ፋሪስ ሂርጳ

ፋሪስ ሂርጳ፣ በ1939 ዓ.ም.  በጨለያ    ወረዳ ቶኬ ቀበሌ ተወለደ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጌዶ ከተማ ደጃዝማች ጫጫ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ። በመቀጠልም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአምቦ ከተማ ማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ተከታትሎ ተመረቀ።

በትምህርቱ እጅግ ውጤታማ እና በየተለያዩ ተግባራትና ዝግጅቶች ግንባር ቀደም ሚና ይጫወት የነበረ በመሆኑ ከእድሜ አቻዎቹ አልፎ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ ነበር። በመሆኑም፡ ክትምህርት ገበታው ተነስቶ ወደ ስራ አለም ያመራው በወቅቱ የለውጥ ጭላንጭል የሚያመላክተውን የመሬት ይዞታ ሚኒስቴርን በመቀላቀል ሆነ።

ከጊዜ በኋላም በእርሻ ሚኒስቴር የሆሮ ጉዱሩ አውራጃ ኃላፊ ሆኖ ተመደበ። በዚህ ወቅት የአርሶ አደሩን አብዮታዊ ትግል በህቡዕ ያደራጅና ይመራል ብሎ ያመነበትን መኢሶንን በአባልነት ተቀላቀለ።

በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ አንዳንድ አባላቱን ከሕጋዊ ወደ ህቡዕ ትግል ሲያሰማራ፣ ፋሪስ ሂርጳ ከሥራ ገበታው ላይ ተይዞ ነቀምቴ የሚገኘው እጅግ አስከፊ የሆነው ጃቶ እስር ቤት ታሰረ። ከዚያም መስከረም 2 ቀን፣ 1972 ዓ.ም ከሌሎች የመኢሶን ጓዶች፣ ከብሩ ወርቁና ከእምሩ ኢብሳ ጋር በአንድነት በግፍ ተረሸነ።

ፋሪስ ከልጅነቱ ጀምሮ ለጭቁኖች መብት የቆመ፣ ለአገር እድገት አሳቢና ተከራካሪ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top