ሽመልስ ኦላና
ሽመልስ ኦላና፣ ከእናቱ ከወ/ሮ የሺእመቤት በላይ ዘለለውና ከአባቱ አቶ ኦላና ባቲ ሁንዴ 1950 ዓ.ም. በቀድሞው የወለጋ ጠቅላይ ግዛት በነቀምት ከተማ ተፈሪ መኰንን ሆስፒታል ተወለደ። እድሜው ለትምህርት እንደ ደረሰ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ድረስ በአዲስ አበባ መካነ ኢየሱስ፣ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ደግሞ ነቀምቴ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአቃቂ ሚሲዩን ት/ቤትና በነቀምቴ ኮምፕሪሄንሲቭ ትምህርት ቤት አጠናቋል። የ12ኛ መልቀቂያ ፈተናን በከፍተኛና የላቀ ውጤት በማጠናቀቅ የእጅ ሰዓት ተሸልሟል።
በ1967 ዓ.ም. በእድገት በህብረት ዘመቻ በመሳተፍ በጉቴ ወረዳ ጣቢያ ዘመቻውን አጠናቋል። ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በትምህርቱ ከፈተኛ ውጤት በማስመዝገብ በማዕረግ እንዳጠናቀቀ በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ይታወሳል። ሽመልስ፣ ከቀለም ትምህርት ጉብዝናው በላይ በመልካም ባህሪው እጅግ በጣም ተወዳጅ ነበረ።
ከእድገት በህብረት ዘመቻ ጣቢያ መልስም፣ የመኢሶንን የፖለቲካ መስመር በመከተል ብዙ ጥናት ክበቦችን በሟቋቋም የመኢሶን ድርጅት በወለጋ ክፍለ አገር ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዲያገኝ ካደረጉ ጓዶች ግንባር ቀደሙ ነበር። በዚህም ጥረቱ፣ ታዋቂ ሰዎችንም የድርጅቱ ደጋፊ አድርጓል። በኢሕአፓ የግድያ ቡድን በተደጋጋሚ በጥይትና በእጅ ቦምብም ጭምር ሕይወቱ ላይ የጥቃት ሙከራዎች ቢደረጉበትም፣ በሕይወት ተርፎ በጅማ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ባልደረባ ሆኖ በ1969 ዓ.ም. ሠርቷል።
በወጣትነት እድሜው ለግል ምቾቱና ሕይወቱ ሳያስብ፣ ለሰፊው ህዝብ መብትና ጥቅም ሲል ከድርጅቱ በተሰጠው ትዕዛዝ ነሐሴ አጋማሽ ላይ በ1969 ዓ.ም. መኢሶን ኅቡዕ ሲገባ፣ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በጅባትና ሜጫ አውራጃ አምቦ አካባቢ፣ ቶኬ በምትባል ስፍራ ለገጠር ትግል ተሰማርቶ ሳለ በሁለት የውስጥ ከሐዲዎች ሴራና ጥቆማ፣ ከሌሎች ዘጠኝ ጓዶች ጋር ከደርግ ጽ/ቤት በተላከ ልዩ ኃይል ታኅሣሥ 30፣ 1970 ዓ.ም. ተይዞ ተገደለ።
ሬሳውም ወዴት እንደወደቀ አልታወቀም። የቅርብ ቤተሰቦቹም፣ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በ1983 ዓ.ም. ባደረጉት ክትትል፣ ሽመልስ ተገድሎ ሬሳው ሳይቀበር፣ ውጭ ተጥሎ ለጅብ ቀለብ እንደተደረግ ተረድተዋል። ይህም መረጃ፣ በጊዜው በልዩ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ በቀረቡ ምስክሮች ተረጋግጧል።
በመኢሶን ተሳትፎ የነበራቸው የሽመልስ ወንድሞች፣ ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች በተለያዩ ጊዚያት በደርግ እስር ቤት ማቀዋል።