ኃይሉ ገርባባ
ኃይሉ ገርባባ፣ ወለጋ ክፍለ አገር ከአባቱ ከአቶ ገርባባ ጋጋ እና ከእናቱ ከወ/ሮ አስቻለች ፋንታ በሆሮ ጉድሩ አውራጃ ጂማ ገነቴ ከተማ ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሻምቡ ከተማ ከተከታተለ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ትምህርቱን አጠናቆ በዲፕሎማ ተመረቀ። በመቀጠልም ለጥቂት ጊዜ በባኮ የእርሻ ምርመር ተቋም ውስጥ ካገለገለ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲት ገባ። በፖለቲካል ሳይንስ ክፍል ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ውስጥ በነበረው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ሳቢያ ወደ ሱዳን ለመሰደድ ተገደደ።
በሱዳን ቆይታውም ካርቱም ዩኒቨርሲቲ በመግባት በፖለቲካል ሳይንስ በዲግሪ ተመረቀ። ከትምህርቱም ባሻገር ምስጢር በሆነ ድርጅታዊ ተልእኮ ሱዳን ሄዶ ካርቱም ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ሥራ ላይ ይገኝ ከነበረው የመኢሶን መሥራች አባል ከነበረው ከዶ/ር ከድር መሐመድ ጋር በቅርብ እየተገናኘ በኅቡዕ ሲንቀሳቀስ ቆየ።
የየካቲት 1966 ሕዝባዊ አብዮትን ተከትሎ በ1967 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ከካርቱም ወደ አገሩ በመመለስ መኢሶን የሰጠውን ተልእኮ በመፈጸም ላይ ቆይቶ በ1968 ዓ.ም. በወለጋ ክፍለ አገር የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ከምክትል ባልደረባው ከካሳሁን ብርሃኑ ጋር ሆኖ እስከ ነሐሴ 1969 ዓ.ም. አርሶ አደሮችን፣ ወዛደሮችን፣ የቢሮ ሠራተኞችን፣ መምህራንን እና ወጣት ተማሪዎችን በማደራጀትና በትግሉ በማሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
መኢሶን በደርግ ላይ የነበረውን ሂሳዊ ድጋፍ ሲያነሳ ኃይሉ ገርባባ በነሐሴ 1969 ዓ.ም. ወደ ገጠር ወለጋ ከጓዶቹ ጋር ለትግል ተሠማራ። በገጠር እያለ በደርግ መንግሥት ወታደሮች ተይዞ ታሠረ። በመጀመሪያ ወደ ነቀምቴ እስር ቤት ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተወሰደ በኋላ፣ አራተኛ ክፍለ ጦር እስር ቤት ከሌሎች የመኢሶን ጓዶቹ ጋር በእስር ላይ ቆየ።
ከታሠረ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ ሐምሌ 5 ቀን 1971 ዓ.ም. ከሌሎች የመኢሶን ጓዶቹ ከኃይሌ ፊዳና ከደስታ ታደሰ ጋር ከታሰረበት ከአራተኛ ክፍለ ጦር እስርቤት፣ እንዲሁም ከርቸሌ ታስረው ከነበሩት ከዶ/ር ንግሥት አዳነና ከቆንጂት ከበደ ጋር ተወስዶ በድብቅ ያለምንም ፍርድ በግፍ ተገደለ። ተገደሎ የተቀበረበት ሥፍራም እስካሁን ድረስ አልታወቀም።
ኃይሉ ገርባባ፣ በታጋይነቱና በቆራጥነቱ፣ እንዲሁም ጌረርሳ ተብሎ በሚታወቀው ሃሳብን የመገለጽና ቀስቃሽ በሆነው በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የቀረርቶ ክህሎት ልዩ ተሰጥኦ እንደነበረው በቅርብ የሚያውቁት ብዙዎች ይመሰክሩለታል።