አበራ ብርሃኑ ተሰማ
አበራ ብርሃኑ፣ መስከረም 1 ቀን 1928 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ብርሃኑ ተሰማ ጓንጉልና ከእናቱ ከወ/ሮ አቦነሽ ጉታ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ በሚባለው ሰፈር ተወለደ። እስከ 10ኛ ክፍል ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ከተማረ በኋላ ጅማ እርሻ ት/ቤት ትምሕርቱን መከታተል ጀመረ። ጅማ እርሻ ት/ቤት በነበረበት ጊዜ በጀመረው በእርሻ ምህንድስና ትምህርት አለማያ እርሻ ኮሌጅ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን ለማግኘት ችሏል። ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ቀድሞዋ ሶቭዬት ህብረት በመሄድ በእርሻ፣ ጥጥ ተክልና ጨርቃ ጨርቅ መሣሪያዎች ምህንድስናና ምርት አገልግሎት ከፍተኛ ስልጠና በማግኘት ወደ አገሩ ተመልሷል።
ኢትዮጵያም እንደተመለሰ በጅማ እርሻ ት/ቤት በመምህርነት፣ ቀጥሎም በ1960 እና 1961 ዓ.ም. የባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል።
በዚያው ዘመን በጎጃም ክፍለ አገር ተቀስቅሶ የነበረውን የገበሬዎች አመፅ በመደገፍ ተነሳስተው የነበሩትን የፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ከደገፉና ካስተባብሩት አንዱ ስለነበር እስከ መታሰር፣ ከክፍለ አገሩም እስከመባረረና በወቅቱ በመንግሥት መሥሪያ ቤትም እንዳይቀጠሩ እስከመታገድ ከደረሱት መሀል አንዱ ነበር።
ለተወሰኑ ዓመታት በመንግሥትም ሆነ የግል ድርጆቶች ውስጥ የመቀጠር ዕድል ተነፍጎት ከቆየ በኋላ ጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት ተቀጥሮ ከድሃ አርሶ አደር ገበሬዎች ጋር በቀጥታ በሚያገናኘው ሙያው አገሪቱንና ህዝቦቿን አገልግሏል። የኢትዮጵያ አብዮት በየካቲት ወር 1966 ከፈነዳ በኋላ ደግሞ ወደ ንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር በመዛወር የእርሻ መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ኮርፖሬሺን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርቷል።
በነሐሴ ወር 1969 ዓም መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ የመኢሶንን ኅቡዕ አባሎች በመደገፍ የሚያደርገው እንቅስቀሴ ተደርሶበት በደርግ መንግሥት ታሠረ። ከአምስት ዓመት እሥር በኋላ ቢፈታም በእሥር ላይ በምርመራ ላይ በነበረበት ወቅት አስከፊ በሆነ መንገድ ስለተደበደበ በጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት። ከእሥር እንደተፈታ በቂ ሕክምና እንዲያገኝ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ትብብር ወደ ስዊድን አገር ተወሰደ። ይሁንና፣ ከጽኑ ሕመሙ ሊድን አልቻለም። በዚህ አኳኋን ከ45 ዓመት የአልጋ ቁራኝነት በኋላ ጥቅምት 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አበራ ብርሃኑ፣ የሚታወቀው ላመነበት ዓላማ በፅናት በመቆም፣ በቆራጥነቱ፣ በሃቀኛነቱ፣ ቀጥተኛነቱና ገደብ የሌለው ርህራሄው ነበር። ከዚህ ሌላ አበራ በተማሪነት ዘመኑ በእጅ ኳስ፣ በዋና፣ እና በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ችሎታው የታወቀ ነበር።