ደምሴ ዓለሙ
ደምሴ ዓለሙ ያደገውና ትምህርት የጀመረው ክብረ መንግሥት (አዶላ) ከተማ ነው። አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በቀድሞው ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ት/ቤት ነበር። ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ት/ቤት በ1945 ዓም ለመጀመሪያ ጊዜ ለ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ካስቀመጣቸው 7 ተማሪዎች አንዱ ደምሴ ዓለሙ ነበር። ስምንተኛ ክፍልን ሲጨርስ በትምህርት ሚኒስቴር ወደ ተደለደለበት ቀበና የሚገኘው ኮኮበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመላላሽ ት/ቤት ገብቶ የአንድ ዓመት የመምህርነት ኮርስ ተከታተሎ ተመረቀ።
ከዚያም፣ ሲዳሞ ክፍለ አገር አለታ ወንዶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ተመደበ። ለሁለት ዓመት በአማርኛ መምህርነት ካገለገለ በኋላ ወደ ክብረ መንግሥት ተዛውሮ ማስተማሩን ቀጠለ። ከዚያም በኋላ ወደ አዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ተዛውሮ ከየክፍለ አገሩ 8ኛ ክፍል ፈተና የጨረሱትንና አዲስ አበባ የተደለደሉትን ተማሪዎች በውጤታቸው መሠረት በየሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚመድበው አስተባባሪ ቡድን ምክትል ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል።
በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ወቅት በሚኖርበት የቀበሌ ማኅበር በሕዝብ ተመርጦ በከፍተኛ 3 የቀበሌ 44 አመራር አባል ሆኖ ያገለግል ነበር። በሕዝባዊ ማኅበር አገልግሎቱ ላይ በነበረበት ወቅት በመጋቢት ወር፣ 1969 ዓም፣ ቤቱ አጠገብ አድፍጦ ይጠብቅ በነበረ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳይ በጥይት ተገደለ።
ደምሴ ዓለሙ፣ በተማሪነት ዘመኑ፣ እግር ኳስ እና መረብ ኳስ ጨዋታ ያዘወትር ነበር። ጭምትና በሥራው ትጉህ፣ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበር።