ዓለምሸት ተዘራ

ዓለምሸት ተዘራ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ አዳነች ወንድም አገኘሁ እና ከአባቱ ከአቶ ተዘራ ዘሪሁን በ1947 ዓ.ም.  በቀድሞ አጠራር ሲዳሞ ክፍለ አገር ሲዳማ አውራጃ ዳራ ወረዳ ቀባዶ ተወለደ።

ዓለምሸት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀባዶና እንዲሁም አገረ ሰላም ደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት ተማረ። ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ይርጋዓለም ራስ ደስታ ት/ቤትና ነጌሌ ቦረና አፄ ካሌብ ት/ቤት አጠናቋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኃላ  ከኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ተመርቋል።

ገና በለጋ እድሜው የፖለቲካ ትግሉን የተቀላቀለው ዓለምሸት በአዲስ አበባ የሕዝብ ድርጀት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ካገለገለ በኋላ፣ መኢሶን ትግሉን በኅቡዕ ለመቀጠል ሲወስን፣ ሲዳሞ ክፍለ አገር ጌዴኦ አውራጃ ተሰማራ። ዓለምሸት፣ በጌዴኦ አውራጃ ዘሪሁን ጋቲራና ታደለ አበበ ከሚባሉ ሌሎች ጓዶች ጋር ሆነው በቡሌ ወረዳ ገበሬውን ማደራጀት ጀመሩ።

በዚሁ አካባቢ፣ ነሐሴ 27 ቀን 1969 ዓ.ም.  በአንድ ወዳጅ ገበሬ ቤት እያሉ ከዲላ በተላኩ የደርግ ጦር አባላትና የተወሰኑ የአካባቢው ገበሬዎች ተከበቡ። አለምሸትና ጓዶቹ፣ ጦሩ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅሎ እንደመጣባቸው ሲያስተውሉ “በገበሬ ላይ አንተኩስም” በማለት መሣሪያቸውን አስቀምጠው ከቤት እንደወጡ ጦሩ እዚያው ባሉበት ቦታ ረሸናቸው።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top