የሕዝብ ፡ ድምፅ
የኢትዮጵያ ሰፊው ሕዝብ ችግር ዛሬ፣ ትናንት ወይንም የወረዱት ሚኒስቴሮች ሲሾሙ የመጣ አይደለም። የኢትዮጵያ ተራ ሕዝብ ችግር የሰነበተ፣ መሠረቱም የሰፋና የጠለቀ ነው። ብዙ ሕዝብ ደካሚ፣ ጥቂቶች ተጠቃሚ ከሆኑ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። ብዙ ሕዝብ በረሃብ በጠኔ ሲንፈራገጥ ጥቂቶች በጥጋብ ቁንጣን ይቸገራሉ። ሰፊው ሕዝብ ከሌሊቱ ቁር ከቀኑ ሐሩር የሚጠለልበት የጭራሮ ጎጆ ሲነፈግ ጥቂቶች ከእልፍኝ እልፍኝ ያማርጣሉ። ደሀው ሕዝብ ሀፍረተ ስጋውን የሚሸፍንበት ብጣቂ ሸማ አጥቶ ጥቂቶች የሚጋልቡበትን ፈረስ፣ የሚጥሉትን ሰንጋ ሀር ይለብሳሉ። ሕዝቡ የዘላለማዊ ደዌ ቁራኛ ሆኖ ሲሰቃይ ጥቂቶች ምግብ አልበላ እያለ ያማቸዋል። እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለብዙዎቻችን ገሃነም ለጥቂቶች ደግሞ ገነት ናት። የረሀቡ፣ የውርጩ፣ የበሽታው፣ የጭቆናው ሸክም በርትቶበት ዛሬ አሻፈረኝ ስላለ ችግሩ ዛሬ ተፈጠረ ማለት አይደለም።
ይህን የችግር ተራራ አላይህ ብለው አይንን ስለጨፈኑ አይወገድም። ወይንም ስለተፆመና እና ስለተፀለየ አይገፋም። አሥራ ስምንት ሚኒስቴሮች በሌሎች ጓዶቻቸው መተካታቸው አያጠፋውም። እርግጥ መልካም አስተዳደር የችግሩን ተራራ ለመናድ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ነው። ነገር ግን መሠረቱ ለተናጋ ቤት ጉልላት ቢለዉጡለት አይስተካከልምና የችግሩ ዋና መፍትሄ የመሠረት ለውጥ ብቻ ነው። ችግር አለ ብሎ መለፈፉ ብቻ አይበቃም። ምንጩን ፈልጎ መድፈን ያስፈልጋል።
የብሶታችን፣ የጭንቀታችን፣ የውርደታችን መነሻዎች በጭሰኛ ጉልበት የሚተዳደሩ መልከኞች፣ በወዝአደሩ ጫንቃ ላይ የተቀመጡት ታላላቅ ከበርቴዎች ጉዳይ አስፈጻሚዎቻቸው የቢሮ ባለስልጣኖች፣ የነዚህም ጭቆና እንዲሰነብት የሚረዱትና በበኩላቸው በሰፊው የሚበዘብዙት የውጭ ሀገር መንግሥታት፣ ይኸውም ኢምፔሪያሊስቶች ናቸው። በአራቱ ጠላቶቻችን ላይ በጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለብን። ያለበለዚያ ግን ይዋል ይደር እንጂ አሰቃቂ የደም መፋሰስ ይፈጥሩብናል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነፃነትና አንድነትን ይመርጣሉ። የኢትዮጵያ ሰፊው ሕዝብ ሰላምንና ግስጋሴን ይሻል። ስለሆነም የሚከተሉትን ይጠይቃል።
ሀ/ በሰፊ ባለ መሬቶች በጥንታዊ ሥርዓት የሚጨቆነው የገጠሩ ሕዝብ የሚከተሉትን ይጠይቃል፡-
- በዘልማድና በጥንታዊ ዘዴ በጢሰኝነት በመጋዦ መሬት እያረሱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ሁሉ በትውልድ ሀገራቸው ከአያት ከቅድመ አያት በያዙት መሬት ላይ በግፍ የተተከሉባቸው ንጉሳዊ ቤተሰብ መሳፍንትና መኳንንት ተነቅለውላቸው በየቀበሌያቸው በመንግሥት አዋቂና በቀበሌ ሸንጎ አማካይነት መሬት እንዲደለደል
- በውርስ ወይንም በሌላ ሕጋዊ መንገድ መሬት የያዙት ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው የመሬት ይዞታቸው ራሳቸው የሚያርሱት ከሆነ በቤተሰብ ከአምስት ጋሻ በላይ እንዳይበልጥ፣ ራሳቸው የማያርሱት ከሆነ ደግሞ ከአንድ ጋሻ መሬት እንዳይበልጥ። ከዚህ በላይ የሆነው መሬት በሙሉ ተወርሶ በቀበሌ ሸንጎና በመንግሥት ባለሙያዎች አማካይነት መሬት ላልተዳረሳቸውና ለተነቀሉ ለቀበሌው ጢሰኞች እንዲደለደል
- በርስት አገር በሚገኘው ስሪት ምክንያት የያንዳንዱ ሰው ይዞታ በጣም ትንሽና የተበጣጠቀ በመሆኑ የሚጠቃለልበትና ገቢውም ከፍ የሚልበት መንገድ በክፍለ አገር ሽንጎና በመሬት ይዞታ አዋቂዎች እንዲዘጋጅ
- ሰፋፊው ሰው ያልሰፈረበት የመንግሥት መሬት መሬት ለሌላቸው ወይንም ለጠበባቸው አርሶአደሮች ከነማቅኛው እርዳታ ጋር እንዲሰጣቸው
- በቤተክርስቲያን እና በመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣኖች የሚበዘበዘው በቤተክርስቲያን የተያዘ መሬት ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች በቅድሚያ ተከፋፍሎ የተረፈው ለሌላው አርሶአደር እንዲደለደል፣ በአርሶአደሩ ላይ የተጫነውም በቤተክርስቲያን ስም የሚሰበሰብ ልዩ ልዩ ግብር እንዲሠረዝ፣ ቤተክርስቲያን ከምእመናን በምታገኘው እርዳታ እና ምፅዋት ብቻ እንድትተዳደር
- ከላይ የተጠቀሱትም ባስቸኳይ ፍጻሜ እንዲያገኙ እና እስከዚያ ድረስ ማንኛውም ጢሰኛ ከሚያርሰው መሬት ላይ እንዳይነቀል፣ ለባለ መሬት የሚከፍለው መጋዦ በቀበሌ ሸንጎዎች እየተመረመረ እንዲቀነስና ሕገ ወጥ የሆነው ልዩ ልዩ አገልግሎት ትርፍ ሥራና የገንዘብ፣ የከብት ወይንም የሌላ ስጦታ አንዲቀርለት
- የመሬት ግብር በየዓመቱ ከሰብል ውጤት ጋር እየተመጣጠነ እንዲከፈል
- የእርሻ ሰብል ዋጋ ዝቅ ሲል ገበሬው እንዳይጎዳ እና ከፍ ሲልም ሸማቹ እንዳይጎዳ መንግሥት ለሁሉም የሚስማማ የዋጋ ተመን እንዲቆርጥ
- አራሹ ገበሬ ዘመናዊ መሳሪያ እና የመሬት ማዳበሪያ በሚችለው ቀላል ዋጋ እንዲገዛ፣ መንግሥት አስፈላጊውን የእርሻ ትምህርትና ጥበብ እንደ ዛሬ ለከበርቴዎች ሳይወሰን ለአነስተኛው ገበሬ በመላ ኢትዮጵያ በነጻ የሚሰጥበት የእርሻ ምርምርና ማስፋፊያ እንዲሁም የብድር መስጫ ጣቢያዎች በየቀበሌው እንዲያቋቁም፣ የደቦና የመረዳጃ የህብረት እርሻ ሥራ በቀበሌ ሸንጎዎችና በእርሻ ጣቢያዎች አማካኝነት እንዲሰራጭ፣ የአርሶአደር ማህበርና ድርጅትም እንዲቋቋም
- በገጠር በአብዛኛው ስፍራ ያለው ከፍ ያለ የውሃ፣ የመገናኛ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የገበያ ችግር በፍጥነት እንዲወገድ
- ገጠሬው አርሶ አደር በትንሹ በትልቁ፣ በረባ ባልረባው በባለስልጣን፣ በሹማምንት፣ በባለሀብቶች የሚጨቆንና የሚዘረፍ ስለሆነ ጨቋኝ ሹማምንት ላይ በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ
- የልማት፣ የትምህርት፣ የመንገድ፣ የወህኒ ቤት፣ የፖሊስ ጣቢያ መዋጮ እየተባለ የሚሰበሰብ ህገወጥ ታክስ ከአሁኑ ተቋርጦ መንግሥት በራሱ ወጭ ሥራውን እንዲያካሂድ
- ሰብል ሲበላሽ፣ ድርቅ፣ ውሃ ሙላት፣ በሽታ ቢመጣ፣ መንግሥት የሕዝቡ ባላደራ ስለሆነ በኃላፊነቱ መሰረት አስፈላጊውን የቅድሚያ ዝግጅትና እርዳታ ለሕዝቡ እንዲያደራጅና ለወደፊቱም ይህን መስል ችግር ቢፈጠር ሕዝብ እንዳይነካ እንዲደረግ ይጠይቃል።
ለ/ በሚሊዮን የሚቆጠረው፣ በባዕዳን እና በኢትዮጵያውያን ከበርቴዎች የሚበዘበዘው ላብአደርና ሥራ አጥ ከዚህ ግርጌ የተዘረዘሩትን እንዲፈጸሙለት ይጠይቃል።
- ማናቸውም ኢትዮጵያዊ፣ ሃይማኖት፣ ዘር ጾታ ሳይለይ ሰርቶ የተሟላ ኑሮ የመኖር መብቱ ታውቆለት መንግሥት ዋስትና በመስጠት ሥራዎችን በአስቸኳይ እየፈጠረና እያቋቋመ ማናቸውም በከተማ ወይንም በገጠር የሚኖር ሥራአጥ ሁሉ ሥራ እንዲያገኝ፣ የሞያ ማሰልጠኛዎች ተቋቁመው ጎልማሶች ሁሉ የሙያ ትምህርት እንዲያገኙ፣ ሥራ ፈልጎ ያጣ ሁሉ፣ ሥራ እስኪያገኘ ድረስ ከነ ቤተሰቡ ሊያኖረው የሚችል የሥራአጥ አበል እንዲያገኝ
- ዝቅተኛ የሠራተኛ ደመወዝ የመንግሥት፣ የግል፣ የቀን፣ የቤት፣ የእርሻ ሠራተኛን ሳይለይ- እንዲወሰን፣ ከኑሮ ዋጋ ሁኔታ ጋር በማመዛዘን ለኑሮ በቂነቱ የተገመተ በየጊዜው እንዲሻሻል፣ የተሰማራበትን ሙያ— የግል፣ የመንግሥት፣ የቤት፣ የእርሻ— ሳይለይ በቀን ከስምንት ሰዓት፣ በሳምንት ከ40 ሰዓት በላይ እንዳይሠራ፣ ከዚያ በላይ ቢሠራ የትርፍ ጊዜ የሥራ አበል እጥፍ እንዲታሰብለት
- የተሰማራበት ሙያ ሳይለይ መብቱንና ጥቅሙን የሚጠብቅበት ነፃ ማህበር እንዲያቋቁምና ከመንግሥትና ከሠራተኛ ድርጅቶች አስፈላጊውን እርዳታና ማበረታቻ እንዲያገኝ፣ በተለይ ዛሬ ይህን እንዳያደርጉ የታገዱ የመንግሥት፣ የቤት፣ የአነስተኛ ንግድ ቤት፣ የእርሻ ሠራተኞች ማህበር እንዲያቋቁሙ በፍጥነት እንዲፈቀድ
- ሥራ፣ ደመወዝ እና እድገት በወገን በወዳጅ በአምቻ በጋብቻ ሳይሆን፣ ጎሳና ዘር ሳይለይ በችሎታ ብቻ እንዲሆን፣ ለተመሳሳይ ሥራ ተመጣጣኝ የሥራ ዋጋ እንዲከፈል
- ሥራአጡ ባለሙያ ስላለ የውጭ ሀገር ሰዎች ከሥራ ተባረው በሙያቸው ተመጣጣኝ የሆኑት ኢትዮጵያዊያን በቦታቸው እንዲተኩ
- የተሰማራው ሙያ ሳይለይ ማንኛውም ሠራተኛ በሳምንት አንድ ቀንና በሕዝብ በዓላት እንዲያርፍ፣ የሥራ ደረጃንና የአገልግሎት ዘመን የአንድ ወር እረፍት፣ ለህመም ለወሊድና ለሌሎችም ተመሳሳይ ምክንያቶች የተወሰኑ እረፍቶች ከደሞዝ ጋር እንዲያገኝ
- ማንኛውም ሠራተኛ የኑሮን ዋጋ መወደድ የሚያስተካክልበት የተወሰነ የደመወዝ ጭማሪ በየዓመቱ እንዲያገኝ
- ሥራቸውን የሚያሻሽሉበት የሙያ ትምህርት በግልም በመንግሥትም የተቀጠሩ በሙሉ እንዲሰጣቸው
- የአንድ ግለሰብ የከተማ ቦታ በ2000 ካሬ ሜትር ተወስኖ ከዛ በላይ የሆነው ሁሉ በመንግሥት ተወርሶ መንግሥት ቤት ለሌለው ሠራተኛ ሕዝብ መኖሪያ ቤቶች እየሠራ በቀላል ዋጋ እንዲያከራይ፣ የራሱን ቤት ሰርቶ ለመኖር ለሚመርጠውም መንግሥት በቀላል ዋጋ የከተማ ቦታ እንዲሰጥ፣ እስከዚያም ድረስ በቤት ኪራይ ላይ ጥብቅ የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግ ይጠይቃል።
ሐ/ የተናቁትና የተጨቆኑት፣ የእኩልነት መብታቸውን የተገፈፉት ልዩ ልዩ ሕዝቦች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ያቀርባሉ።
- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች፣ ነገዶች፣ ጎሳዎች፣ ዘሮች ሁሉ እኩል መሆናቸው እንዲታወቅና እኩልነታቸው በግብር ላይ እንዲውል፣ ሌላውን መጨቆኑ፣ ተገዥ ማድረጉ፣ መሬቱን ርስቱን መቀማቱ፣ ቋንቋውን ሃይማኖቱን ባህሉን መናቁና ማንቋሸሹ እንዲቀር
- እያንዳንዱ ክፍለ ሃገር በውስጣዊ አስተዳደሩ ሙሉ ነፃነት ኖሮት በዛ የሚኖረው ሕዝብ በመረጣቸው አማካሪዎችንና አስተዳዳሪዎች ራሱን ችሎ እንዲተዳደር
- መሬት ለሌለው መሬት በሚሰጥበት ወቅት ለክፍል አገሩ ተወላጅ ቅድሚያ እንዲሰጥ
- እያንዳንዱ ብሄረሰብ ከአሁን ጀምሮ በገዛ ቋንቋው እንዲናገርበት እንዲዳኝበት፣ የቋንቋው ስፋት ብሄረሰቦችና በጠቅላላው የአገሪቷ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ መሰረት እንዲማርበት እንዲስተዳደርበት እና እንዲሠራበት፣ ባህሉን ወጉን እምነቱን እንዲያስፋፋበት እንዲደረግ ይጠይቃሉ።
መ/ በዱር በበረሃ በመንከራተት የአገርን ድንበርና ነፃነት ለመጠበቅ ከባድ መስዋዕትነት የሚቀበሉትና የጥቂት ሰዎች ምቾት ለመጠበቅ በየእሳቱ እንዲማገዱ የሚደረጉት ወታደሮች የሚከተለውን ይጠይቃሉ።
- ከኑሮ ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና በየጊዜው የሚሻሻል፣ ከነቤተሰባቸው በደህና ሁኔታ ሊያስኖራቸው የሚችል ደመወዝ እንዲያገኙ፣ ከሥራ ሲወጡም የሚሰጣቸው የጡረታ አበል ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚበቃ እንዲሆን
- የማናቸውም ወታደር መብት እኩል እንዲጠበቅ፣ መኮንኖች እንደግል አሽከራቸው እንዳይጠቀሙባቸው በጥብቅ እንዲከለከል
- ከተወሰነ ዓመታዊ አገልግሎት በኋላ ቢፈልጉ በውትድርና እንዲቆዩ፣ ባይፈልጉ ለመውጣት መብታቸው እንዲጠበቅ
- ዕድገትና ሹመት በሥራና በችሎታ ብቻ እንጂ በዝምድና፣ በተለማማጭነት፣ በወሬ አቀባይነት እንዳይሆን ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ
- ባገልግሎት ላይ ሕይወታቸውን ያሳለፉ ወታደሮች ቤተሰቦች ችግር እንዳይደርስባቸው መንግሥት የህይወት ዋስትናና ካሳ እንዲሰጣቸው
- ወታደሮች ከሕዝቡ ጎን ሆነው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ እና ከውትድርና በወጡ ጊዜም በሲቪልነት ደህና ሥራ ማግኘት እንዲችሉ የቀለምና የቴክኒክ ትምህርት ከአሁን ጀምሮ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
ሠ. ለሀገሩ ነፃነት፣ ለክብሩ፣ ለደህንነት ሕይወቱን ደጋግሞ የሰዋው ነፃነቱን በእጅ አዙር በኢምፔሪያሊስቶች የተቀማው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀጥለውን ይጠይቃል።
- በጋራ መከላከያ አስመስሎ የኢትዮጵያን መሬት ለጦር ማስፈሪያ የኢትዮጵያን ማዕድንና የተፈጥሮ ኃብት ለጦር ስንቅ ማዘጋጃ የሚያደርጉት ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር የተፈራረሙት ስምምነቶች በተለይ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የተፈረሙት የጦር ውሎች በፍጥነት እንዲሰረዙ
- የአሜሪካን የጦር አማካሪዎች የሚባሉት ሰላዮች ከሀገር እንዲወጡ፣ አንድም የበዓድ ወታደር በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዳይሰፈር፣ በመገናኛ፣ በህክምና፣ በመዝናኛ ድርጅት ስም ተሸፋፍነው የሚገኙት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት የጦር ማስፈሪያዎች እንዲለቀቁ
- አማካሪ፣ አዋቂ፣ ሊቅ ተብለው በየመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተሰማሩ የአሜሪካንና የሌላ ኢምፔሪያሊስቶች ሰላዮች ከሀገር እንዲባረሩ
- ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ አውታር የሆኑት፣ ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል ቁልፍ የሆኑት የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የአስመጭና ላኪ፣ የቤንዚን አከፋፋይና፣ የማመላለሻ ኩባንያዎች፣ እንደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ አባድር እና ተንዳሆ እርሻ የመሳሰሉ ታላላቅ ኩባንያዎች፣ በባእዳን እጅ የሚገኙት በሙሉ ተወርሰው በመንግሥት እንዲካሄዱ፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ዋና መሰረትም የኢኮኖሚ ነፃነት ስለሆነ የወጭም ሆነ የአገር ውስጥ ንግድ በኢትዮጵያውያንና በመንግሥት ድርጅቶች ብቻ በትብብር እንዲሠራ
- ለውጭ ሀገር መንግሥታት ወይንም ሰዎች የተሰጠው መሬት ሁሉ እንዲመለስ ይጠይቃል።
ረ/ የሀገሩ ውድቀት፣ የሕዝቡ መደህየትና መጎሳቆል፣ የነፃነት ትርጉም ማጣት፣ የሰብአዊ መብቶች መገፈፍና መሠረዝ ህሊናውን ያናወጠው አገር ወዳድና ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ያቀርባል።
- ጉቦንና መድልዎን የሚያጠፋ ሕግና ድርጅት እንዲቋቋም፣ ሕጉን ጥሶ ጉቦ ሲቀበል፣ መድሎ ሲያደርግ የተገኘ ፣ወይም በስልጣን አማካይነት የሕዝብ ኃብት የሚዘርፍና የሚቀማ፣ በሕዝብ ላይ በደልና ግፍ የሚሠራ፣ የመንግሥት ሀብት ለራሱ ጥቅም የሚያውልና የሚያባክን፣ የተጣለበትን የሕዝብ አደራ ያጎደለ በስልጣን ከፍ ያለ ቅጣት እንዲቀጣ
- እስከዛሬ ድረስ በፍትህ ማጣት የተጉላላው ሰው ሁሉ ትክክለኛ ፍርድ ያገኝ ዘንድ የፍርድ ቤቶች አቋም በቶሎ እንዲለወጥ እና የፍርድ ሥራ እንዲፋጠን፣ ፍርድ ቤቶች ከአስተዳደር ተለይተው ትልቅ ትንሽ ሳይሉ ያለ አድልዎ እንዲፈርዱ፣ እስካሁን ጉቦ በመብላት የታወቁ ዳኞች ከስፍራቸው ተነስተው እርምጃ እንዲወሰድባቸው
- ቤተክርስቲያን እና መንግሥት እንዲለዩ፣ ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል መሆናቸው እንዲታወቅ፣ መንግሥት አንዱን ሃይማኖት ድግፎ ሌላውን እንዳይጨቁን፣ ከሁሉም ገለልተኛ እንዲሆን
- ሴተኛ አዳሪዎች ይህንን ወራዳና አሳፋሪ ሥራ ትተው ሌላ ለሰው ክብር ተስማሚ የሆነ ሥራ እንዲያገኙ መንግሥት ልዩ ጥረት እንዲያደርግላቸው፣ መጠጥና የአመንዝራ ሥራን በማስፋፋት የሚጠቀሙ ባለቡና ቤቶች ይህን ሥራሳቸውን በቶሎ እንዲያቆሙና ገንዘባቸውን በሌላ ጠቃሚ ሥራ ላይ እንዲያውሉት እንዲደረግ
- የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ተራውን ሕዝብ የሚጠቅም አመራር እንዲኖረውና ቋሚና ጥብቅ የሆነ የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግ፣ ከውጭ የሚመጣ እቃ የጥቂቶች መንደላቀቂያ ሸቀጥ ሳይሆን ለአገሪቷ ልማት ብቻ የሚውል እንዲሆን፣ የመንግሥት በጀት ለርካሽ መደለያ፣ መጋበዢያ፣ መፈንጠዢያ ሳይውል ለልማት ብቻ እንዲወሰን፣ ታክስና ግብር በየሰዉ ጠቅላላ ገቢ ላይ ተመሥርቶ እንደየገቢው ከፍተኛነት ለመንግሥት የሚከፍለውም ታክስና ግብር እንዲያድግ
- በከተማና በገጠር ውሃና መብራት ማከፋፈያዎች፣ እንደ አንበሳ አውቶቡስ፣ እንደ ቀ.ኃ.ሥ በጎ አድራጎት ድርጅት የመሳሰሉ ድርጅቶች በመንግሥት እንዲወረሱ
- ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ጠብና ጭቅጭቅ በወንድማማችነት መንፈስ እንዲበርድ ተደርጎ በአፍሪካና በቅርብ ምሥራቅ ካሉ ነጻ አገሮች ጋር ሁሉ የወንድማማችነት ግንኙነት እንዲመሰረት እና እንዲስፋፋ፣ ለነፃነታቸው ለሚዋጉ አፍሪካውያን በገንዘብ ሆነ በትጥቅ እርዳታ እንዲደረግ
- ማናቸውም ኢትዮጵያዊ የሀሳብ ነፃነቱ እንዲጠበቅ እና እንዳይደፈር፣ ሀሳቡን በቃል፣ በፅሁፍ ወዘተ የመግለጽ መብቱ እንዲከበር፣ ይህ መብቱ አሁኑኑ በሥራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው ዋስትና እንዲሰጠው
- የፈለገውን ሃይማኖት የማመን፣ የመረጠውን ፍልስፍና የመከተል፣ ይህንኑ ለሌሎች የማስተላለፍ መብቱ እንዲከበርለት እና ሥራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው ዋስትና እንዲሰጠው
- በህግ፣ በልማት፣ በእምነት ላይ የተመሰረተ፤ በአስተዳደግ፣ በትምህርት፣ በጋብቻ፣ በሥራ፣ ባስተዳደር ተካፋይነት በሴቶች ላይ የሚደረገው ድርብ ድርብርብ ጭቆና ተሰርዞ የጾታዎች እኩልነት በሕግ አስፈላጊው ዋስትና ተሰጥቶት በቃል ብቻ ሳይሆን በገቢርም ጎሳ እና ሀይማኖት ሳይለይ እንዲመሰረት
- የመሰብሰብ እና ማህበር የማቋቋም መብቱ እንዲጠበቅ እና እንዲከበር፣ የፖለቲካ፣ የሙያ፣ የንግድ የመረዳጃ ወዘተ ማህበሮች ለማቋቋም፣ እነርሱም ውስጥ ለመሳተፍ የሚችልበት፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ስሜቱንና ፍላጎቱን የሚገልጽበት መብቱ እንዲጠበቅለት እና እንዲከበርለት፣ ይህም መብቱ ሥራ ላይ የሚውልበት አስፈላጊው ዋስትና አሁኑኑ እንዲሰጠው
- የደህንነት እና የህልውና መብቱ እንዲጠበቅ እና እንዲከበር፣ ያላግባብ እንዳይታሰር፣ እንዳይጉላላ፣ እንዳይቀጣ፣ መኖሪያ ቤቱ፣ ደብዳቤዎቹ እንዳይፈተሹ አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግለት
- ሕዝቡን የሚያጉላሉ በፀጥታ፣ በካቢኔ በልዩ ቅርንጫፍ ወዘተ ስም የሚጠሩ በግልጽ እና በስውር የሕዝቡን የፖለቲካ መብት የሚቃረኑ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፖሊስ ድርጅቶች እንዲዘጉ
- ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይል ሁሉም በነጻ እንዲማር፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ግዴታ እንዲሆን፣ መንግሥት አስፈላጊውን እርዳታ እየሰጠ ትምህርት የሚፈልግ ሁሉ እንዲማር፣ እውቀቱንም እንዲያዳብር መንግሥት ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ
- በአገሪቱ ውስጥ ምን እንደተሠራ፣ ምን እንዳልተሠራ፣ ምን እንደታቀደ በራድዮ፣ በጋዜጣና በዜና ማሠራጫዎች አማካይነት ለሁሉም በይፋ እንዲገለጽ፣ ሕዝቡን በጉዳዩ ሀሳቡን በመንግሥትም ሆነ በግል ማሠራጫዎች መስጠት እንዳይከለከል
- ትክክለኛና የማያዳላ መንግሥት የማግኘትና የመመስረት መብቱ የሕዝቡ ብቻ እንደሆነ ታውቆ መንግሥቱ በሕዝብ የተመረጠና የተደገፈ፣ በሕዝብ ቁጥጥር ስር ብቻ የሆነ፣ በሕዝብ ፊት ኃላፊነት… እንዲሆን ይጠይቃል።
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በሙሉ እስኪያስፈጽም ድረስ ሰፊው ሕዝብ ትግሉን ይቀጥላል። ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት መሰረታዊ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች የሚያምኑ፣ እነዚህን ለማስፈፀም በሥራ ላይ ለመዋል ቆርጠው የተነሱ ሁሉ መደራጀት ይገባቸዋል። ድርጅት —በአንድነት ላንድ አላማ መሰለፍ— ኃይል ነው። መብትን በመግፈፍ የሚጨቁነውንና የላን ዋጋ የሚዘርፈውን ጠላት በደንብ ለመቋቋምና ድል ለማድረግ፣ ራስን ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ከባድና የማይበገር ኃይል ነው።
ለብዙ ዘመናት ወስጥ ውስጡን እንደእሳተ ጎሞራ ሲገመግም የነበረው የሕዝብ ትግል ባለፈው ወር ፈንድቷል። የገዢው መደብ ትግሉን ለማጨናገፍ በብዙ መንገድ ሲጥር ይታያል። በአሁኑ ጊዜ እዚህም እዚያም ቦግ ቦግ ያለው እንቅስቃሴ ያልተያያዘና መሰረቱ ያልጠነከረ በመሆኑ የገዢው መደብና ግብረአበሮቹን ሊያዳክሙት ይችላሉ። ትግሉን ለመቀጠልና ወደፊት ለማራመድ የሚቻለው በመደራጀት ብቻ ነው።
23.7.66
