ተረፈ ወልደ ጻድቅ (ዶ/ር)

ዶ/ር ተረፈ ወልደ ጻድቅ፣ ጥቅምት 18 ቀን፣ 1930 ዓ.ም. ወሊሶ ከተማ ተወለደ። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያው ወሊሶ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ አዲስ አበባ ሄዶ አምሃ ደስታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማረ። የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናውን በጥሩ ውጤት በማለፉ ኮተቤ፣ በቀድሞ አጠራሩ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ። እዚያም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዲሁ በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ    ከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በቀድሞ አጠራሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ) ተከታትሎ የባችለር ኦፍ አርትስ  ዲግሪውን በ1956 ዓ.ም. አገኘ።

ዶ/ር ተረፈ፣ ኮሌጅ እያለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚደንት ሆኖ አገልግሏል። በወቅቱ፣ በ1956 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብሎ የነበረውን ታዋቂውን የጥቁር አሜሪካኖች መብት ተሟጋች ማልኮልም ኤክስን ጋበዞ ስለ ጥቁር አሜሪካኖች የመብት ትግል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ንግግር እንዲያደርግ አድርጓል።

በ1956 ዓም መጨረሻ፣ ዲግሪውን እንዳገኘ ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ኔዘርላንድስ በመሄድ ደን ሀግ ከተማ ከነበረው ኢንተርናሸናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሶሻል ስተዲስ (International Institute of Social Studies) ማስተር ኦፍ ሶሻል ሳይንስ (MSSc) ዲግሪውን ተቀበለ። በመጨረሻም፣ በኢንስቲተዩቱ ውስጥ በመምህርነት በሚያገለግልበት ወቅት የዶክትሬት ዲግሪውን አገኘ።

ተረፈ፣ ከመኢሶን መሥራች አባሎች አንዱ እና የጠቅላይ ኮሚቴውም አባል ነበር። በአብዮቱ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ በ1968 ዓ.ም፣ የየካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ቤት ሲቋቋም፣ የት/ቤቱ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል።

በነሐሴ ወር 1969 ዓም መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ባደረገበት ወቅት፣ ተረፈ እና የትዳር ጓደኛው አጥናፍ፣ ጋሹ ተረፈ እና አቡሽ (ተካልኝ) ተረፈ የተባሉ ሁለት ህጻን ልጆቻቸውን ለአንድ ዘመድ እና ለአንድ ሌላ የቅርብ ጓደኛ አደራ ሰጥተው ወደ ኅቡዕ ትግል ተሠማሩ። በወቅቱ ተረፈ የትምህርት ሚኒስትር ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር።

ምዕራብ ሸዋ፣ ግንጪ አጠገብ ደንዲ ወረዳ በሕቡዕ ይኖሩበት የነበረውን ቤት የሚያውቁና በአገናኝነት ይሠሩ የነበሩ ሁለት የጅባትና ሜጫ አውራጃው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ባልደረቦች በፈጸሙት ክሕደት በድብቅ የሚኖሩበት ቦታ ምስጢሩ ደርግ እጅ ገባ። ከዚያም፣ ከደርግ ጽ/ቤት የመጣ ልዩ ኃይል፣ በነዚህ ሁለት ከሃዲዎች እየተመራ ተረፈ፣ አጥናፍና ሌሎች አብረዋቸው የነበሩ ስምንት ጓዶች ያሉበትን ቤት በሌሊት ከብቦ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ አሥሩንም ያለ ምንም ፍርድ በጭካኔ ረሸኗቸው።

ዶክተር ተረፈ ትሁት፣ ረጋ ያለ፣ ትእግስተኛ፣ ሰውን የማዳመጥና የማስተማር ችሎታ የነበረው አብዮተኛ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top