አጥናፍ-ዓለም ይማም

አጥናፍ-ዓለም ይማም፣ ኅዳር 18 ቀን 1938 ዓ.ም. በወሎ ክፍለ አገር ደሴ ከተማ ተወለደች። አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ደሴ፣ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ካጠናቀቀች በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመቀጠል በ1951 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው አቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት ገባች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች በ1955 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በ1959 ዓ.ም. ከዩኒቨርሲቲው ሶሻል ወርክ ትምህርት ቤት በዲፕሎማ ተመረቀች። ከባለቤትዋ ከዶክተር ተረፈ ወልደጻድቅ ጋር የተገናኙትም በዚሁ በኮሌጅ ተማሪነትዋ ወቅት ነበር።

ዶክተር ተረፈ፣ ከኔዘርላንድስ መንግሥት ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በማግኘቱ፣ ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ፣ በነሐሴ ወር 1960 ዓ.ም. ከባለቤትዋ ጋር አብራ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኔዘርላንደስ ሄደች። እዚያም ከፍተኛ ትምህርቷን ተከታትላ መጀመሪያ በ1965 ዓ.ም. በከተማ ማኅበራዊ እድገት፣ ከዚያ ቀጥሎ በ1966 ዓ.ም. በሶሻል ሳይንስ ማስተርስ ዲግሪዋን ደን ሀግ ከሚገኘው ከኢንተርናሸናል ሶሻል ስተዲስ ኢንስቲትዩት አገኘች።

አጥናፍ የሁለት ልጆች እናት ነበረች። የመጀመሪያ ልጃቸው፣ ጋሹ ተረፈ ወልደጻድቅ የተወለደው ነሐሴ 4 ቀን 1962 ዓ.ም. ደን ሀግ ከተማ፣ ኔዘርላንድስ እያሉ ሲሆን፣ አሁን በሕይወት የሌለው ሁለተኛው ልጃቸው፣ ተካልኝ ተረፈ ወልደጻድቅ የተወለደው በአብዮቱ ወቅት ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የካቲት 21 ቀን 1969 ዓ.ም. ነበር።

አጥናፍና ባለቤቷ ተረፈ፣ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ ከደርግ ጋር የነበረውን የሂሳዊ ድጋፍ ፖለቲካዊ ግኝኙነት ባቋረጠበት ወቅት ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን ትግላቸውን በኅቡዕ ለመቀጠል፣ ነሐሴ 13 ቀን 1969 ዓ.ም. በጅባትና ሜጫ አውራጃ በተሰማሩበት ወቅት ተካልኝ ገና የአምስት ወር ሕጻን ነበር።

በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንዲ ወረዳ ተሸሽገው እያሉ ሁለት ውስጥ አዋቂ የድርጅት አባሎች በፈጸሙት ክሕደት አጥናፍ፣ ባለቤትዋ ተረፈና ሌሎች ስምንት ጓዶች ሊያዙና በታህሣሥ ወር 1970 ዓ.ም. ያለ ምንም ፍርድ በግፍና በጭካኔ በአንድነት ከተያዙበት አካባቢ ሊገደሉ በቁ።

አጥናፍ ከሰው ጋር በቀላሉ የመግባባት ችሎታ የነበራት፣ ዓይን አፋር፣ ፈገግታ የማይለያት፣ ትሁት ሰው ነበረች።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top