አሰፋ ነመራ

አሰፋ ነመራ በወለጋ ከፍለ አገር በነቀምት አውራጃ ዲጋ ወረዳ ቤንዲ በምትባል መንደር በ1941 ዓ/ም ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህሩቱን ዲጋ ሆዶዶ ትምህርት ቤት ተከታተለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ነቀምት ከተማ ከተከታትለ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው በዕደማርያም ላቦራቶሪ ትምህርት ቤት ገባ። እዚያም የነበረውን ትምህርት እንዳጠናቀቀ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ፋኩልቲ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ። በኮሌጅ ተማሪነቱ ወቅት በተማሪው እንቅስቃሴ በንቃት ይሳተፍ ነበር።

የኢትዮጵያ አብዮት ግቡን ይመታ ዘንድ በነበረው ጽኑ ፍላጎት የበኩሉን ለማበርከት አንድ ዓመት የቀረውን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ በህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት የጅባት እና ሜጫ አውራጃ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።

በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. መኢሶን ትግሉን በኅቡዕ ለመቀጠል ውሳኔ ሲያደርግ፣ አሰፋም ይሰራበት በነበረበት በጅባትና ሜጫ አውራጃ ከነዶ/ር ተረፈ ወልደ ጻዲቅ ጋር እንዲሰማራ ተመደበ። ይሁን እንጂ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ እሱና ሌሎች ጓዶች፣ በኅቡዕ ይኖሩበት የነበረውን ቤት የሚያውቁና በአገናኝነት ይሠሩ የነበሩ ሁለት የጅባትና ሜጫ አውራጃው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ባልደረቦች በፈጸሙት ክሕደት ምክንያት የመኖሪያቸው ቦታ ምስጢር ደርግ እጅ ገባ።

ከዚያም፣ በነዚህ ሁለት ከሃዲዎች ጠቋሚነት በቀጥታ እየተመሩ የመጡት የደርግ ልዩ ኃይል ወታደሮች፣ አሰፋና ሌሎቹ ጓዶች የነበሩበትን ቤት ሲከበብ እጃቸውን ለመስጠት ተገደዱ። ነገር ግን፣ የደርግ ልዩ ኃይል ወታደሮች እጃቸውን በሰላም የሰጡትን አሰፋንና ሌሎች ዘጠኝ ጓዶቹን እዚያው በተያዙበት አካባቢ ረሸኗቸው።

አሰፋ የሁለተኛ ደረጃ ታማሪ ከነበረበት ግዜ ጀምሮ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ በከፍተኛ ንቃት ይሳተፍ የነበረ አብዮታዊ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top