ዳንኤል ታደሰ

ዳንኤል ታደሰ ከእናቱ ከወ/ሮ ፋንታዬ ሩፋኤል እና ከአባቱ ከፊታውራሪ ታደሰ ማርቆስ በአዲስ አበባ ከተማ ታኅሳስ 23 ቀን፣ 1934 ዓ.ም. ተወለደ። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን እና እንዲሁም ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት  ቤት ነበር። ዳንኤል፣ በሊሴ ገብረማርያም ቆይታው ከክፍሉ በተደጋጋሚ ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ያስታውሱታል። በመስከረም 1952 ዓ፣ም. የሁለተኛ  ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ፣ በፈረንሳይ የትምህርት ሥርዓት ባካሎሪያ የተባለውን ፈተና በአጥጋቢ ውጤት ካለፈ በኋላ የነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ፈረንሣይ አገር አቀና። በዚያን  ወቅት የ18 ዓመት ወጣት ነበር።

በመጀመሪያ ትምህርቱን የተከታተለውም፣ ፈረንሳይ በሊዮን ከተማ በሚገኘው የሊዮን የተግባር ሳይንስ ኢንስቲትዩት ነበር። በዚህ ተቋም ትምህርቱን ለአራት ዓመታት ከተከታተለ በኋላ በ1955 ዓ.ም. በምህንድስና የባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪውን ተቀበለ። ለትምህርት በነበረው ፍቅር የተነሳ የምህንድስና ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ፓሪስ በመሄድ ብዙ እውቅ የአገር እና የድርጅት መሪዎችን በማፍራት በሚታወቀው የፖለቲካል ሳይንስ ብሔራዊ ኢንስቲትዩት በመግባት ትምህርቱን ለሁለት ዓመታት ከተከታተለ በኋላ በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ተጨማሪ ዲግሪ አገኘ።

በፓሪስ ቆይታው ወቅት በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ኃይሌ ፊዳን ከመሳሰሉ በንቃት ከሚሳተፉት የፖለቲካ ግንባር ቀደም ተማሪዎች መሃል አንዱ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በፓሪስ የአፍሪካ ተማሪዎች ፌዴሬሽን ውስጥ የጎላ ሚና ነበረው። በዚህም ተሳትፎው በኋላ የጊኒ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሪ ለመሆን ከበቃው ከአልፋ ኮንዴና፣ እንዲሁም ከእውቁ የሴኔጋል የታሪክ ተመራማሪ ከሼክ አንታ ዲዮፕ ጋር እጅግ የቅርብ ትውውቅ እና ጓደኝነት አፍርቶ ነበር።

በ1958 ዓ.ም.ዳንኤል በፓሪስ የነበረውን ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በመጀመሪያ በኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ኩባንያ፣  በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በሙያው አገልግሏል። ከጥቅምት 1961 እስከ ግንቦት 1961 ዓ.ም. ፈረንሣይ አገር ተጨማሪ ስልጠና ወስዷል። ዳንኤል፣ በነሐሴ 1960 ዓ.ም. የተቋቋመውን የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄን (መኢሶን) ከመሰረቱት ጠንሳሽ አባላትና መሪዎች መሃል አንዱ ነበር።

ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት በፊትና ከዚያም በኋላ በአገር ቤት የመኢሶንን የኅቡዕ እንቅስቃሴዎች በማቀናበር እና በግንባር ቀደምነት በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው። በ1966 ዓ.ም. በኅቡዕ ይበተኑ የነበሩ ጽሕፎችን በመጻፍና አርትኦት በማድረግም ይሳተፍ ነበር። በተለይም “ሽሙጥ” ተብላ ትታወቅ የነበረችውና በድብቅ “እንዳመቻት” የምትበተን ተወዳጅ የፖለቲካ አቃቂር ጋዜጣ አዘጋጅም ነበር።

ዳንኤል በየካቲት 1968 ዓ.ም የከተማ ልማት እና ቤቶቸ ሚኒስትር ሁኖ ተመደበ። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በሚንስትርነት ከመቀላቀሉ በፊት የወጣው የከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤት ዓዋጅ መሠረታዊ ቸግሮቸ እንደነበሩበት በመገንዘብ ጉድለቶቹን ለመቅረፍ ዳንኤል ያቀረበውን የማሻሻያ ረቂቅ ዓዋጅ ሥልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግሥት ሳይቀበለው ቀረ። በነሐሴ 1969 ዓ/ም አጋማሸ መኢሶን ሂሳዊ ድጋፍ የሚለውን የትግል መሥመር ትቶ የታወቁ መሪዎቹን እና አባላቱን ኅቡዕ ማስገባት ሲገደድ ዳንኤልም የቤቶች እና የከተማ ልማት ሚንስትርነት ሥልጣኑን ፣ ባለቤቱን እና ሦስት ጨቅላ ልጆቹን ትቶ ከአዲስ አበባ ብዙ ሳይርቅ ሙሎ ወረዳ ለጊዜው በስውር እንዲቀመጥ ተወሰነ። እርሱ በኅቡዕ የነበረበት ስፍራ፣ የመኢሶን ጠቅላይ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ የነበረው ዶ/ር ከበደ መንገሻ፣ ምትኩ ተርፋሳ፣ ደንቢ ዲሣሣ እና ደምበል አየለ ይገኙበት ነበር።

ነሐሴ 30 ቀን 1969 ዓ/ም ዳንኤል እና ጓዶቹ ያሉበት ስፍራ በደርግ የጸጥታ ሃይሎች ተከቦ እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ዳንኤል እና ዶ/ር ከበደ ከእነርሱ ወጣት የነበሩትን እና ያነሰ ድርጅታዊ ኃላፊነት የነበራቸውን ጓዶች አሰናብተው፣ እነርሱም ተሰነባብተው በያዙት መሣሪያ እራሳቸውን ሰዉ። ይህ የግል ምቾታቸውን ትተው ለድርጅቱ ዓላማ መሳካት ከከፈሉት ዋጋ በተጨማሪ በሕይወታቸው የከፈሉት የመጨረሻው መስዋዕትነት ነበር።

ዳንኤል ለአገር የሚጠቅም  እምቅ የአዕምሮ ጉልበትና ልምድ ነበረው። ቢሆንም ግን፣ ይህቺ ሕዝቦቿ ከችግርና መከራ ተላቀው በደስታ እንዲኖሩባት የሚመኛትን አገሩን ሳያይ በለጋ የ35 ዓመት እድሜው ተቀጠፈ።

ዳንኤል ብዙ ስቃይ እና ሰቆቃ ከደረሰባትና ዛሬ በሕይወት ከምትገኘው የትዳር አጋሩ ከወ/ሮ እንጉዳይ በቀለ ሁለት ወንድ ልጆች እና አንዲት ሴት ልጅ አፍርቷል።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top