መኮንን ጆቴ (ዶ/ር)
የዶክተር መኮንን ጆቴ የትውልድ ቦታ ስሬ፣ ወለጋ ሲሆን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሻምቡ ከተማ ካጠናቀቀ በኋላ በ1953 ዓ.ም. ጂማ የእርሻና የቴክኒክ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ።። ዶክተር መኮንን በአራት ዓመት የእርሻ ትምህርት ቤት ቆይታው በቅርብ የሚያውቁት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የሚያስታውሱት ረጋ ያለ፣ ቁም ነገረኛና በትምህርቱ ላይ የሚያተኩር እንደነበረ ነው።
በ1956 ዓ.ም. ከጂማ እርሻና ቴክኒክ ትምህርት ቤት በዲፕሎማ ከተመረቀ በኋላ መጀመሪያ በወቅቱ ቡና ቦርድ በመባል በሚታወቀው መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ መቀመጫውን በደሌ (ኢሉባቡር) በማድረግ የአውራጃው የቡና ልማት ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል። ከዚያም በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የተለያዩ ስፍራዎች ሲሠራ ቆይቶ በ1959 ዓ.ም. የነፃ ትምህርት እድል በማግኘቱ ወደ ሶቭየት ህብረት ሄደ። በሶቭየት ህብረት ቆይታው በተለይ የቋንቋ ትምህርቱን አጠናቆ ሞስኮ የእንስሳት ሕክምና አካዳሚ ከገባ በኋላ በተማሪዎች ማህበራት ተሳታፊ ነበር።
መጀመሪያ በሞስኮ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፐሬዜዳንት፣ ቀጥሎም በሶቭየት ህብረት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፐሬዜዳንት ሆኖ አገልግሏል። በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ጉባኤዎች ላይ በመገኘትም በሊቀ መንበርነት ጭምር መርቷል።
በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበራት በአገራቸው የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ መምጣት እንዳለበት ጽኑ አቋም ያዙ። በዚህ ጊዜ ነበር ዶ/ር መኮንንም በተማሪዎች ማህበራት ውስጥ በሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ የርዕዮተ-ዓለምና አጠቃላይ የፖለቲካ አስተሳሰብ ግንዛቤውን ያሳደገው። ከዚያም በመነሳት፣ ለለውጥ የሚደረገው ትግል ከተማሪዎች ማህበራት በላይ የተደራጀ አካል የሚጠይቅ መሆኑን ከተገነዘቡ ጥቂት ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ፈለገ ጥበብ” የሚባል የጥናት ቡድን መስርተው ለላቀ ትግል ራሳቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ።
ዶክተር መኮንን፣ የእንስሳት ሕክምና ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በሰለጠነበት ሙያ በግብርና ሚኒስቴር ወስጥ የኢሉባቡር ክፍለ አገር የአንስሳት ሐኪም ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ መኮንን በተለይ በጂማ ሕዝባዊ ኮሚቴ ውስጥ በኅቡዕ በመሳተፍ ትግሉ እንዲፋፋም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በቀጣይም በመኢሶን ሥር በመደራጀት የፖለቲካ ተሳትፎውን የበለጠ አጠናክሮ ታግሏል።
በ1969 ዓ.ም. የሸዋ ክፍለ አገር ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ አገሩን አገልግሏል። በዚሁ ሥራ ላይ እያለ፣ ኅዳር 2 ቀን፣ 1970 ዓ.ም. ወደ ሥራው ለመሄድ ከቤቱ ሲወጣ የደረሰበት ግድያ “በለየላቸው የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች” የተደረገ ተብሎ በመንግሥት ዜና ማሰራጫዎች ተለፈፈ። ሀቁ ግን የዶ/ር መኮንን ጆቴ ሕይወት ያለፈው በደርግ ነፍሰ ገዳዮች የጥይት ውርጅብኝ ነበር።