተባብርና የምትመራ ጓድ ነበረች።

የደርግ መንገስት በወደቀ በሁለተኛ አመት፣ የዶ/ር ንግሥት አጽም በሚስጥር ተገድላ ከተቀበረችበት ከራስ አስራተ ካሳ ግቢ ወጥቶ በቤተሰቧ መካነ መቃብር በክብር አርፏል።

ዶክተር ንግሥት አዳነ አብሯት በደርግ የተገደለው የደስታ ታደሰ ባለቤትና የሰባት ዓመት ልጅ እናት ነበረች።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top