ፍቅሬ መርዕድ

ፍቅሬ መርዕድ፣ ከእናቱ ከወ/ሮ አበባ ፈለቀ እና ከአባቱ ከጄኔራል መርዕድ መንገሻ በአዲስ አበባ ከተማ ጥር 27 ቀን፣ 1934 ዓ.ም. ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ በሚገኘው ሳንፎርድ የእንግሊዝ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።

ፍቅሬ መርዕድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአራት ዓመት ትምህርት ተከታትሎ በፓለቲካል ሳይንስ የባችለር ኦፍ አርትስ ዲግሪውን በከፍተኛ ማዕረግ ተቀብሏል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም “ኒውስ ኤንድ ቪውስ” ይባል የነበረውን የተማሪዎች መጽሔት በዋና አዘጋጅነት አገልግሏል።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ፈረንሳይ በማቅናት በኤክስ ማርሴይ ዩኒቨርሲቲ ለ9 ዓመታት በህግ የመደበኛ እና የድህረ ምረቃ ትምህርቱን አጠናቋል።

በፈረንሳይ አገር ቆይታውም በአውርጳ የተማሪዎች ማህበር ውስጥ የጎላ ተሳትፎ ነበረው። ማህበሩ ያሳትማቸው የነበሩትን ትግላችን እና ታጠቅ የተባሉትን መጽሔቶች በዋና አዘጋጅነት አገልግሏል። በእውሮጳ ቆይታው ወቅት በነሐሴ 1960 ዓ.ም. በሀምቡርግ የተመሠረተው የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መሥራች አባል ነበር። ፍቅሬ መርዕድ፣ ከአማርኛ በተጨማሪ በእንግሊዘኛና በፈረንሳይኛ ሃሳቡን በጥራት የመግለጽ ድንቅ ችሎታ ነበረው።

በ1964 ዓ.ም. በፈረንሳይ በሕግ ከፍተኛ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ በመምህርነት አገልግሏል። በመምህርነቱም ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ፣ ውስብስብ ሃሳብን ግልጽ አድርጎ በማስረዳት ችሎታው በተማሪዎቹ ዘንድ ታላቅ አድናቆትን ያተረፈ መምህር ነበር። ከማስተማሩም በተጨማሪ በአብዮቱ ዋዜማ ተቋቁሞ በነበረው የዩንቨርሲቲው መምህራን የውይይት መድረክ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበር። በዚህም ሳቢያ በጠቅላይ ሚንስትር እንዳልካቸው መኮንን አጭር የአስተዳደር ዘመን ለጥቂት ጊዜ ከሌሎች መምህራን ጋር ለእስር ተዳርጎ ነበር።

አብዮቱን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው ተዘግቶ፣ ተማሪዎች ለእድገት በህብረት ዘመቻ በተሰማሩበት ወቅትም ፍቅሬ መርዕድ በሕግና ፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አገልግሏል። በ1968 ዓ.ም.  የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሲቋቋም ወደዚሁ ጽ/ቤት ተዛውሮ ማገልገል ጀመረ። ይህንንም ውሳኔ በሚያደርግበት ወቅት በዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ ያገኝ የነበረውን ደመወዝ ቀንሶ እና አግኝቶ የነበረውን የቤተስቡን ወጪ ጭምር የሚሸፍን በውጪ አገር የሙሉ ስኮላርሺፕ ዕድል በመተው ነበር።

በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት የጊዜያዊ ጉዳዮች ሰብሳቢ በመሆን በማገልገል ላይ እያለ መሰከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሞርጌጅ ህንጻ ውስጥ ትሠራ የነበረችውን ባለቤቱን መኪናው ውስጥ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ሳለ አድብቶ ይጠብቅ በነበረ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳይ በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ በአጭር ተቀጨ።

በብዙዎች ዘንድ በምሁርነቱ፣ በትህትናው፣ በጨዋነቱና አስተዋይነቱ የሚታወቀው ፍቅሬ መርዕድ ሕይወታቸው በአጭር ከተቀጩት ታዋቂ የመኢሶን መሪዎች የመጀመሪያው ነበር።

ፍቅሬ መርዕድ ከትዳር አጋሩ ከወ/ሮ ማንያህልሻል ከበደ ሁለት ልጆች አፍርቷል።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top