መርዕድ ከበደ

መርዕድ ከበደ በ1941 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኮተቤ አጠናቀቀ።  የፖለቲካ ሕይወቱን የጀመረውም ኮተቤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነበር።

መርዕድ፣ በ1964 ዓ.ም. ከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ጀርመን፣ በርሊን ከተማ አቀና። ጀርመን በነበረበትም ጊዜ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበር። ከጀርመን የሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ አሜሪካ፣ ዋሺንግተን ዲ.ሲ. መኖር ጀመረ።

በ1966 ዓ.ም. አብዮቱ ሲቀጣጠል አሜሪካ የነበሩ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ኤምባሲ በመያዝ ተቃውሞ ሲያሰሙና ለፖለቲካዊ ለውጥ ጥሪ ሲያደርጉ፣ መርዕድ ከንቅናቄው መሪዎች አንዱ ነበር። በተጨማሪም፣ የተማሪዎቹ ቃል አቀባይ በመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይና መከራ ለዓለም የመገናኛ አውታሮች ያሰማ ነበር።

ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት በኋላ፣ መርዕድ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ የመኢሶን መሪዎች አዲስ አበባ አራት ኪሎ በከፈቱት ተራማጅ መጽሐፍት መደብር ሠርቷል።  በመኢሶን ወጣት ክንፍ ውስጥም ተሳትፏል።

በነሐሴ 1969 ዓ.ም. መኢሶን ትግሉን በኅቡዕ ለመቀጠል ውሳኔ ሲያደርግ፣ መርዕድም ከነዶ/ር ተረፈ ወልደ ጻዲቅ ጋር ወደ ገጠር እንዲሰማራ ተመደበ። ከዚያም እሱና ሌሎች ጓዶች፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ግንጪ አጠገብ በደንዲ ወረዳ በኅቡዕ ይኖሩበት የነበረውን ቤት የሚያውቁና በአገናኝነት ይሠሩ የነበሩ ሁለት የጅባትና ሜጫ አውራጃው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ባልደረቦች በፈጸሙት ክሕደት ምክንያት የመኖሪያቸው ቦታ ምስጢር ደርግ እጅ ገባ።

ከዚያም፣ በነዚህ ሁለት ከሃዲዎች በቀጥታ እየተመሩ የመጡት የደርግ ልዩ ኃይል ወታደሮች፣ መርዕድና ሌሎቹም ጓዶች የነበሩበት ቤት ሲከበብ እጃቸውን ለመስጠት ተገደዱ። ነገር ግን፣ የደርግ ልዩ ኃይል ወታደሮች እጃቸውን በሰላም የሰጡትን መርዕድንና ሌሎች ዘጠኝ ጓዶቹን እዚያው በተያዙበት አካባቢ ረሸኗቸው።

መርዕድ በዚህ አኳኋን በግፍና በጭካኔ ያላንዳች ፍርድ በተገደለበት ወቀት የ28 ዓመት ወጣት ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top