እሸቱ አራርሶ

እሸቱ አራርሶ፣ የተወለደው በቀድሞ አጠራር ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ ጌዴኦ አውራጃ፣ ሲዳማና ጌዴኦ አውራጃዎች አዋሳኝ ድንበር ላይ በሚገኝ ቀበሌ ውስጥ ነበር። አንደኛ፣ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አለታ ወንዶ ካጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በቀድሞው ራስ ደስታ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ይርጋዓለም ከተማ ነው። 

ከዝያም አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሕግ ት/ቤት ገብቶ ከፍተኛ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በነበረበት ወቅት በተማሪዎች ፖለቲካዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በነበረው ግንባር ቀደም የአመራር ሚና ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት ከታገዱት ተማሪዎች መሀል አንዱ ነበር። የዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረበትም ወቅት በ1960 እና በ1961 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር ዋና ጸሓፊ ሆኖ አገልግሏል።  ከትምህርት ታግዶ በቆየበት ወቅት አዲስ አበባ አፍንጮ በር ስዊድሽ ት/ቤት ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቶአል። 

ከአብዮቱ በኋላ በ1967 ዓ.ም. የወጣውን የገጠር መሬት አዋጅ በማስፈጸም በተለያዩ ክፍለ አገሮች እየተዘዋወረ ሠርቷል። ከዚያም በ1968 ዓ.ም. የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲቋቋም የሲዳሞ ክፍለ አገር የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል። በዝያን ወቅት አዋሳ ከተማ፣ ዋርካ በተባለ ሆቴል እራቱን በመብላት ላይ እያለ በአደፈጡ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች በተተኮሰ ሦስት ጥይት ተመቶ፣  አዲስ አበባ በሚገኘው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዶክተሮች ከፍተኛ ርብርብ  በወቅቱ ሕይወቱ ሊተርፍ ችሎ ነበር።

እሸቱ፣ መኢሶን በ1969 ዓ.ም. በነሐሴ ወር የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ በደቡብ ኢትዮጵያ ኅቡዕ የገባው ቡድን የአመራር አባል ሆኖ አገልግሏል። በዚያን ወቅት በጌዴኦ፣ በሲዳማና በአሬሮ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ሲታገል ቆይቶ ሶማልያ ሲገባ፣ በሶማልያ መንግሥት ታስሮና በአካል ተሰቃይቶ በእስር ላይ እያለ ሕይወቱ አልፏል።

እሸቱ፣ ሲዳምኛ፣ ጌዴኦኛ፣ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል። እሸቱ አራርሶ መንፈሰ ጠንካራ ታጋይ፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top