ዮሐንስ መስፍን
ዮሐንስ መስፍን በሰኔ ወር 1944 ዓ/ም ከእናቱ ከወ/ሮ ዮቫን መሰፍን እና ከአባቱ ከአቶ መስፍን ዘለለው በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ።
ዮሐንስ ከ1ኛ እስከ 11ኛ ከፍል ያለውን ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ዮሴፍ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው። ከክፍሉ ከፍተኛውን ውጤት በማምጣትም ይታወቅ ነበር።
ዮሐንስ መስፍን፣ በወቅቱ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳትፎው ሳቢያ ከትምህርት ቤቱ በመባረሩ፣ እንዲሁም ደህንነቱ በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ክትትል አደጋ ላይ ስለወደቀ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ወደ አሜሪካ በመሄድ ሰሜን ዳኮታ ግዛት በሚገኘው ኦክ ግሮቭ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
ዮሐንስ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም የኮሌጅ ትምህርቱን ሚኒሶታ ግዛት በሚገኘው ኮንኮርዲያ ኮሌጅ ጀመረ። በዚህን ወቅት ከትምህርቱ በተጓዳኝ በቀድሞው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር (ESUNA) ስር የሚኒሶታ ቻፕተርን በመቀላቀል በንቃት ተሳትፏል። ማህበሩም በእንግሊዘኛ ያወጣው በነበረው Challenge ተብሎ ይጠራ በነበረው መጽሔት ላይ፣ ዮሐንስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ባበረከታቸው ጥልቀት ባላቸው የትንታኔ መጣጥፎቹ ይታወሳል።
በጥር ወር 1964 ዓ.ም. የኮሌጅ ትምህርቱን በአውሮጳ ለመቀጠል ወስኖ ጀርመን በርሊን ሄደ። ዉስብስቡን የፍልስፍና ትምህርት አዲስ በተማረዉ የጀርመንኛ ቋንቋ አጥንቶና ፈተናዎቹን በከፍተኛ ማዕረግ አልፎ ከፍራይ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ዉጤት በማስተርስ ዲግሪ ተመረቀ። በጀርመን ቆይታውም በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር (አኢተማ) ጉልህ ተሳትፎ አድርጓል። በጀርመን የማህበሩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል እና “ታጠቅ“ በመባል ይታወቅ የነበረውን የድርጅቱን የቲዎሪ መጽሔትና የእንግሊዝኛ ጽሁፎች አዘጋጅ በመሆን አገልግሏል።
በ1969 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ዮሐንስ ድርጅቱ መኢሶን ያደረገለትን ጥሪ በመቀበል ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። በዚያን ጊዜ መኢሶን፣ በሂሳዊ ድጋፍ ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን በመገንዘብ በህጋዊ መንገድ በመሥራታቸው የተጋለጡትን አባላቱን እና መሪዎቹን ወደ ገጠር ለመሰወር እና ተተኪ አመራር ለማዋቀር የሚጥርበት ወቅት ነበር። ዮሐንስ ይህንን ጉድለት ለሟሟላት ከውጪ ወደ አገር ቤት ከመጡት አንዱ ነበር።
መኢሶን ኅቡዕ በገባበት በዚያ አስቸጋሪ ዘመን፣ ዮሐንስ ድርጅታዊ ግዴታውን እየተወጣ ሳለ በ1970 ዓ.ም. ጥር ወር መጀመሪያ ላይ፣ አውሮጳ በነበረበት ወቅት ያውቀው በነበረ የመንግሥት ደጋፊ ተጠቁሞበት ታሰረ። ጥቂት ጊዜ በደርግ ምርመራ ክፍል ከቆየ በኋላ ሌሎች የመኢሶን ጓዶች ታስረው ወደ ነበረበት 4ኛ ክፍለ ጦር ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዛወረ። እዚያም ጥቂት ካቆዩት በኋላ በ1970 የካቲት ወር መጨረሻ ላይ አስፋው ሺፈራው እና ጀማል አባስ ከተባሉ የመኢሶን ጓዶች ጋር ተወስዶ፣ በምርመራ ወቅት አስከፊ አካላዊ ስቃይ ከተፈጸመበት በኋላ ያለ ምንም ፍርድ በድብቅ በደርግ መንግሥት ተገደለ። ብሩህ አዕምሮና ለአገር የሚጠቅም እምቅ ጉልበት የነበረው ዮሐንስ፡ ያለምንም ፍርድ ሕይወቱ የተቀጠፈው በ26ኛ ዓመቱ ላይ ነበር።
ዮሐንስ ከጀርመናዊት ጓደኛው አንድ ልጅ አፍርቷል።