ኃይሌ ፊዳ

ኃይሌ ፊዳ፣ ከአባቱ ከአቶ ፊዳ ኩማ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ጉዲኒ ደጋ በወለጋ ክፍለ አገር በአርጆ ከተማ በ1932 ዓ.ም. ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደባት በአርጆ ከተማ እና በነቀምቴ ከተማ ተከታተለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ በሚገኘው የጄነራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት በነጻ የመማር ዕድል አግኝቶ ነው። አብረውት የነበሩ ተማሪዎች በጎበዝ ተማሪነቱ ያስታውሱታል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው በከፍተኛ ማዕረግ ነበር።

በ1952 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ አንድ ዓመት በሐረርጌ ክፍለ አገር በደደር ከተማ በመምህርነት ካገለገለ በኋላ፣ በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኋላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ  በመባል ይታወቅ በነበረው የትምህርት ተቋም ገብቶ በ1955 ዓ.ም. የባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪውን በጂኦሎጂ እና ፊዚክስ በከፍተኛ ማዕረግ ተቀበለ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ኃይሌ የፖለቲካና ማኅበራዊ ለውጥ ይጠይቅ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በንቃት ይሳተፍ ነበር። የቅርብ ጓደኞቹ እንደሚመሰክሩት በዚህን ወቅት ነበር በሶሻሊስት ርዕዮተዓለም እየተመሰጠ መሄድ የጀመረው። ከዩኒቨርሲቲው ሲመረቅ ባገኘው ከፍተኛ ውጤትም እዚያው ረዳት መምህር እንዲሆን ተመርጦ ማስተማር ቀጠለ።

በ1956 ዓ.ም. አንድ ዓመት በረዳት መምህርነት ካገለገለ በኋላ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ የጂኦሎጂ ትምህርቱን ፈረንሳይ፣ ፓሪስ ተከታትሏል። በተጨማሪም በእውቁ የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ተከታትሎ በሶስዮሎጂ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቋል። በፈርንሳይ በኤኮል ናሲዮናል ላንግ ኦርዬንታል ቪቫንት እንዲሁም ጀርመን በሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ አስተምሯል።

በፈረንሳይ አገር ቆይታውም ኃይሌ ፊዳ በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበርን በማደራጀት እና በማንቃት ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃል። ኃይሌ በኅብረተሰብ እድገት፣ ፍልስፍና፣ ቋንቋ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች እና በሌሎች በርካታና አብይ ርእሶች ላይ ጽሁፎችን በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ አበርክቷል።  ታጠቅ” እና ትግላችን” ይባሉ በነበሩት በአውሮጳ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር መጽሄቶች ላይ በተለያዩ የብዕር ስሞች በሚያቀርባቸው ጥልቅ ሃሳብ አዘልና ግልጽ መጣጥፎቹ፣ በስብሰባዎች ላይ በሚሰነዝራቸው ጠለቅ ያሉ ገንቢ ሃሳቦቹ ይታወቃል።

በነሐሴ ወር 1960 ዓ.ም. ምዕራብ ጀርመን፣ በሀምቡርግ ከተማ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ሲመሠረት ከመሥራች አባላቱና መሪዎች መሃል አንዱ ነበር። የመኢሶን ጠቅላይ ኮሚቴ የመጀመሪያው ዋና ጸሓፊ በመሆንም ተመርጦ በመሪነት አገልግሏል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮም የመኢሶን ልሳን የነበረው የሰፊው ሕዝብ ድምፅ‘ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል።

ኃይሌ፣ የቋንቋ ዝንባሌ እና ተሰጥኦም ነበረው። አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ፈርንሳይኛ እና ጀርመንኛን አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ከእነዚህም በተጨማሪ በእስር ቆይታው ቀደም ብሎ ጀምሮት የነበረውን የአረብኛ እና የትግርኛ እውቀቱን የላቀ ደረጃ አድርሶት ነበር። የሩስያን ቋንቋም በመማር ላይ ሳለ ነበር ሕይወቱ የተቀጠፈችው።

ኃይሌ ለአፋን ኦሮሞ መዳበር ፈደሉን ከመቅረጽ አንስቶ፣ የሰዋስው መጽሐፍ በማዘጋጀት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርጓል። ቋንቋውንም በፈረንሳይ አገር በቅርብ ምሥራቅ ቋንቋዎች ኢንስቲትዩት እና በጀርመን አገር በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል አስተዋውቋል። ከቋንቋ አስደናቂ ተሰጥኦው በተጨማሪም ሰዕል የመሳል እና የተለያዩ ሙዚቃዎችን አዳምጦ የማድነቅና የመረዳት ችሎታም ነበረው።

የየካቲት 1966 የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት መቀጣጠሉን ተከትሎ ኃይሌ የበኩሉን የትግል ድርሻ ለማበርከት በጥር 1967 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት ተመለሰ። እንደተመለሰም ጥቂት ቀደም ብሎ በመኢሶን የተቋቋመውን ተራማጅ የመጻሐፍት መደብር በአስተዳዳሪነት መርቷል። እንዲሁም፣ ‘ዲያሌክቲካዊና ታሪ ቁስአካነት’ በሚል ርእስ በ1968 ዓ.ም. ያሳተመውና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እጅግ የተጋጋለ ውይይት የቀሰቀሰው መፅሐፉ የማርክሲዝም ፍልስፍና ጽንሰ-ሃሳብ በሰፊው እንዲታወቅ አስተዋጻኦ አድርጓል።

መኢሶን በደርግ መንግሥት ላይ ሂሳዊ ድጋፍ የሚለውን አቋም መውሰዱን ተከትሎ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲመሠረት፣ ጽ/ቤቱን በሊቀ መንበርነት መርቷል። በጽ/ቤቱ አማካኝነት የወጣውን የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን በማርቀቅም ቁልፍ ሚና ነበረው። ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ እንዲወጣ ታስቦ የነበረውን፣ ነገር ግን ደርግ በሕግ ለማጽደቅ ፈቃደኛ ያለሆነበትን የዴሞክራሲያዊ መብቶች አዋጅ በማርቀቅ እና ረቂቁ ጸድቆ እንዲዋጣ ብዙ ታግሎ ነበር።

በተጨማሪም፣ ኃይሌ ብዙ ጥረት አድርጎበት የነበረው ጉዳይ በወቅቱ የብዙ ኢትዮጵያንን ሕይወት እየቀጠፈ እና ንብረት እያወደመ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኤርትራ ጦርነት ጉዳይ በድርድርና በሰላም የሚቋጭበትን መንገድ መሻት ነበር። ለዚህም ዓላማ፣ በደርግ መንግሥትና በኤርትራ አማጺያን ግንባሮች መካከል ውይይት እንዲጀመር፣ ኤርትራ ድረስ ከሰላም ልዑካን ጋር በመጓዝ ለሰላም ድርድርና እርቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

መኢሶን በደርግ መንግሥት ላይ የነበረውን ሂሳዊ ድጋፍ የሚለውን የፖለቲካ አቋሙን አንስቶ በነሐሴ 1969 ኅቡዕ ገባ። በዚህም ምክንያት፣ ኃይሌም ከጥቂት የመኢሶን ጓዶችና አመራር አባሎች ጋር ከከተማ ሳይርቅ የገጠሩና የከተማውን ትግል ለማቀነባበር የሚመችና አስተማማኝ ተብሎ የተገመተው የሙሎ ወረዳ ውስጥ ሆኖ እንዲታገል ተወሰነ። ሆኖም፣ በጳጉሜ 2 ቀን 1969 ዓ.ም. ኃይሌ በደርግ መንግሥት ወታደሮች እጅ ወደቀ።

በእስር ላይ እያለም፣ በደርግ ጽ/ቤት የምርመራ ክፍል ብዙ እንግልትና ድብደባ ተፈጸመበት። ከዚያም በ4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ወደነበረው የደርግ እስር ቤት አዛውረውት ለሁለት ዓመታት እስከ ሐምሌ 1971 ዓ.ም. ካቆዩት በኋላ፣ ከደስታ ታደሰ፣ ሃይሉ ገርባባ፣ ዶ/ር ንግሥት አዳነና ቆንጂት ከበደ ጋር በድብቅ በግፍ ተገደለ።

በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ ኃይሌ በጥልቅ እውቀቱ፣ በአስተዋይነቱ፣ በአድማጭነቱ፣ በእርጋታው፣ በትህትናው እና ለተበደለ ሁሉ በተቆርቋሪነቱ ያስታውሱታል።

ኃይሌ ፊዳ፣ ከትዳር አጋሩ ከበርናዴት ኃይሌ ፊዳ ሁለት ሴት ልጆችን አፍርቷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top