ከበደ ዲሪባ

ከበደ ዲሪባ አወቀ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ አበበች ደበሌና ከአባቱ አቶ ዲሪባ አወቀ በ1937 ዓ.ም.  በመናገሻ አውራጃ በሆለታ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሆለታ ደጃዝማች መንገሻ ይልማ ት/ቤት ተማረ።  ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በከፊል አምቦ ከተማረ በኋላ የተቀረውን ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተምሮ በዲፕሎማ ተመረቀ።

 

ከዚያም በወለጋ ክፍለ አገር፣ ግምቢ አውራጃ፣ መንዲ ወረዳ በመምህርነት ተመድቦ ለሁለት ዓመት አገልግሏል። በመምህርነት ሥራ ላይ እያለ የኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወስዶ በጥሩ ውጤት አለፈ። በ1958 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአገኘ በኋላ ለሦስት ዓመታት በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ተቀጥሮ አገለገለ። ከዚያም የብሪቲሽ ካውንስል ስኮላርሽፕ አግኝቶ በ1966 ዓ.ም. ታዋቂው ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በመግባት በከተማ ኘላኒንግ የማስተርስ ዲግሪውን አገኘ።

 

ትምሕርቱን አጠናቆ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ በ1968 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ቀድሞ ይሠራበት በነበረው የመሬት ይዞታ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት እስከ የካቲት 1968 ዓ.ም. አገለገለ። ከዚያም በመቀጠል ከመጋቢት 1968 ዓ.ም. ጀምሮ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ እስከ አደረገበት ነሐሴ 13 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. ድረስ የሸዋ ክፍለ አገር የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊ በመሆን ሰርቷል።

 

መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ፣ ከእነዶ/ር ተረፈና ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን ጅባትና ሜጫ አውራጃ ኅብዕ ገባ። ብዙም ሳይቆይ፣ በውስጥ ከሃዲዎች ጥቆማ፣ ከበደና አብረውት የነበሩ ጓዶቹ በደርግ ወታደሮች ተይዘው ያለምንም ፍርድ ተረሸኑ።

 

ከበደ ዲሪባ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የ33 አመት ጎልማሳ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top