ዘሪሁን ጋቲራ

ዘሪሁን ጋቲራ፣ ከእናቱ ከወይዘሮ አዳነች ገብረ ሥላሴ እና ከአባቱ ከአቶ ጋቲራ ዱላ በ1936 ዓ.ም. ተወለደ። ዘሪሁን ያደገው ከሦስት ወንድሞቹና ሁለት እህቶቹ ጋር ነው።  የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ሲዳሞ ፣ ዲላ ከተማ፣ አፄ ዳዊት ትምህርት ቤት ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው አዲሰ አበባ  በሚገኘው ተግባረ እድ ትምህርት ቤት ነው።

ከዚያም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እያለ የነፃ ትምህርት እድል በማግኘቱ ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ ከዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ተመድቦ በማስተማር ላይ እያለ በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን የተማሪዎች አመጽ አነሳስታችኋል በመባል አሱና ጓደኞቹ ከሥራቸው ተባረሩ። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው እንዳይሠሩ በመታገዳቸው ለበርካታ ወራት ሥራ አጥ ሆነው ከቆዩ በኋላ ምህረት ተደርጎላቸው ዘሪሁን በሕዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር ውስጥ ለመቀጠር ቻለ።

ከዚያም በአብዮቱ ወቅት፣ የቆመለትን ድሃ ገበሬ በቅርብ ሆኖ ለማገልገል ያስችለኛል ብሎ ወዳመነበት ወደ መሬት ይዞታ ሚኒስቴር ተዛውሮ የጌዴኦ አውራጃ የመሬት ይዞታ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በማገልገል ላይ እያለ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ ከድርጅቱ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሥራውን ለቅቆ እዚያው በሚሠራበት በጌዴኦ አውራጃ በኅቡዕ ትግል ተሠማራ።

በዚህ ሁኔታ በአውራጃው ውስጥ ታደለ አበበ እና ዓለምእሸት ተዘራ ከሚባሉ ሌሎች ጓዶች ጋር ሆነው በቡሌ ወረዳ እየተንቀሳቀሱ በነበሩበት ወቅት ነሐሴ 27 ቀን 1969 ዓ.ም. ባደሩበት በአንድ ወዳጅ ገበሬ ቤት እያሉ ከዲላ በተላኩ የመንግሥት ጦር አባላትና የተወሰኑ የአካባቢው ገበሬዎች ተከበቡ። ዘሪሁንና ጓዶቹ፣ ጦሩ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅሎ እንደመጣባቸው ሲያስተውሉ “በገበሬ ላይ አንተኩስም” በማለት መሣሪያቸውን አስቀምጠው ከቤት እንደወጡ ጦሩ እዚያው ባሉበት ቦታ ረሸናቸው።

ዘሪሁን ጋቲራ በተገደለበት ወቅት የሰላሳ ሦስት ዓመት ጎልማሳ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top