ከድር መሐመድ (ዶ/ር)

ዶ/ር ከድር መሐመድ፣ ኢሉባቡር ጎሬ አውራጃ፣ በአሌ ወረዳ፣ ቀድሞው ቆንሲል ሜዳ በሚባለው አሁን ኩንዲና ጋጊ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ከልክሌ በሚባለው የገጠር መንደር ውስጥ ከእናቱ ከወ/ሮ አሊማ ድልቦና ከአባቱ አቶ መሐመድ አብደላ (በአካባቢው ሕዝብ አባ ጎሮ መሐመድ አብደላ ተብለው የሚታወቁ) በ1930 ዓ.ም. ተወለደ። ከድር ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ነበር።

በ1936 ዓ.ም. በቀድሞው ጎሬ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ገብቶ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል። ከዚያም አዲስ አበባ በሚገኘው ተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት ገብቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አርትስ ፋኩልቲ ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ገባ። የኮሌጅ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በጊዜው በማዕረግ ለተመረቁ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረውን የወርቅ ቅብ ሰዓት ተሸልሟል። በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ1955 ዓ.ም. ከተቀበለ በኋላ አዚያው ኮሌጅ ውስጥ በረዳት መምህርነት ለአንድ ዓመት አገልግሎ ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ኔዘርላንደስ በመሄድ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት (PhD) ዲግሪውን ተቀበለ።

የመኢሶን መሥራች አባል የሆነው ከድር፣ የሱዳን ድንበር አዋሳኝ በሆኑት በኢሊባቦር እና በወለጋ በኩል አቋርጦ አገር ውስጥ በመግባት፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ በድብቅ የመኢሶንን ድርጅታዊ እንቅስቃሴ በገጠር ለመትከል የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በ1962 ዓ.ም. ካርቱም ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጠረ። በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት መጀመሪያ ላይ በኢሉባቡር ክፍለ አገር የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ተጠሪ ከዚያም የክፍለ አገሩ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኖ የገጠር መሬት አዋጁን በማስፈጸምና ገበሬዎችን በማደራጀት ሠራ።

በመጨረሻም፣ በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ በማድረግ ከደርግ ጋር የነበረውን ፖለቲካዊ ግንኙነት ሲያቋርጥ እዚያው ክፍለ አገሩ ውስጥ በኅቡዕ ትግል ተሰማርቶ እያለ በ1970 ዓ.ም. ታኅሣሥ ወር በደርግ ወታደሮች እጅ ወደቀ። ከዚያም እሱንና አብረውት የተያዙትን ጓዶች፣ ከጂማ ወደ አዲስ አበባ የሚወስዷቸው አስመስለው በአዲስ አበባ አቅጣጫ መንገድ ከጀመሩ በኋላ በደርግ መሪዎች ትእዛዝ ጊቤ በረኻ ወስጥ ከመኪና አውርደው ረሸኗቸው።

ዶክተር ከድር መሐመድ፣ ዝምተኛ እና ሲናገርም ሐሳቡን ባጭሩ መግለጥ የሚያዘወትር፣ ርህሩህ፣ ረጋ ያለና በራሱ የሚተማመን ታጋይ ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top