ከበደ ቦረና
ከበደ ቦረና በወለጋ ክፍለ አገር በሆሮ ጉዱሩ አውራጃ በአቢ ደንጎሮ ወረዳ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በሻንቡ ከተማ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው አዲስ አበባ በሚገኘው በጄነራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናውን በከፍተኛ ማዕረግ በማለፍ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዮኒቨርሲቲ መከታተል ጀመረ። በ1966 የኢትዮጵያ አብዮት በተከሰተበት ወቅት የ2ኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ነበር።
በ1968 ዓ.ም. የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲመሠረት ኢሉባቡር ክፍለ አገር የድርጅቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። በነሐሴ ወር 1969 ዓ/ም መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ ከሌሎች የመኢሶን ጓዶች ጋር ትግሉን በኅቡዕ ለመቀጠል እዚያው ኢሉባቡር ገጠር ውስጥ ገባ።
ከበደ፣ በታኅሣሥ 1970 ዓ.ም. በደርግ ወታደሮች ተይዞ ከዶ/ር ከድር መሐመድና ከሌሎች ሁለት የመኢሶን ጓዶች ጋር በመቱ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ብዙ እንግልት ደረሰበት። ከዚያም አዲስ አበባ ትወሰዳላችሁ ብለው በመኪና ከጫኗቸው በኋላ፣ ጊቤ በረኻ ላይ ያለምንም ፍርድ ረሸነው ባልታወቀ ስፍራ ቀበሯቸው።
ከበደ ቦረና ብሩህ አዕምሮ የነበረው ቆራጥ ታጋይ ነበር።