ግዛው ጅማ
ግዛው ጅማ በአዲስ አበባ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው በአዲስ አበባ ከተማ ነበር። ከዚያም፣ መርካቶ በሚገኘው ቀድሞ፣ ልዑል መኮንን ይባል በነበረው ት/ቤት በአስተማሪነት አገልግሏል።
በ1960 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት እድል ፍለጋ፣ በቱሪስት ቪዛ ወደ ስዊድን አገር ሄደ። ዓላማው ግን የመኖሪያ ፈቃድ ጠይቆ ከፍተኛ ትምህርት ለማግኘት በማቀድ ነበር። እዚያ ከደረሰ በኋላም የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀ። ጥሩ ምክርና መልካም አቀራረብ ረድቶት የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄው በአጭር ጊዜ ተቀባይነት አስገኘለት። ለአንድ ወር ተኩል ያህል በስቶኮሆልም ከተማ ከቆየ በኋላ ወደ ኡፕሳላ ከተማ ተዛውሮ በኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጀመረ። በኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ ሲከታተል የነበረውን የፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ፣ የሁለተኛ ዲግሪ ከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ስቶኮልም ዩኒቨርሲቲ ገባ።
ግዛው ጅማ፣ ትምህርቱን በተከታተለበት ዘመን ሁሉ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ከፍተኛና ንቁ ተሳትፎ ነበረው። ከዚያም የመኢሶን አባል ሆነ። በየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ለአብዮቱ አስተዋጽኦ ለማበርከት ከአውሮጳ ወደ አገራቸው ሳያቅማሙ ቆርጠው ከተመለስሱት በርካታ ወጣት ምሁራን አንዱ ነበር። አዲስ አበባም እንደተመለሰ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥራት ጀመረ።
መኢሶን፣ ነሐሴ አጋማሽ 1969 ዓ.ም. ኅቡዕ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ በመላው የድርጅቱ አባሎች ላይ በደርግ በቀጠለው ግድያ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 1970 ዓ.ም. ግዛው ጂማ፣ የመኢሶን አባል በነበረው በተስፋየ ታደሰ መኪና ከአምስት ኪሎ ቁልቁል አብረው ሲጓዙ ደርግ ደህንነት ቢሮ ያሰማራው ስውር ገዳይ ቡድን እየተከታተለ የጥይት እሩምታ አወረደባቸው። ለጊዜው ተስፋዬ ታደሰ ሲተርፍ፣ ግዛው ጅማ ግን በዕለቱ፣ ታኅሣሥ 24፣ 1970 ዓ.ም. ሕይወቱ አለፈች።