ገሠሠ በላይ

ገሠሠ በላይ፣ በትግራይ ክፍለ አገር አድዋ ከተማ ኅዳር 28፣ 1948 ዓ.ም. ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እስከ ስምንተኛ ክፍል አድዋ ውስጥ ንግሥት ሳባ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። በትምህርቱ እጅግ ጎበዝ በመሆኑ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም አዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተቀብለውት ተማረ። በጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት ከአሥራ ሁለተኛ ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ በ1965 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋከልቲ ገባ። ከሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ የወርቅ ሰዓት ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

ገሠሠ በላይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ የሳይንስ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበር። የመኢሶን አባል፣ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ንቅናቄ (ኢአወን) አመራር አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመኢሶን ወጣቶች ህዋሳት አስተባባሪም ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ተማሪ ሳለም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። ገሠሠ በላይ በ1965 – 1966 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጠቅላላው 1,500 የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ካገኙት ሦስት ተማሪዎች መሃል አንዱ ነበር።

የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች፣ የካቲት 11፣ 1969 ዓ.ም በውድቅት ሌሊት ገሠሠ ይኖርበት የነበረውን አዲስ አበባ ኦርማ ጋራዥ አጠገብ የሚገኘውን የወንድሙን የመስፍን በዛብህን ቤት ሰብረው ገብተው በጥይት እሩምታ ገሠሠን ገደሉት። ከገሠሠም ጋር የሺመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት አሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ የነበረው፣ ጌታሁን ታመነም የኢሕአፓ የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆነ።  በተጨማሪም ሁለት የቤት ሠራተኞች በተኙበት ተገደሉ። ታላቅ ወንድሙ መስፍን በዛብህና ሕጻን ልጁ ደግሞ በጥይት ቆስለው በሕይወት ተረፉ።

ገሠሠ በላይ አእምሮው ብሩኅ የሆነ ለጋ የሃያ አንድ ዓመት ወጣት ነበር። በፖለቲካ የሐሣብ ልዩነቶች ላይ ተከራክሮ የማይደክመውና በግልም ውይይት ይሁን በስብስባ ላይ፣ በሐሣብ ለማሳመን ወይም ለማመን ሁልጊዜም ዝግጁ የነበረ ጽኑ ታጋይ ነበር። 

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top