ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ

ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ፣ ትግራይ ውስጥ አዲግራት ተወለደ። ወላጆቹ ገብረ እግዚአብሔርን ለማሳደግ አቅሙ ስላልነበራቸው፣ በሕጻንነቱ ባለጸጋ ለነበሩ ቤተሰቦች ኀላፊነት ተሰጠ። በአሳዳጊዎቹም ተከታታይነት በልጅነቱ፣ በካዛንቺስ በጎ አድራጎት የሕጻናት ማሳደጊያ አደገ። እስከ ስምንተኛ ክፍል ካዛንቺስ አስፋ ወሰን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱንም በ1966 ዓ.ም. አስፋ ወሰን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ አጠናቀቀ።

በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የገብረ እግዚአብሔር (ገብሬ) ፖለቲካዊ ተሳትፎው እጅግ ምስጢራዊ ነበር። በየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ፣ ገብረ እግዚአብሔር በተማሪው ንቅናቄ ውስጥ ግንባር ቀደም የነበሩ ተማሪዎችን በቅርብ እያገኘ ይወያይ ነበር። በውይይቱ ላይም ከተማሪ ንቅናቄ ያለፈ ጠንካራ ድርጅት እንደሚያስፈልግና ለዚህም የኢትዮጵያ ተራማጆች ህብረት አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ከመወትወት ችላ ብሎ አያውቅም። መኢሶን ገና ማንነቱን በይፋ ባልገለጸበት ወቅት፣ በኋላ ላይ መኢሶን ውስጥ በንቃት የተሳተፉና ለድርጅቱ ዓላማ የተሰዉ ብዙ ጓዶችን በኅቡዕ ድርጅታዊ ሕዋሳት በማደራጀት ስለ አገራቸውና ስለ ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጭቆናና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ እንዲያጠኑ ያደርግ የነበረ ጠንካራ ታጋይ ነበር። 

በ1967 ዓ.ም. በእድገት በህብረት ዘመቻም፣ በመጀመሪያ ትግራይ ክፍለ አገር ውስጥ ተምቤን አውራጃ ወርቂ እምባ ወረዳ ዘምቷል። እዚያም ሳለ የዘማቾች ምክር ቤት (ካውንስል) ሊቀ መንበር ሆኖ በዘማቾች ተመርጧል። ወርቂ እምባ በነበረበት ወቅት በተማሪዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅና የተከበረ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ሕዝቡን ልታሳድሙ ሞክራችኋል በሚል እርሱና ሌሎች 12 ዘማቾች በመንግሥት ተይዘው መጀመሪያ መቀሌ ከዚያም አዲስ አበባ ታሰሩ። ከእስር በኋላም በቦረና አውራጃ ሀረ ቀሎ የምትባል አነስተኛ ከተማ ተመድቦ ለአጭር ጊዜ አገልግሏል። ዘመቻውን አቋርጦ ከተመለሰም በኋላ፣ የመኢሶን ሙሉ ጊዜ (ፕሮፌሽናል) አብዮተኛ ሆኖ እስከኅልፈቱ ድረስ በጽናት ይሠራ ነበር።

ገብሬ፣ በአስተሳሰቡ እጅግ ብልህና በፖለቲካ እውቀቱም ብስል ነበር። የማስተማር፣ የማወያየትና ማደራጀት ችሎታው እጅግ ድንቅ ነበር። ገብሬ የመኢሶን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አባልና የወጣት ክንፉም የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ንቅናቄ (ኢአወን) መሥራችና ዋና ጸሐፊም ነበር።

ገብሬ ስህተት ሲፈጸም አይቶ አያልፍም። ትልቅ ትንሽ ሳይል ሃሳቡን ጥርት ባለ መልክ ያቀርባል። የማይስማባበትን ካለ አንዳች ይሉኝታ ይናገራል። ጓዶቹ ሲሳሳቱ ይገስጻል። ገብረ እግዚአብሔር፣ ቁም ነገረኛ ብቻ ሳይሆን ተጨዋችና እጅግ ከሰው ጋር ተግባቢ ነበር። የፒያሳ መኖሪያ ሠፈሩ ሕጻናት እጅግ ይወዱታል። 

ገብሬ፣ ለተበደሉ ይቆረቆራል። ሠርቶ አደር ወገኑን ይወዳል። በሀገራችን ሉዓላዊነትና በሕዝባችን የራስ መተማመን ጉዳይ ላይም የጸና አቋም ነበረው። ገብሬ፣ ጥቅምት 2 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. የመኢሶን “አባል” ነው ተብሎ ከሚታወቅ፣ የኢሕአፓ ሰርጎ ገብ ጋር ለመወያየት ተቀጣጥሮ አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኝ ካሳ ቡና ቤት ውስጥ ይጠብቅ ነበር። ነገር ግን፣ በቀጠሮው ሰዓት ገብሬ የሚጠብቀው ሰው አልመጣም። በምትኩ፣ አንድ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳይ ቀጠሮ ቦታው ደርሶ ገብሬን በተደጋጋሚ በጥይት መትቶ ገደለው።

ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ ሕይወቱ ሲያልፍ የ21 ዓመት ወጣት ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top