አምበርብር በላይ
አምበርብር በላይ ከእናቱ ከወ/ሮ ናፈቁ በለውና ከአባቱ ከአቶ በላይ ወንዴ ነሐሴ 24፣ 1933 ዓም በጎንደር ከተማ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ጎንደር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ኮተቤ) ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ በዲግሪ ተመርቋል። በተጨማሪ ስዊድን ሀገር በመሄድ ከፍተኛ የቴክኒክ ኮርሶችን አጠናቋል።
አምበርበር ከፍተኛ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ቴለኮሙኒኬሺን መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። በተለይም ከእጅ ማዞሪያ ወደ ማይክሮዌቭ የቀየረውን የቴሌኮሙኒኬሺንን ፕሮጀክት ከመሩት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነበር።
አምበርብር በግሉም ሆነ በመኢሶን አባልነቱ፤ ለሕዝብና ለሀገሩ ባለው ፍቅር ሰዎችን መርዳት፣ ማስተማርና የማሳደግ ፍላጎት ነበረው። ስለሆነም በአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች የቀበሌ ማኅበራት ሲቋቋሙ፤ ሕዝብን ለማደራጀት በነበረው የፖለቲካዊ ተሳትፎ በከፍተኛ 21 የቀበሌ 4 ሊቀ መንበር ሆኖ ተመረጠ።
ሆኖም ግን ለቀበሌው ነዋሪ ከዚያም አልፎ ለሀገሩ መልካም ለውጥ ለማምጣት በትጋት መሥራቱን የሚቃወሙ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች ሰኔ 14 ቀን ወደ ቢሮው ሲጓዝ አዲስ አበባ መንገድ ላይ ጠብቀው ገደሉት። አምበርብር በ36 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለየን ባለትዳርና የሁለት ሕጻናት አባት ነበር::