ሰንበታ ዋቅጅራ
ሰንበታ ዋቅጅራ በወለጋ ክፍለ አገር ተወለደ። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በኮተቤ የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ትምህርቱን ተከታተለ። ከዚያም እስከ ታሰረበት ቀን ድረስ በመቱ ገብረኤል ትምህርት ቤት በመምህርነት በማገልገል ላይ ነበር።
ሰንበታ ለተገፉና ለተበደሉ ወገኖቹ መብትና ጥቅም መከበር፣ እንዲሁም ለፖለቲካዊ ለውጡ ዘለቄታ ፅኑ ፍላጎት ነበረው። ስለሆነም፣ በግሉም ሆነ መኢሶን ውስጥ በነበረው ድርጅታዊ ኃላፊነት ወገኖቹን በማንቃትና በማደራጀት ሥራዎች ተሰማርቶ ነበር።
በነሐሴ 1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ ዶ/ር ከድር መሐመድና ሌሎች የመኢሶን መሪዎችና አባሎች ትግላቸውን በኅቡዕ ለማካሄድ ከከተማ ተሰወሩ። ከዚያ በኋላ በሥራ ላይ የነበሩ ሌሎች ጓዶች በታኅሣሥ ወር 1970 ዓ.ም. በደርግ ወታደሮች ተይዘው ታሰሩ። ሰንበታም፣ ከእነዚህ የመኢሶን ጓዶች ጋር አብረህ ትሠራ ነበር በሚል እስር ቤት ተወረወረ። እስር ላይም ከፍተኛ እንግልት ደረሰበት። በመጨረሻም አዲስ አበባ ትወሰዳላችሁ ተብለው መኪና ላይ ካሳፈሯቸው ጓዶች መሃል አንዱ ሆነ።
ይሁንና፣ ሰንበታና ጓዶቹ አዲስ አበባ አልደረሱም። ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ጊቤ በረኻ ሲደርሱ ሰንበታን፣ ከድር መሐመድን፣ ከበደ ቦረናንና ገመቹ ለሙን ከተሳፈሩበት መኪና አውርደው በደርግ መሪዎች ትእዛዝ ካለምንም ፍርድ በግፍ ረሸኗቸው።
ሰንበታ በሕዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና ለተጨቆኑ ወገኖቹ የሚቆረቆር ታጋይ ነበር።