ተስፋዬ ታደሰ
ተስፋየ ታደሰ፣ ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በመጀመሪያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲት ነበር። ሆኖም፡ በጊዜው በመፋፋም ላይ በነበረው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ በነበረው የጎላ ተሳትፎ የተነሳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እይታ ስር በመግባቱ ድንበር ጥሶ ወደ ሱዳን ገባ። ከዚያም በመሻገር ሌባኖን ቤይሩት ከተማ በሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ቀጠለ። በቤይሩት ዩኒቨርሲቲ ቆይታው ወቅትም በመካከለኛው ምሥራቅ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ ነበር። ተስፋዬ ላመነበት የፖለቲካ ዓላማ ጽኑ ተሟጋች ነበር። በተለይም፣ የፖለቲካ ድጋፉን በግልጽ ለመኢሶን ካደረገበት ጊዜ አንስቶ የተቃዋሚዎችን ስም በግልም ሆነ በጥቅል በማጠልሸትና በአሉባልታ የተካነው ኢሕአፓ፣ ተስፋየ ታደሰ ላይ ዘምቶበት ነበር።
በየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ከመካከለኛው ምሥራቅ በስደት ይገኙ እንደነበሩት እንደሌሎች ተማሪዎች ሁሉ ተስፋዬም ወደ አገሩ ተመለሰ። አዲስ አበባም እንደተመለሰ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራ ጀመረ።
መኢሶን፣ ነሐሴ አጋማሽ 1969 ዓ.ም. ኅቡዕ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ በመላው የድርጅቱ አባሎች ላይ ደርግ ባካሄደው የግድያ ዘመቻ፣ ታኅሣሥ 24፣ 1970 ዓ.ም. ተስፋየ ታደሰ መኪናውን እያሽከረከረ ከአምስት ኪሎ ቁልቁል ሲጓዝ ደርግ ያሰማራው ስውር ገዳይ ቡድን አባሎች በመኪና ተከታትለው የጥይት እሩምታ አርከፈከፉበት። ሆኖም፡ በዚያች ዕለት ከእርሱ ጋር በመኪናው ተሳፍሮ የነበረው ግዛው ጂማ በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ሲያልፍ ተስፋዬ ለጊዜው በሕይወት ተረፈ። ተስፋዬ ታደሰ፣ በዚያች ዕለት በሕይወት ቢተርፍም ቅሉ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለምርመራ በሚል ደርግ ጽ/ቤት ተወስዶ ሳይመለስ ቀረ። ደርግ፣ ተስፋየ ታደሰን ያለፍርድ በድብቅ ገደለው።