ብርሃኑ ገመዳ

ብርሃኑ ገመዳ ከእናቱ ከወ/ሮ ናሲሴ ማሊሞ እና ከአባቱ ከአቶ ገመዳ ዱሬሳ በወለጋ ክፍለ አገር በጊምቢ አውራጃ፣ በመነሲቡ ወረዳ መንዲ ከተማ በ1940 ዓ/ም ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው መንዲ አጠናቀቀ።

በወቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች እየተመረጡ ወደ ተለያዩ የሙያ ትምህርት ቤቶች ይመደቡ ነበር። ብርሃኑም ጥሩ ውጤት ስልነበረው በአዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ተመድቦ የሚሰጠውን የአራት ዓመት ትምህርት አጠናቅቆ በሂሳብ አያያዝ በዲፕሎማ ተመረቀ። ከፍተኛ የትምህርት ጉግት ስለነበረውም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በግሉ ተዘጋጅቶና ተፈትኖ አጥጋቢ ውጤት በማስመዝገቡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቻለ። ትምህርቱንም ይከታተል የነበረው በንግድ ሥራ አስተዳደር ዘርፍ ነበር።

በተጓዳኝ፣ በወቅቱ ይካሄድ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በንቃት ይሳተፍ ነበር። የተማሪዎች ማህበር መሪ የነበረውን የጥላሁን ግዛውን ሞት ተከትሎ፣ በጸጥታ አስከባሪዎች እና በተማሪዎች መካከል በነበረው ግጭት፣ የጸጥታ አስከባሪዎች እይታ ውስጥ ገብቶ ደህንነቱ አደጋ ላይ ወደቀ። በሁኔታው ተመሳሳይ ስጋት ውስጥ ከነበረው ከቅርብ ጓደኛው እና ጓዱ ከኃይሉ ገርባባ ጋር ተመካክረው በአንድነት በመንዲ፣ በአሶሳ በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ተሰደዱ። በሱዳን ቆይታውም ሕግ አጠና።

ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት በኋላ ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ በወለጋ ክፍለ ሃገር የመሬት ይዞታ ኃላፊ ነበር። በዚህም የላቀ ኃላፊነቱ የየካቲት 1967 የመሬት ላራሹን አዋጅ ሥራ ላይ በማዋል፤ የወለጋ አርሶ አደሮችን ጥቅሞችን ለማስጠበቅና መብቶችን ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ብርሃኑ፣ የመኢሶን ጠቅላይ ኮሚቴ አባል በመሆኑ፣ ድርጅቱ በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. ኅቡዕ ሲገባ በተሰጠው ከፍተኛ ድርጅታዊ ኃላፊነት፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተደብቆ ድርጅታዊ ሥራዎችን በስፋት ያቀነባብር ነበር።

ሆኖም፣ በሚያዚያ 1970 ዓ.ም.፤ በድብቅ ከሚኖርበት ከሰባራ ባቡርና በቅዱስ ዮሐንስ ጠበል መካከል በሚገኘው አዲስ ሞዴል ከሚባል የመኖሪያ አፓርትመንት ሕንጻ ውስጥ አንድ ድርጅቱን በከዳ “የሕዝብ ክንፍ” መስራች ነኝ በሚል የቀድሞ አባል ጠቋሚነት በሰደድ ካድሬዎችና የደርግ ወታደሮች ተከበበ። አንሶላውን እንደገመድ ተጥቅሞ በመስኮት በኩል ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ ስይሳካ ቀርቶ ሲወድቅ በጀርባ አጥነቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት። ከወደቀበት ማምለጥ ባይቻለውም በያዘው ሽጉጥ ከከበቡት ስዋች መሃል ጥቂቶቹን አስወግዶ አራሱንም ሰዋ። በዚህም የሚያውቀው በርካታ ድርጅታዊ ምስጢር ተጠብቆ እንዲቆይ አደረገ።

ብርሃኑ፣ ቆራጥና መንፈሰ ጠንካራ አብዮታዊ ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top