አስፋው ሽፈራው

አስፋው ሽፈራው በ1942 ዓ.ም. ከእናቱ ከወ/ሮ አበበች ታምሩና ከአባቱ   ከባላምባራስ ሽፈራው ሙላቱ በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ቃዊሳ በተባለች መንደር ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደባት በቃዊሳ ተከታተለ። የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አርጆ በሚገኘው በቢትወደድ መኮንን ደምሰው ትምህርት ቤት ነበር። በመቀጠልም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ነቀምቴ በሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ   ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አዲስ አበባ በሚገኘው የኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርቱን ቀጥሎ በዲፕሎማ ተመረቀ። ከተመረቀም በኋላ በጂጅጋ ከተማ ለአንድ ዓመት በመምህርነት አገለገለ። በመቀጠልም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ አስተዳደር ዘርፍ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።

የየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ግቡን እንዲመታ፣ አስፋው በመኢሶን አባልነቱ በፖለቲካ የማንቃትና የማደራጀት የግል ድርሻውን ያለማመንታት ይወጣ ነበር። ከአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ለመመረቅ አንድ ሴሜስተር ቢቀረውም፣ ትምህርቱን አቋርጦ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በአምቦ ከተማ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኖ ማገለገል ጀመረ።

በነሐሴ 1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ በአውራጃው ውስጥ ኅቡዕ ገብተው የነበሩ የመኢሶን ጓዶች በደርግ መንግሥት ወታደሮች ተይዘው ሲረሸኑ፣ አስፋው ከመሥሪያ ቤቱ ተይዞ ታሠረ።

በየካቲት 1970 ዓ.ም. አስፋው ሽፈራው፣ በእስር ላይ ከነበረበት ከ4ኛ ክፍለ ጦር እስር ቤት ከሌሎች ሁለት የመኢሶን ጓዶች፣ ከዮሐንስ መስፍን እና ከጀማል አባስ ጋር ተወስዶ ያለምንም ፍርድ ተገደለ።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top