ደስታ ታደሰ

ደስታ ታደሰ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ ፋንታዬ ሩፋኤል እና ከአባቱ ከፊታውራሪ ታደሰ ማርቆስ በአዲስ አበባ ከተማ በ1935 ዓ.ም. ተወለደ። ደስታ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ በሚገኙት የጄኔራል ዊንጌት እና የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤቶች ነው። ደስታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ለጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት እና በኢትዮጵያ የሞስኮ ራዲዮ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል አገልግሏል።  ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አቀና።

በሶቨየት ህብረት ቆይታውም ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በሲኒማቶግራፊ የትምህርት ዘርፍ ነበር። ከትምህርቱ በተጓዳኝም በሞስኮ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል ባልደረባ በመሆንም አገልግሏል። ደስታ፣ በነበረበት በሶቭየት ህብረትም ሆነ በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉትና አመራር ከሚሰጡት መሀል አንዱ ነበር። በሶቭየት ህብረት ቆይታው በአውሮጳ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ከነበራት እና ትምህርቷን በከፍተኛ ሕክምና ዘርፍ ከተከታተለችው ከዶክተር ንግሥት አዳነ ጋር ትዳር መስርተው አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል። 

በ1966 ዓ.ም. የለውጥ ማዕበል ሀገራችንን ሲጎበኝ ደስታ እና ባለቤቱ ዶ/ር ንግሥት አዳነ የጥቂት ዓመታት እድሜ የነበረውን ልጃቸውን ይዘው ለለውጡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከተመለሱም በኋላ አባል የነበሩበት ድርጅታቸው መኢሶን የሰጣቸውን የማንቃት እና የማደራጀት ተልእኮ በትጋት ይወጡ ጀመር። ደስታ፣ ከፖለቲካ ተሳትፎው በተጨማሪ ከታወቀው የፊልም ዳይሬክተር ሚሼል ፓፓታኪስ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ፊልም ማዕከልን አቋቁሟል።

ደስታ በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በራሽያን ቋንቋዎች ልዩ ተሰጥኦ እና ክህሎት ነበረው። በማኅበራዊ ሕይወቱም ከሰው ጋር በቀላሉ ተግባቢ እና ተጫዋች ነበር። የቅርብ ወዳጆቹ፣ ደስታ ሁሉን ሰው በእኩል ዓይን የማየት የማክበርና የመንከባከብ ባህሪ የነበረው፣ አዲስ የተዋወቁትን ሰዎች በአጭር ጊዜ መማረክና ወዳጅ ማድረግ የሚችል፣ ቁም ነገረኛና ጥሩ አድማጭ ነበር በማለት ያስታውሱታል።

መኢሶን ከደርግ ጋር ሂሳዊ ድጋፍ በሚለው መርሆ በተወሰነ ደረጃ ትብብር ሲጀምር ደስታ በባህል ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን ተመድቦ ድርጅቱ ትብብሩን አቋርጦ ኅቡዕ እስከገባበት እስከ ነሐሴ 1969 ዓ.ም. በዚሁ ደረጃ ሲያገለግል ቆይቷል። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ኅቡዕ ገብቶ በነበረበት በከምባታ እና ሃዲያ አውራጃ ባለቤቱን ዶ/ር ንግሥትን ጨምሮ ከሌሎች የመኢሶን ጓዶች ጋር በደርግ ወታደሮች እጅ ወደቀ። በደርግ የምርመራ ክፍል ብዙ እንግልት ከደረሰበት በኋላ አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ወደ ነበረው እስር ቤት ተዛወረ።

ከዚያም ከሌሎች የመኢሶን ጓዶች ጋር በእስር ከቆየ በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 1971 ዓ.ም. ከኃይሌ ፊዳ እና ከኃይሉ ገርባባ ጋር ከታሰረበት ከአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ተወስደ። በዚያኑ ቀን ወህኒ ቤት የነበሩት ባለቤቱ ዶክተር ንግሥት አዳነ እና ወ/ት ቆንጂት ከበደ ተጨምረው ሁሉም በአንድነት በድብቅ በግፍ ተገደሉ።

ደስታ ሕይወቱ የተቀጠፈው በ36 ዓመቱ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top