ቆንጂት ከበደ
ቆንጂት ከበደ፣ የካቲት 30፣ 1945 ዓ.ም. ከእናቷ ከወ/ሮ አሰለፈች ዳርጌና ከአባቷ ከደጃዝማች ከበደ ይርዳው አዲስ አበባ ተወለደች። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሊሴ ገብረ ማርያም ት/ቤት ከአጠናቀቀች በኋላ በፈረንሳይ አገር ከኤክስ-አን- ፕሮቫንስ ዩኒቨርስቲ በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማግኘት ተመርቃለች።
ቆንጂት፣ በአውሮፓ ተማሪዎች ማህበርና በመኢሶን ውስጥ ሕዝብ በማንቃትና በማደራጀት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራት። በተለይም መኢሶን ውስጥ በተለያዩ የድርጅቱ የትግል እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራት፣ ሙሉ ጊዜዋን ለአብዮቱ የሰዋች ታጋይ ነበረች። የመኢሶን የሴቶች ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢሴአን) አመራር አባልም ሆና አገልግላለች።
ቆንጂት፣ መኢሶን በነሐሴ ወር አጋማሽ 1969 ጅምሮ በኅቡዕ ትግሉን ለመቀጠል ከወሰነ በኋላ የተሰጣትን ተግባራት ስታከናውን፣ አዲስ አበባ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ በደርግ ወታደሮች ተይዛ ታሰረች።
ሁለት ዓመት ያህል በእስር ላይ ከቆየች በኋላ፣ ሐምሌ 5 ቀን 1971 ዓ.ም. ከታሰረችበት እስር ቤት ተወስዳ ከኃይሌ ፊዳ፣ ደስታ ታደሰ፣ ኃይሉ ገርባባና ዶ/ር ንግሥት አዳነ ጋር ያለ ምንም ፍርድ በደርግ በድብቅ ተገደለች። እንደ ዶ/ር ንግሥት፤ የሷም አጽም በሚስጥር ተገድላ ከተቀበረችበት ከራስ አስራተ ካሳ ግቢ ወጥቶ በቤተሰቧ መካነ መቃብር በክብር አርፏል።
ቆንጂት ሕይወቷ ሲያልፍ የ26 ዓመት ወጣት ነበረች።