ቴዎድሮስ በቀለ
ቴዎድሮስ በቀለ ከእናቱ ከወ/ሮ ይታክቱ ደስታ እና ከአባቱ ከመቶ አለቃ በቀለ በላቸው በ1939 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተስፋ ኮከብ፣ ሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን ኮከበ ጽባህ ት/ቤት ተከታትሏል። ከዚያም በ1952 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ተቀጥሮ መጀመሪያ ከተመረቁት መርከበኞች አንዱ ሊሆን ችሏል። በባሕር ኃይል ውስጥ በመሃንዲስነት ከመስራቱም ሌላ በተመደበበት ኢትዮጵያ የጦር መርከብ ለአንድ አመት ያህል በአፍሪቃ፣ እስያና አውሮፓ በመጓዝ ከፍተኛ አገልግሎት አበርክቷል። ከባሕር ኃይል ግልጋሎቱ በተጨማሪ በወንጂ ስኳር ፋብሪካና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሠርቷል።
ቴዎድሮስ እውቀቱን ይበልጥ ለማስፋት በነበረው ጽኑ ፍላጎት ምክንያት ወደ አውሮፓ ሄዶ ተጨማሪ የመርከበኛ ትምህርት ተከታትሏል። አውሮፓ በነበረ ጊዜም በሲቪል መርከብ ድርጅቶች ውስጥ ሠርቷል።
ቴዎድሮስ ለሰው ፍቅር ያለው፣ የተቸገሩ ወገኖቹን መርዳት የሚወድ ጥሩ ሰው ነበር። ከአውሮፓ እንደተመለሰ መጀመሪያ ከሰራቸው ስራዎች መሃል አንዱ የሲማኖች (መርከበኞች) መረዳጃ ማህበር ማቋቋም ነበር። ይህ ማህበር በተለያየ ምክንያት ከባሕር ኃይል የወጡ መርከበኞች ሥራ አጥ እንዳይሆኑና እንዳይቸገሩ በተለያዩ ድርጅቶች እንዲቀጠሩ የሚረዳ ነበር።
የመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር በ1969 ዓ.ም. ታኅሣሥ ሲቋቋም ከትራንስፖርት ኢንዱስትሪ የመጣው ቴዎድሮስ በቀለ በከፍተኛ ድምጽ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። እንደተመረጠም በትጋት ሥራውን ማከናወን ጀመረ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የካቲት 18 ቀን 1969 ዓ.ም. ከኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ አለፈች።
ቴዎድሮስ በቀለ ከትዳር አጋሩ አንድ ወንድ ልጅ አፍርቷል።