ፀጋዬ የኋላው

ፀጋዬ የኋላው፣ የኢትዯጵያ ሲቪል አቪየሽን መሥሪያ ቤት ባልደረባ ነበር።  በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ሠራተኞችን በማደራጀትና በመምራት በነበረው ቀልጣፋና ጉልህ ተሳትፎ፣ የሲቪል አቪየሽን ሠራተኞች ማኅበር ሊቀ መንበር ሆኖ ተመርጧል። በዚህም ኃላፊነቱ፣ የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በማይታጠፍ ጽናት ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሊቀ መንበርነቱም በወዛደሮች የሙያ ማኅበራት መሀል የቅርብ ትብብርና ትስስር እንዲፈጠርና እንዲዳብር ከሚታገሉት   አንጋፋ የሠራተኞች መሪዎች አንዱ ነበር። ከዚሁ አኳያ፣ ለመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበር (መኢሠማ) መመሥረትና መደራጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ፀጋዬ የኋላው፣ ከ1968 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የመኢሶን አባል ሆኖ፣ በወዛደሮችና በወጣቶች የኅቡዕ ጥናትና አደረጃጀትም ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው። በነበረው የሠራተኞች ማኅበር አመራር ተሳትፎውና በሠራተኞች መሀል በነበረው አክብሮት ምክንያት፣ በተለይ ከመስከረም 1969 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በአንድ በኩል፣ በሰደድ/ደርግ ከፍተኛ መሪዎች ድርጅታዊ አቋሙን ወደ ሰደድ እንዲቀይር ያልተቋረጠ ማስፈራሪያ ይደርስበት ነበር። በሌላም በኩል፣ እንደሌሎች የመኢሶን አባሎች ሁሉ፣ የኢሕአፓ የከተማ የግድያ ቡድንም ኢላማ እንደነበርም ያውቀው ነበር።

ፀጋዬ የኋላው፣ የካቲት 1969 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በደፈጣ ግድያ ሕይወቱን አጣ።

ፀጋዬ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪና በእርጋታ የማዳመጥ ባህሪ ነበረው። በሠራተኞች ማኅበር ውስጥ በነበረው የአመራር ኃላፊነት፣ የተጣበበ ጊዜ ቢኖረውም፣ የፖለቲካ እውቀቱን ለማዳበር ማንበብና መወያየትን እጅግ የሚያፈቅር ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top