ምትኩ ተርፋሳ

ምትኩ ተርፋሳ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ መገርቱ ስንታሮና ከአባቱ ከአቶ ተርፋሳ ሊሙ በ1943 ዓ.ም. በኅዳር ወር ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን መንዲ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታተለ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቢሾፍቱ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ ሲከታተል ቆይቶ  ትምህርቱን ከመጨረሱ በፊት  በዚያን ጊዜ ለተማሪዎች ይሰጥ በነበረው የፊልድ ሰርቪስ ፕሮግራም አሜሪካ ተልኮ አንድ ዓመት ቆይቶ ተመልሷል። ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ኢኮኖሚክስ ተምሯል።

በመቀጠልም፣ ጀርመን አገር ሄዶ ሁለት ዓመት ቆይቶ አገሩ ተመልሷል። ኢትዮጵያ እንደተመለሰ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት የሸዋ ክፍለ አገር የመናገሻ አውራጃ  ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል።

ምትኩ፣ የመኢሶን አባል ከሆነ በኋላ በተለያዩ የትግል ዘርፎች ተሳትፏል። የመኢሶን ፕሮግራም ለሕዝብ ይፋ ሲሆን በግንባር ቀደምትነት የድርጅቱን ፕሮግራም በአፋን ኦሮሞ ከተረጎሙት ጓዶች መሃል አንዱ ነበር።

መኢሶን የትግል ስልቱን ቀይሮ ኅቡዕ ሲገባ፣ ምትኩ ከእነ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ጋር ሙሎ  ወረዳ ሆኖ ትግሉን እንዲያስተባብር ተመደበ። እዚያም እያለ ነሐሴ  30 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. አርፈውበት የነበረው ቤት  በደርግ ወታደሮች ተከበበ። ምንም እንኳን የድርጅቱ አመራር የነበሩት ዶ/ር ከበደ መንገሻና ዳንኤል ታደሰ፣  ለእነ ምትኩ ተርፋሳ፣ ደንቢ ዲሳሳና ደንበል አየለ በሰላም እጃቸውን  እንዲሰጡ ቢመክሯቸውም እነሱ ግን አሻፈረን ብለው ከከበባቸው የደርግ ወታደሮች ጋር እየተታኩሱ ተሰው።

ምትኩ ተርፋሳ፣ በጠባዩ ተግባቢና  ተጫዋች ሲሆን በዕረፍት ጊዜው የቅርጫት ኳስ መጫወት ይወድ ነበር።

ምትኩ፣ ሲሰዋ የ27 ዓመት ወጣት ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top