ከበደ መንገሻ (ዶ/ር)

ዶ/ር ከበደ መንገሻ፣ ግንቦት 1 ቀን 1927 ዓ.ም. በወሎ ክፍለ አገር በወረኢሉ አውራጃ ገነቴ ቆላ በተባለ ቀበሌ ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በደሴ ከተማ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው አዲስ አበባ በሚገኘው ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ነው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአመርቂ ውጤት እንዳጠናቀቀም ከሮም ዩኒቨርሲቲ የእስኮላርሺፕ እድል አግኝቶ ወደ ጣልያን አገር አቀና:: በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለበርካታ ዓመታት በመከታተል በሲቪል  ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪውን ለማግኘት በቃ።

በጣልያን አገር የዶክትሬት ዲግሪውን እንዳገኘም በግንቦት 1957 ዓ.ም.  ስካንስካ ሲሜንት በተባለው ግዙፉ የስዊድን ኩባንያ ከፍተኛ ደመወዝ እና የመኖሪያ ፈቃድ የሚያሰጥ የሥራ ዕድል አግኝቶ ወደ እስቶክሆልም ስዊድን ሄደ። ሆኖም፣ ዶ/ር ከበደ በወር 6000 የስዊድን ክሮና ያስገኝ በነበረው ሥራው ላይ ብዙ አልቆየም። ከጥቂት ወራት በኋላ ያንን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሥራውን በፈቃዱ ለቆ በምትኩ ለአብዮታዊ ሥራዎቹ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት በቂ ጊዜ የሚሰጠውን ሥራ ፈልጎ አገኘ።

አንድ አሮጌ አልባሳት እየሰበሰበ ወደ አፍሪካ የሚልክ ምግባረ-ሰናይ ድርጅት በየሳምንቱ እሁድ ሦስት ሰዓታት ብቻ ለሚከናወን የመጋዘን ጠረጋ ቀጠረው። የተቀጠረበት 350 የስውዲን ክሮና ደሞዙ በዚያን ጊዜ ለአንድ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ይሰጥ ከነበረው 800 የስውዲን ክሮና ግማሽ እንኳን ባይሆንም፣  ዶ/ር ከበደ ካለምንም ማቅማማት ሥራውን ተቀበለው። ቁጥብ ኑሮ በመኖር ወጪውን ከገቢው ጋር አስተካከለ።

ነጋ ጠባ የሚመገበው የገበታ ቅቤና ጨው ብቻ በአናቱ የተጨመረበት ቅቅል የፓስታ ዝርያ ሆነ። የሚኖርበት ቤት በዚያ እጅግ የሚያስከፋ ብርድ ባለበት በስውዲን አገር ማሞቂያና ሙቅ ውሃ እንኳን አልነበረውም። የሚለብሳቸው ልብሶችም ከዚያው ከምግባረ-ሰናይ ቀጣሪ ድርጅቱ መጋዘን እንዲወስዳቸው የሚፈቀዱለትን አሮጌ ልብሶች ነበር። ዶ/ር ከበደ አዲስ ልብስ ለብሶ ታይቶ አያውቅም። የመጋዘን ማጽዳት ሥራውንም የሚሠራው እሁድ ቀን ብቻ ስለነበረ እሱ ቆርጦ ላመነበት አብዮታዊ ሥራዎቹ በቂ ጊዜ ሰጠው።

ይህ ሁሉ ሲሆን ዶ/ር ከበደ አንድም ቀን ኑሮውን አማርሮ ወይንም ሕይወቱ ምን እንደሚመስል ለማንም ተናግሮ አያውቅም። የቅርብ ወዳጆቹና ጓዶቹ እራሳቸው የዚህን እጅግ ቁጥብ ኑሮውን ዝርዝር ያወቁት በጥር 1962 ዓ.ም በስውዲን የኢትዮጵያ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ኤምባሲ በያዙ ጊዜ ፍርድ ቤት ተከሰው ቅጣታቸውን ለመመዘን ገቢያቸው ተመርምሮ ይፋ በተደረገበት ወቅት ነበር።

የዘወትር ምኞቱ በአገሩ ውስጥ ለውጥ መጥቶ ማየት ነበርና ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በመተባበር ከፖርቱጋል አንድ እድሜ ጠገብ የኅትመት መሣሪያ አስመጥቶ፣ ስቶክሆልም አንድ ቀዝቃዛ ምድር ቤት ውስጥ አስገብቶ፣ ቀንና ለሊት የኅትመት ሥራውን በቋሚነት ማከናወን ጀመረ። አመዛኝ  ጊዜውን የሚያውለው፣ እንደዛሬው የኅትመት ቴክኖሎጂ ሥራን ባላቀለለበት ዘመን በመሆኑ፣ እያንዳንዱን ፊደል በጣቶቹ  እየለቀመና በኅትመት ገበታው እየገጣጠመ ታገል እና ታጠቅ በመባል ይታወቁ የነበሩትን በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር መጽሔቶች በማተም ነበረ። እጄን አልሰጥም ብሎ የራሱን ሕይወት እስከሰዋበት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1969 ዓ.ም ድረስ ይለቅማቸው በነበሩት የኅትመት ፊደላት ስለት የተተፈተፉት የጣቶቹ ጠባሳዎች እንዳሉ ነበሩ።

ዶ/ር ከበደ፣ ስዊድንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ያሉ ኢትዮጵያዊ ተማሪዎችን ደከመኝ ሳይል እየተዘዋወረ ያነቃና  ያደራጅ ነበር። ሌሎች ሰዎች የሚሉትን በእርጋታ ማዳመጥ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልፁ፣ እንዲናገሩና መድረኮችን ተጋርተው እስተዋፅኦ እንዲያደርጉ መገፋፋት በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅበት ባህሪው ነበር።  የእያንዳንዱን አስተያየት ሲያዳምጥና እንዲሁም ከተሳታፊዎች ጋር ያለውን የነቃ መስተጋብር ያየ ሰው፣ ዶ/ር ከበደ አድካሚና አሰልቺ ከሆኑ የኅትመት ሥራዎቹ ተነስቶ የመጣ ነው ብሎ መገመት አይችልም። ደማቅ ሕዝባዊ መድረኮች ላይም ልታይ-ልታይ ያለማለቱ ዋና መለያው ነበር። እሱን በቅርብ ለማወቅ እድል ያገኙ ታናናሾቹ ሁሉ ያለማመንታት የሚመሰክሩት፣ ይህ ከራስ-ወዳድነት የጸዳ አብዮተኛ ተምሳሌትነቱ እንዴት እንደማረካቸውና  ወደ ትግል ሕይወት እንዳስገባቸው ነው።

ዶ/ር ከበደ በነሐሴ ወር 1960 ዓ.ም. የተመሠረተው የመላው ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መሥራች የአመራር አባል ሲሆን ከዘጠኝ አመታት በኋላ በህልፈቱ ወቅት የድርጅቱ ጠቅላይ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ድርጀቱን ይመራ ነበር።

በ1965 ዓ.ም፣ ዶ/ር ከበደ መንገሻ በስዊድን ከስምንት ዓመታት የማንቃት እና የማደራጀት ድርጅታዊ ሥራው በኋላ፣ ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት ወደ ሱዳን ጎራ ብሎ በወቅቱ ካርቱም ዩኒቨርሲቲ ያስተምር የነበረውን፣ ጓዱን ዶ/ር ከድር  መሐመድን በመገናኘት ስለ ድርጅቱ እንቅስቃሴ ከተመካከሩ በኋላ ጉዞውን ወደ ኢትዮጵያ ቀጠለ። ኢትዮጵያም እንደደረሰ  ቀደም ብለው አገር ቤት ገብተው ከነበሩት የመኢሶን ጓዶች ጋር የኅቡዕ ትግሉን ማስተባበር ቀጠለ። በአዋሽ ሸለቆ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም በምህንድስና ሙያው ማገልገል ጀመረ። ሕዝባዊ አብዮቱን ተከትሎ በ1968 ዓ.ም. የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲቋቋም የአዋሽ ሸለቆ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን ለቆ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት  የአዲስ አበባና አካባቢዋ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ማገልገል ጀመረ።

በነሐሴ  1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ፣ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ከሌሎች የመኢሶን ጓዶች ጋር ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቅ  በከተማና በገጠር የነበረውን  ድርጀታዊ የኅቡዕ እንቅስቃሴ ከቅርብ ርቀት ለማስተባበር አስተማማኝ ነው ተብሎ በተገመተው ሙሎ ወረዳ ውስጥ ሆኖ እንዲሠራ ተመደበ። ዶ/ር ከበደና ጓዶቹ፣ እዚያ እንዳሉ ነሐሴ  30 ቀን 1969 ዓ.ም. ደርግ የላካቸው ወታደሮች እነ ዶ/ር ከበደ የነበሩበትን ቤት  ከበው እጅ እንዲሰጡ ይጠይቋቸዋል። የመኢሶን አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር ከበደ መንገሻና ዳንኤል ታደሰ፣ አብረዋቸው የነበሩትን ወጣት የመኢሶን ታጋዮች እጃቸውን እንዲሰጡ አበረታተው ያሰናብቷቸዋል። ከዚያም ያረፉበት ቤት ባለቤት የነበረው ገበሬ እጅግ ቢለምናቸውና ቢማጸናቸውም እምቢ ብለው እርስ በርስ ከተሰነባበቱ በኋላ፣ ሁለቱም በየገዛ መሣሪያቸው እራሳቸውን  መስዋዕት አደረጉ። ይህ በስቃይ ተንገላተው የድርጅቱን ሚስጥር ላለማባከን የከፈሉት የመጨረሻው ዋጋ ነበር።

ሠርቶ የማይደክመው፣ ለቁሳዊና ዓለማዊ ምቾት ቁብ የሌለው፣ መንፈሰ ንጹሑና ቆራጡ ከበደ መንገሻ፣ ኑሮውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና አብዮታዊ ለውጥ አሳልፎ የሰጠ፣ ድንቅ ስብዕና የተላበሰ ኢትዮጲያዊ ምሁር ነበር። በመጨረሻም ለሚወደው ወገኑና ለገነባው ድርጅት ህልውና ሲል በተወለደ በ42 ዓመቱ ውድ ሕይወቱንም ሰዋ።

ዶ/ር ከበደ መንገሻ፣ ለአጭር ጊዜ  ከዚህ ዓለም  በሞት ከተለየችው ከወ/ሮ ፀሐይ ፈለቀ ጋር ትዳር መስርቶ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top