ታደሰ ጠጊቾ
ታደሰ ጠግቾ በ1945 ዓ.ም. በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ አገር፣ በሲዳማ አውራጃ፣ በአርቤጎና ወረዳ ልዩ ስሙ ማኑሱሮ ዲከ በሚባል ቦታ ተወለደ ። እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ በ1952 ዓ.ም በአገር ሰላም ሚስዮን ትምህርት ቤት ገበቶ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ወደ አገረ ሰላም ወረዳ ደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት በመግባት በ1960 ዓ.ም. የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። በመቀጠልም ለሁለት አመታት በ1961 እና 1962 ዓ.ም. ይርጋዓለም በሚገኘው ራስ ደስታ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማረ በኋላ፣ በ1963 እና 1964 ዓ.ም. ሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም በመምህርነት ሙያ ሰልጥኖ ተመረቀ።
ታደሰ ጠጊቾ፣ በ1965 ዓ.ም. በወለጋ ክፍለ አገር፣ በጊምቢ አውራጃ በመምህርነት ለአንድ ዓመት ካገለገለ በኋላ በ1966 ዓ.ም. ወደ ትውልድ ወረዳው አርቤጎና ተዛውሮ በአርቤጎና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግሏል። ከዚያም በ1967 ዓ.ም. ይርጋዓለም አጠገብ ወደ ሸበዲኖ ወረዳ ተዛውሮ በምድረ ገነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አገልግሏል።
ታደሰ፣ ለሕዝብ ካለው ፍቅር የተነሳ በ1968 ዓ.ም. በወቅቱ ሕዝብን ለማንቃትና ለማደራጀት የተቋቋመውን የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤትን ተቀላቀለ። በሲዳማ አውራጃ የዳሌ ወረዳ ጽ/ቤቱ ሀላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ እያለ ጥር 27 ቀን 1969 ዓ.ም. በ24 ዓመት ለጋ ዕድሜው በይርጋዓለም ከተማ በኢሕአፓ ታጣቂ ነፍሰ ገዳይ ቡድን ተገደለ።