ኢዮብ ታደሰ

ኢዮብ ታደሰ በሸዋ ክፍለአገር በጊምቢቹ ወረዳ ልዩ ስሙ አርዳጋ በተባለ ቀበሌ ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቢሾፍቱ ዓፄ ልብነድንግል ተብሎ ይታወቅ በነበረው ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። በመቀጠልም ከጅማ የእርሻ ኢንስቲትዩት በሰርቲፊኬት ተመረቀ። በተጓዳኝም የሁለተኛ ደረጃ መለቀቂያ ፈተናውን ወስዶ በአጥጋቢ ውጤት በማለፉ ወደ ዓለማያ እርሻ ኮሌጅ አቀና። በእርሻ ኮሌጅ የሠሁለት ዓመት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሶስተኛ ዓመት ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ለጥቂት ጊዜ ከተከታተለ በኋላ የትምህርት ትኩረቱን ቀይሮ ወደ ሕግ ፋኩልቲ በመግባት በ1962 ዓ.ም. በሕግ የባችለር ኦፍ ሎውስ ዲግሪ ተመረቀ። ከሕግ ፋኩልቲ ከተመረቀ በኋላም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሕግ አማካሪነት ማገልገል ጀመረ።

በ1966 መጀመሪይ ላይ ነጻ የትምህርት እድል አግኘቶ በሕግ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል እንግሊዝ አገር ወደሚገኘው እውቁ የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ አቀና። እዚያም የማስተር ኦፍ ሎውስ ዲግሪውን አግኝቶ የዶክትሬት ደረጃ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ፣ በድርጅቱ በመኢሶን ጥሪ ትምህርቱን ለጊዜው በማቋረጥ፣ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በመመለስ የሕግ መምሪያ ሃላፊ በመሆን ማገልገል ጀመረ።

በነሐሴ 1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ ኢዮብም ከሌሎች ጓዶች ጋር ጅባትና ሜጫ አውራጃ ተመደበ። ታኅሣሥ 1970 ዓ.ም. የጅባትና ሜጫ አውራጃ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ካድሬ በነበሩ ሁለት ግለሰቦች ክሕደት ኢዮብና ጓዶቹ የተጠለሉበት ቤት በደርግ ልዩ ገዳይ ቡድን ተከበበ።  ከከበባቸው ልዩ ኃይል ጋር ለመግጠም የሚያስችል ኃይል እንደሌላቸው ሲያውቁ እጃቸውን በሰላም ሰጡ። የያዛቸው ጦር ከአዲስ አበባ የመጣባቸውን ተሽከርካሪዎች ወዳቆመበት በሚወስደው መንገድ በእግር ጥቂት እንደተጓዙ ኢዮብንና ዘጠኙን ጓዶች አንድ ገደል አፋፍ ላይ አቁመው ረሸኗቸው።

አገሬን አገለግላለሁ ብሎ ትምህርቱን አቋርጦ የመጣው የኢዮብ ታደሰም ሕይወት በአጭር ተቀጨ።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top