ደንበል አየለ
ደንበል አየለ፣ ሶዶ፣ አማውቴ በተባለ ቀበሌ በ1947 ዓ.ም. ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታተለ። ደንበል፣ የአጎቱ ልጅ እና መምህሩ በሆነው በተስፋዬ ገላን (ጄንጂስ) አማካይነት የመኢሶንን ጽሑፎች ማንበብና የፖለቲካ ጥናትም መከታተል ጀመረ። የመኢሶን አባልም ሆነ።
በሰፈሩ የነበሩ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች “ተስፋዬ ገላንና ደንበል አየለ ይሰቀሉ” የሚሉ መፈክሮች አዘውትረው ያወርዱና በየቤታቸው በራፎች ላይ በቀይ ቀለም ይጽፉ ነበር። የተስፋዬ ባለቤትም በየቀኑ እነዚያን የስድብና የውግዘት ጽሑፎች ስታጥብ ትውል እንደነበር ትናገራለች።
የጄንጂስ ባለቤት፣ ደንበል አየለን ለመጨረሻ ጊዜ ስታየው የነበራትን ትውስታ እንደሚከተለው ትገልጸዋለች፣ “በነሐሴ 13 ቀን የቡሄ ዕለት ‘እባክሽ የቡሄ ዳቦ ስጭኝ’ ብሎ ሰጥቸው፣ ያንን ይዞ በሚሾፍረው መኪና ወጥቶ ሄደ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጫንጮ ላይ ተገደለ ሲባል ሰማሁ”። ነሐሴ 13 ቀን ደንበል ከድርጅቱ በተመደበለት መኪና የመኢሶን አመራር አባሎችን ይዞ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቁ ከተማ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ በቅርብ ርቀት ለማስተባበር እንዲችሉ አስተማማኝ ነው ተብሎ በተገመተው ሙሎ ወረዳ ውስጥ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ይዟቸው ሄደ።
እዚያ እንዳሉ የደርግ መንግሥት ወታደሮች መረጃ ደርሷቸው ከበባ በማድረግ እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ የአመራር አባላት የሆኑት ዶ/ር ከበደ መንገሻና ዳንኤል ታደሰ፣ አብረዋቸው የነበሩትን ደንበል አየለ፣ ምትኩ ተርፋሳና ደንቢ ዲሳሳን ወታደሮቹ እናንተን ምንም ላያደርጓችሁ ይችላሉና እጃችሁን ስጡ ብለዋቸው እነሱ በታጠቁት መሣሪያ ራሳቸውን ሠው። የሃያ ሦስት አመቱ ደንበልና ሁለት ጓዶቹ ግን፣ እጃቸውን ከመስጠት ይልቅ እየተታኮሱ በጀግንነት ወደቁ።