ገመቹ ለሙ

ገመቹ ለሙ በወለጋ ክፍለ አገር ፣ በሆሮ ጉድሩ አውራጃ፣ ጊዳ ወረዳ፣ ለቡ በምትባል ቀበሌ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተወለደ። ትምህርቱን በጊሳ አያ፣ ለሙ እና ነቀምቴ ተከታተለ። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በ1966 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዮኒቨርስቲ ገባ። በ1966 አጋማሽ ዮኒቨርሲቲው ሲዘጋ በጊዜያዊ ሥራ ላይ ተሰማራ።

በ1967 ዓ.ም. የገጠር መሬት ዓዋጅ መውጣትን ተከትሎ ዓዋጁን በሥራ ላይ ለማዋል ከተመለመሉት ሰዎች መሃል አንዱ በመሆን በኢሉባቡር ክፍለ አገር የዳሩሙ ወረዳ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተመድቦ ሲያገለግል፣ ከገበሬዎች እና ከአለቆቹ በአገኘው አድናቆት በ1969 ዓ.ም. የመቱ አውራጃ የመሬት ይዞታ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ተጠሪ ሆኖ ተመደበ።

በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. በክፍለ አገሩ የነበሩ የመኢሶን መሪዎች ድርጅቱ የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ፣ ትግላቸውን ገጠር ውስጥ በኅቡዕ ማካሄድ ጀመሩ። በዚህን ወቅት ምንም እንኳን ገመቹ ለመስክ ሥራ ወደ ገጠር ወጥቶ የነበረ ቢሆንም ሲመለስ የመኢሶን ጠላቶች ከመኢሶን እና ከገበሬው ጋር የነበረውን ቅርበት በመመልከት ብቻ አስረውት በገበሬ መሪዎች ጥረት ተፈትቶ ወደ መደበኛ ሥራው ለመመለስ ቻለ።

ነገር ግን፡ በታኅሣሥ 1970 ዓ.ም እነ ዶ/ር ከድር መሐመድ ሲታሰሩ ገመቹ በድጋሚ ለእሥር ተዳረገ። ከእነ ዶ/ር ከድር መሐመደ ጋር በመቱ ፖሊስ ጣቢያ ብዙ እንግልት ደረሰበት። በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ትወሰዳላችሁ በሚል ከዶ/ር ከድር፣ ከበደ ቦረና እና ሰንበታ ዋቅጂራ ጋር መኪና ላይ እንዲሳፈሩ ተደረገ። ነገር ግን አዲስ አበባ ሳይደርሱ የደርግ ወታደሮች ጊቤ በረኻ ላይ አውርደው ያለምንም ፍርድ ረሸኗቸው።

ገመቹ ለሙ፣ በገበሬዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች እጅግ ይከበርና ይወደድ የነበረ ታጋይ ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top