ዘውዱ ዓለማየሁ
ዘውዱ ዓለማየሁ፣ ግንቦት 9 ቀን 1939 ዓ.ም. ከእናቱ ከወ/ሮ አስቴር ተሰማ እና ከአባቱ ከአቶ ዓለማየሁ ጉርሙ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አዲስ አበባ ውሰጥ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ኮተቤ ተብሎ በተለምዶ በሚጠራው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዳሪነት ነው።
በ1961 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ስዊድን አቀና። በስዊድንም ሉንድ ዮኒቨርሲቲ ትምህርቱን ተከታትሎ በፖለቲካል ሳይንስ እና አስተደደር የባችለር ኦፍ አርትስ ዲግሪውን አገኘ። በስዊድን ቆይታዉም በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ውስጥ በአባልነት ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር።
የየካቲት 1966 የኢትዮጵያ አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ በ1967 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥር የሠራተኛና ሥራ ማገናኛ ጽ/ቤት ውስጥ በክፍል ኃላፊነት መሥራት ጀመረ። ከመደበኛ ሥራው በተጓዳኝም ከመኢሶን አመራር የሚሰጠውን ሥራ በትጋትና በድብቅ ያከናውን ነበር።
በዚህ ሙያዊ የአስተዳደር ሥራውና ፖለቲካ ትግል ሕይወት ውስጥ ተጠምዶ እያለ ነሐሴ 13 ቀን 1969 ዓ.ም. ምሳ ሰዓት ላይ ካዛንቺስ ከቢሮው መኪናውን እያሸከረከረ በመውጣት ላይ እያለ፣ በኢሕአፓ የነፍሰ ገዳይ ቡድን ከግቢው በር ላይ በደፈጣ በተተኮሰበት እሩምታ ጥይት በርካታ የሰውነቱ ክፍል ላይ ተመትቶ በተወለደበት የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሳይደርስ ሕይወቱ ባጭር ተቀጨ።
ብዙዎች ዘውዱን የሚያስታውሱት በጨዋነቱ፣ በደግነቱ፣ በሰው አክባሪነቱ እና በትሁትነቱ ነው።