መኮንን ተስፋዬ
መኮንን ተስፋዬ፣ አዲስ አበባ ከተማ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ማኅበር መሪ ነበር። በኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሠአማ) አመራር ውስጥም አገልግሏል። ከዚያም በመቀጠል፣ በአዲስ መልክ በተደራጀው ከመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር (መኢሠማ) ሊቀ መንበር ከቴዎድሮስ በቀለ ጋር ጉልህ የማንቃትና የማደራጀት ድርሻም ነበረው።
በመኢሶን አባልነቱም በአዲስ አበባና አካባቢው የነበሩ ሠራተኞችን በመኢሶን ዙርያ በመሰብሰብና በኅቡዕ በማደራጀት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። እንዲሁም የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ውስጥ ከተመደቡ የመኢሶን ጓዶች ጋር በመሆን ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሠራተኞች ስለ ሠራተኛው መብትና ሠራተኛው በትግሉ ውስጥ ሊኖረው ስለሚገባው ቦታ የፖለቲካ ንቃት እንዲያገኙ ያደርግ ነበር።
መኢሶን፣ ነሐሴ አጋማሽ 1969 ዓ.ም. የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ ኅቡዕ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ ደርግ፣ በመላው የድርጅቱ አባሎች ላይ ባካሄደው የእስራትና የግድያ ዘመቻ፣ መኮንን ተስፋየ በ1970 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ታሰረ። መኮንን ታስሮ ብዙ ስቃይና እንግልት ከደረሰበት በኋላ፣ በድብቅ ያለፍርድ በደርግ ተገደለ።