ፀጋዬ ደባልቄ
ጸጋዬ ደባልቄ፣ በ1927 ዓ.ም. ሸዋ ክፍለ አገር ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሙ ንብጌ ማርያም ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አስፋ ወሰን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቋል። ከዚያም በምህንድስና ኮሌጅ ትምህርቱን ተከታትሏል።
ጸጋዬ እጅግ የተደነቀ የሙዚቃ አቀናባሪ ከመሆን አልፎ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ፣ በተለያዩ የብሔረሰቦች ውዝዋዜና ባህላዊ ጨዋታዎች ላይ የምርምር ጽሁፎችን አቅርቧል።
የባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ሆኖ ከማገልገሉ በፊት በማስታወቂያና መርሃ-ብሔር ሚኒስቴር፣ ከዚያም ቀደም ብሎ በትምህርት ሚኒስቴር በመምህርነትና በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገሩን ያገለገለ አብዮታዊ ነበር።
የመኢሶንን የፖለቲካ አቋም በመደገፉና በማራመዱ ብቻ በጠላትነት ታይቶ፣ በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች በተተኮሰበት ጥይት በተወለደ በ42 ዓመቱ የተገደለው ፀጋዬ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበር።