ሰሕድ ቁ. 34

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 34፣    ታሕሣሥ 20፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ግፊት በወታደራዊ መንግሥት የታወጁት አዋጆች በተግባር እስካሁን ተፈጻሚነት  እንዳላገኙ ይጠቁማል። አዋጆቹ በእርግጥም የአብዮታዊ ትግሉ ጎዳና ጠቋሚዎች መሆናቸው የማይካድ ሃቅ እንደሆነ ይገልጻል። ሆኖም ግን፣ አዋጆቹ በተግባር ላይ ውለው ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ትግሉ ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባል። ተራማጆችም ትግሉ በአሸናፊነት እንዲጓዝ፣ መታገልና ማታገል እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባል።      

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 34                                                                      ቀን 20/4/68

 

አዋጆች፣ ዘመቻውና አብዮቱ

ብዙ መስዋእትነት ሲያደርጉ ቆይተው በየካቲት 1966 ዓ.ም. የገማውንና የተላውን የአጼን አገዛዝ በገሃድና በአንድነት ከዘመቱበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በተፋጠነ ሁኔታ ብዙ ድሎችን ተጐናጽፈዋል። ያገኟቸው ድሎች በአዋጅ ደረጃ ጐልተው ሲታዩ በድርጊት ደረጃ ግን ገና ተፈፃሚነት አላገኙም። እነዚህ የአዋጅ ድሎች በተግባር ተፈፃሚነት እንዲያገኙ፣ በእርግጥ ወደሰፊው ሕዝብ እጅ እንዲገቡ ገና ብዙ ትግል መደረግ አለበት። እነዚህ የአዋጅ ድሎች መገኘታቸውን ግን እራሱ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮት ጐዳና መራመድ ለመጀመሩ አይነተኛ ምልክቶች ናቸው፤ መታገያ ነጥቦች ናቸው፤ የአብዮት ኃይሎችን ከፀረአብዮት ኃይሎች የሚለዩ የአብዮታዊ ትግል መድረክ ክፋቾች ናቸው። ስለዚህም ዛሬ፣ ወላዋይና አመንቺ የሆነው ወታደራዊ ደርግ የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ እርምጃ ሲያደናቅፍ፣ ኢምፔሪያሊስቶች በቢሮክራሲውና በደርጉ ውስጥ በተሰገሰጉት ቡችሎቻቸው አማካይነት ሲያሴሩና ሲዶልቱ፣ መሳፍንትና መኳንንት ከነጭፍሮቻቸው ተደራጅተውና ታጥቀው ፀረአብዮት ትግላቸውን በያለበት ሲያፋፍሙ የአብዮቱ ጥሪ፣ የሰፊው ሕዝብ የደም ድምጽ በአብዮታውያን ጆሮ፣ በሃቀኛ ተራማጆች ጆሮ ከምንግዜውም ይበልጥ ይደውላል።

የተራማጆች ሚና ሰፊው ሕዝብ ድል ሲጐናፀፍ በድሉ ሳይሰክሩ ለሚቀጥለው ትግል እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ የጊዜውን ዋና ጠላት ከሁለተኛ ደረጃ ጠላቶች ለይቶ ሰፊው ሕዝብ በሙሉ ኃይሉ እንዲቋቋመው ማድረግና እያንዳንዷ ትክክለኛ ድርጊት በጠቅላላው አብዮታዊ ጐዳና ላይ ምን ያህል ወደፊት እንደምታራምድ ማሳየት ነው። ይህንንም ሲያደርግ ባልጠራና ባልበራ እንቶ ፈንቶ ተረት ሰፊው ሕዝብ እንዳይታለል፣ አድርባዩችን፡ ፀረአብዮት ከፋፋዩችንና ውዥንብር ነዥዎችን፣ የሰፊው ሕዝብ ወገን ነን በማለት ብቻ እያወናበዱ ሰፊውን ሕዝብ ሳይዘጋጅ በማጋፈጥ ቅስሙን የሚያሰብሩትን፣ በውስጡ ሰርገው የገቡ የጠላት ጋሻ ዣግሬዎችንና ጠቋሚዎችን ነጥሎ እንዲያወጣ መታገል ያስፈልጋል።

እነዚህ ውዥንብር ነዥዎች በሰፊው ሕዝብ ትግል ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት፣ ሊያሳዩት የሚሞክሩትን አሳቻ ጐዳና አደገኛነት በመመልከት፣ ካሁን ቀደም በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 3ዐ ላይ በመጠኑ አሳባችንን የገለጽንበት ቢሆንም የዘመቻውንና የአብዮቱን ጉዳይ ዛሬ እንደገና እናነሳዋለን።

በቁጥር 3ዐ ለማመልከት እንደሞከርነው “አብዮታዊው የመሬት አዋጅ፣ የአንዳንድ የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች መወረስ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች የመንግሥት መሆን . . . የማይናቁ ድሎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በአዋጅ በመነገራቸው ብቻ አብዮት ተደረገ ብለው የሚያምኑ በአዋጅ እንጂ በሰፊው ሕዝብ ትግል እምነት የሌላቸው ብቻ ናቸው። በሌላ በኩል ግን በአዋጆቹ በመጠቀም አብዮታዊውን ትግል ለማፋፋምና ለማጠናከር የማይነሳሱት   “ተራማጆች”  ሁሉ ደግሞ፣ በአዋጆች ብቻ ከሚያምኑት ባላነሰ በሰፊው ሕዝብ ትግል ላይ እምነት የሌላቸው ናቸው። ዛሬ የሚታወጁት ስርነቀል አዋጆች ሁሉ፣ በሰፊው ሕዝብ ትግል የተገኙ የሰፊው ሕዝብ ድሎች እንጂ፣ “ጥቂት ምርጥ መኮንኖች” ስላሰኛቸው የሚለግሱአቸው ገፀበረከቶች አይደሉም። ይህንን እውነት አለመረዳት /ተረድቶም አለመቀበል/ ወይ ፍፁም የዋህነት አለበለዚያም የአድሃሪያንን ሰልፍ ማሳመር ነው።

“የገበሬዎችን ማህበራት ለማደራጀትና ለማጠናከር” የወጣው የታህሳስ 4 ቀን 1968 ዓ.ም. አዋጅም እንደተቀሩት ስርነቀል አዋጆች ሁሉ አብዮቱ ገፍቶ ያስገኘው አዋጅ ነው። ለመስከረም 2 ቀን “በአል” መጥተው የነበሩ የገበሬ ማህበራት ተወካዮችና በጠቅላላውም ሰፊው አርሶአደር ሕዝብ፣ ወዝአደሩ፣ ተራማጅ ዘማቾች፣ የመሬት ይዞታ ሠራተኞች  የገበሬ ማህበራት ህጋዊ አካል ኖሯአቸው ከአድሃሪ አስተዳዳሪዎችና ፖሊሶች ተጽእኖ እንዲወጡ ደጋግመው ጠይቀዋል፣ ታግለዋል። መለስ ብሎ “የገጠርን መሬት የሕዝብ ያደረገው አዋጅ” በሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት የገጠሙትን ችግሮች፣ መሰናክሎችና ዝብርቅርቅ የተመለከተ፣ የአርሶአደሩንና የጠቅላላውን የተራማጅ ወገኖች ጥያቄዎች በትክክል ያጤነ ሁሉ፣ የታህሳስ 1968 ዓ.ም. አዋጅ በሞላ ጐደል ለአብዮታዊ ኃይሎች ሁሉ የተሻለ የሥራ አካባቢ እንደሚፈጥርላቸው ይረዳል። የተሻለ የሥራ አካባቢ ይፈጥራል ስንል እስካሁን በዚህ ረገድ የነበረው ችግር ምንድነው? 

ዛሬ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከአንዳንድ ቦታዎች በስተቀር፣ ገበሬው ከሁለት ጠላት ጋር ተፋጧል። በአንድ በኩል በመሬት ይዞታ አዋጅ መሬቴን ተቀማሁ ባዩ የመሬት ከበርቴ ሁሉ፣ ጉልተኛ ሁሉ በደርጉ የቀኝ ክንፍ ውስጣዊ ፈቃድ ታጥቆ የገበሬ ማህበራትን ሊያፈርስ ይታገላል። በሌላ በኩል ፀረአብዮት የሆነው ቢሮክራሲና ፖሊስ ከነዚህ ጉልተኞች ጋር እየተመሳጠረ የገበሬ ማህበራት መሪዎችን ያሥራል፣ ይረሽናል። በሲዳሞ እንደደረሰውም (ሰህድ ቁጥር 32 ተመልከት) ፊውዳል አስተዳዳሪዎችና አድሃሪ የደርግ አባሎች ሲገናኙ ትልቅ የሕዝብ እልቂት ይከናወናል። እንደቤጌምድር ባሉ የመንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ ኃይሎች ለማንሰራራት በሚሞክሩባቸው ቦታዎች አድሃሪ አስተዳዳሪዎች እየተፈራረቁ፣ ሕዝቡ እንዳይነቃ፣ እንዳይደራጅ ያደርጋሉ፣ ያወናብዳሉ። ዘማቾች የመሬትን አዋጅ መሳሪያ አድርገው ሕዝቡን ሲያደራጁ፣ ሲያስተምሩና ከጐኑ ሲሰለፉ ፖሊሶችና አድሃሪ የደርግ ዟሪ ቡድን አባላት ያስሯቸዋል፣ ይረሽኗቸዋል። ከአድሃሪዎች ጋር በተጨባጭ መንገድ የተሰለፉ አድርባዩች ዘማቹን ተስፋ እያስቆረጡ ለሥራ ከሚያመችበት አካባቢ ሳይቀር ከገበሬው ጋር እንዳይሰራ፣ የትግሉን ሜዳ እየለቀቀ እንዲሄድ ይገፋፉታል።የዘመቻ መምሪያ በተባለው ድርጅት ውስጥ የተሰገሰጉ የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች /አድሃሪ ኘሮፌሰሮች/ ታጋይ ዘማች እንደ ወንጀለኛ እንዲቆጠር፣ በፖለቲካ እንዳይነቃ፣ አርሶአደሩንም ሕዝብ እንዳያነቃ፣ ፊደል ማስቆጠር እንኳ በዝቶ በ“ጽዳት ዘመቻ” እንዲወሰን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ አዲሱ የታህሳስ አዋጅ በራሱ ይለውጠዋል ማለት ባንችልም የዚህ አዋጅ መታወጅ ለገበሬው፣ ለመሬት ይዞታ ሠራተኛውና ለዘማቹ ተጨማሪ ጥይት ይሰጠዋል፣ ህጋዊ ድጋፍ ያስገኝለታል። አዋጁ ራሱ የቀድሞ ባለመሬቶችን፣ አድሃሪ አስተዳዳሪዎችን፣ አድሃሪ የደርግ አባሎችን ከምድር ገጽ እያጠፋቸውም፤ ወይም ተራማጅ መሰል አወናባጆችን እንዳያወናብዱ አያደግጋቸውም። የገበሬ ማህበራትንና ታጋይ ዘማቾችን አሁንም መራራ ትግል ይጠብቃቸዋል።

ይህንን አዋጅ፣ ይህንን የሰፊው ሕዝብ ድል መናቅ፣ ወይንም በአዋጆቹ ተጠቅሞና ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሁኖ አብዩታዊውን ትግል ለማፋፋምና ለማጠናከር አለመነሳሳት፣ እራስን እንደእፍታ፣ ሰፊውን ደግሞ እንደዝቃጭ ቆጥሮ ከትግሉ መድረክ መውጣት ነው፤ ያለዚያም ጭልጥ ብሎ ከአድሃሪው ሰፈር ውስጥ መግባትና መደባለቅ ነው። በሌላ በኩል ግን፣ በአዋጆቹ ክልል ውስጥ ብቻ ተውጦ መቅረትና መዳከር ደግሞ፣ ሲያንስ የአብዮታዊውን ትግል ባህርይ አለመረዳት፣ ሲበዛ ደግሞ አድሃሪነት ነው።

የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቀደም ብሎ እንዳመለከተው ሁሉ፣ ተራማጆች “መሬት እንደውሃ የጠማው ገበሬ መሬት ላራሹ ከሚለው መፈክር አልፈው፣ ዛሬ በትግሉ በበለጠ በቀሰመው ትምህርት እየተጠቀሙ ነፃነት ላራሹ በሚለው መፈክር ስር እንዲሰለፉ ማድረግ አለባቸው።”ደርጉ ሺህ ጊዜ “የዘመቻው መታጠፍ የአብዮቱ መታጠፍ ነው” እያለ ቢደነፋ፣ እነርሱ ደግሞ ቢልዩን ጊዜ ለሰፊው ሕዝብ “አብዮቱ የሚታጠፈው ዲሞክራሲያዊ መብቶች በመታፈናቸው፣ ሰፊው ሕዝብ ባለመታጠቁ ነው” እያሉ ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ማስተማር አለባቸው፣ መታገል አለባቸው። ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆነው ለዲሞክራሲያዊ መብቶችና በትጥቅ ለተደራጁ የገበሬ ማህበራት መታገል አለባቸው። የነቁ የታጠቁ የገበሬ ማህበራት ለጀመርነው ለአዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮት ተገን ሰራዊት መሆናቸውንና ሕዝቡ ስልጣኑን እጁ የሚያስገባው አወናባጆች እንደሚሉት በምርጫ ሳይሆን መሳሪያ በመጨበጥ መሆኑን ማስተማር አለባቸው። ውዥንብር ነዥዎች እንደሚያስሞክሩት ሕዝቡ ብድግ ብሎ “ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት” እንደመና ከሰማይ ይውረድልን እያለ የጊዜውን አጣዳፊ ተግባር እንዲስት ማድረግ ሳይሆን ሰፊው ሕዝብ ተደራጅቶ፣ ነቅቶ፣ ታጥቆ ድል በድል እየተጐናፀፈ የፖለቲካውን ስልጣን እንዲወስድ መጣር አለባቸው።

ዛሬ ተራማጆች በጽሁፍና በቃል ደጋግመው እንደሚሉት ሕዝቡ “መብቶቹን ለማግኘት በሚያደርገው ትግል ሁሉ ከጐኑ እንሰለፋለን” ማለት፣ በጥንቃቄና በትጋት ከሰፊው ሕዝብ ጋር መዋሃድ፣ ከርሱ መማር መልሶም ማስተማር፣ ከርሱም ጋር ሆኖ አዲሲቱን ኢትዮጵያ መመስረት ማለት እንጂ፣ ሰፊውን ሕዝብ በአፍ ጉቦ መደለልና መሸንገል ማለት አይደለም።

ዛሬ የህብረተሰባችን ልዩ ልዩ መደቦችና የፖለቲካ ቡድኖች ባለዘመቻው መቀጠልና አለመቀጠል የተለያዩ አቋሞች እንዳሏቸው ግልጽ ነው። መሰረታዊ ልዩነታቸውም ዘመቻው ይቀጥል አይቀጥል በሚለው ጥያቄ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እንዴት ይቀጥል በሚለውም ጥያቄ ላይ ጭምር ነው።

አድሃሪው ወገንና ዛሬ ሰፊውን ተማሪና ዘማች እያወናበዱ “ዘመቻውን መበተን” በሚለው መፈክር አብዮቱን በማዳከም ላይ ያሉ “ተራማጆች” የማይነዙት ፀረዘመቻ ኘሮፖጋንዳ የለም። ዘማቾችን ከአርሶ አደሩ ሕዝብ ጋር ለማጣላት ያልጠነሰሱት ሴራና ያልገለበጡት ድንጋይ የለም። ዘማቾች በየገጠሩ የገጠማቸውን ችግር፣ አጉልቶ አጉላልቶ ማሳየቱና ከዚህም የተነሳ ጣቢያቸውን እየለቀቁ ወደከተማ እንዲመጡ መገፋፋቱ ከአብዮቱ አንፃር ሲታይ አደገኛና ዙሮ ዙሮም ለፀረአብዮት ኃይሎች የሚያመች ድርጊት ነው።

ሰፊው አርሶአደር ገበሬ፣ ዘማቾችና ተራማጅ የመሬት ይዞታ ሠራተኞች  ባዶ እጃቸውን ተጋፍጠው አድሃሪዎቹ የመሬት ከበርቴዎችና የመንግሥቱ የመጨቆኛ መሳሪያዎች ይህ ነው የማይባል የማስፈራራት፣ የማንገላታታና የውንብድና ተግባር እንደፈፀሙባቸው፣ የብዙዎችን ሕይወትም እንዳጠፋ ግልጽ ነው። እንደዚህ አይነቱ ፀረሕዝብ ድርጊት እንዲቆም ማድረግ የምንችለው ግን ዘመቻው እንዲበተን፣ በዘማቹና በአርሶአደሩ መካከል የተገነባው የትግል አንድነት እንዲፈርስ በመገፋፋት ሳይሆን ገበሬው እንዲታጠቅ፣ ዘማቹም የራሱን አብዮታዊ ሥራ ትክክል በሚመስለው መንገድ የሚያቀናብርበት፣ የሥራ ልምድ የሚለዋወጥበት፣ ለወደፊቱም የሥራ እቅድ የሚተልምበትና ብሶቱን የሚገልጽበት የዘማቾች ጉባኤ እንዲጠራና የዘማቾች ኮሚቴ እንዲቋቋም በመታገል ነው።

ዛሬ ሰፊውን ተማሪና ዘማቾችን በተራማጅነት ስም የተደባለቃቸው የፖለቲካ ቡድን አሳሳች ጥሪዎችን በመንዛት ዘመቻውን ለመበተን ይህ ነው የማይባል ጥረት እንደሚያደርግ የአደባባይ ምስጢር ነው። የዘመቻውን መጨናገፍ የሚሻው እርሱ ብቻ አይደለም። “የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት” በሚለው ፊውዶፋሽስት ድርጅት ስር የተደራጁት እነመንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ -ኢያሱ መንገሻም የዘመቻው ጉዳይ ሆዳቸውን በልቷቸዋል። የዚህ የ“ዲሞክራቲክ” ድርጅት መግለጫ እነሆ፡-

​   “ደርጉ የለውጡ ዋና ደጋፊዎችና ብዙ መስዋአትነት በመፈፀም ጥርጊያውን የከፈቱለት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እየጎተቱ በሚገባ ባልተጠናና አስፈላጊ ለሆነውም ዝግጅት በቂ ጊዜ ሳይሰጥ ለደርጉ ኘሮፖጋንዳ ወደ ገጠር ዘመቻ እንዲያደርጉ የላካቸው ወጣቶች በገጠማቸው ችግር ምክንያት ወደ ዘመዶቻቸው ሲመለሱ፣ ሌሎቹም ለትምህርት በመጓጓት ተደብቀው ሲቀሩ፣ ብዙዎቹ ደግሞ የደርጉን አሰራር በመቃወም በየጐረቤት አገር መሰደድ ግዴታ ሆነባቸው። በዚህም ምክንያት በትእዛዝ አለማክበር አሳበው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከሞት የተረፉት በእስር ይማቅቃሉ። ከዚህ በላይ ባጭሩ በተገለፁት ምክንያቶች የደርጉ አባሎች አገሪትዋን ወደነፃነትና ሰላም ወደፊት በማራመድ ፈንታ እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን የሕዝቡን አካሎች በማጉላላት ኢትዮጵያን ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደገደል አፈፋፍ አድርሶ ዛሬ ከነጭራሹ ገደል ገብታ እንድትበታተን ወደሚያስገባት ደረጃ አድርሷታል” ይላል።

    አንባቢው የኢትዮጵያን ሕዝብ የቁም ስቃይ ሲያሳዩ የነበሩት፣ በየአደባባዩ “መሬት ላራሹ” ብሎ የሚያስተጋባው ወጣት ሲረሽኑና ሲያስረሽኑ የነበሩት መኳንንትና መሳፍንት ዛሬ ለተማሪና ላገሪትዋ ተቆርቋሪ ሆነው የሚያፈሱለትን የአዞ እንባ ልብ በልልን። የዘመቻው መታወጅ፣ የዘማቾች በየገጠሩ መሰማራት የአብዮቱን መጠናከር እንደሚያስከትል ስለሚገነዘቡት የቀድሞ ገዥዎቻችን በሆነ ባልሆነው እያመካኙ ዘመቻውን ለመበተን ቢነሱ አንገረምም፣ በኘሮፖጋንዳ ብቻ ሳይሆን በጥይትም እየበተኑት ነው። የሚገርመን ግን በተግባር ከመሳፍንት ጋር የተሰለፉትን “ተራማጆች” ተመሳሳይ መግለጫ ስናይ ነው። “ተራማጆቹ” እንዲህ ይላሉ፡-

​“ሰፊው ሕዝብ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመሰለፍ፣ የመደራጀት  . . .  ወዘተ. መብቶቹ ሳይከበሩለት፣ ይሰራለታል የሚባለው ነገር ሁሉ ፍፁም ቅጥፈት ስለሆነ፣ መብቶቹን ለማግኘት በሚደረገው ትግል ሁሉ ከጐኑ እንሰለፋለን” ካሉ በኋላ ቀጠል አድርገው “ . . .ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን ዘመቻ ላይ ታስረን በመቆየት፣ ምንም ባንሰራለት የድሃውን ገንዘብ በመብላት በሁለተኛ ደረጃም ቢሆን (በአንደኛ ደረጃ ተጠያቂው “የምርጦቹ መንግሥት” ነውና) ተጠያቂ መሆናችንን ስለምናውቅ (ያለአግባብ መበልፀግ ብቻ ሳይሆን ያለአግባብ ማባከንም ወንጀል ነውና) የሚደርስብንን ሁሉ እንቋቋመዋለን እንጂ፣ በወንጀሉ ተባባሪዎች አንሆንም” ካሉ በኋላ ቀጠል አድርገው “አሁን ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ ነው። ዘመቻው ውድቅ መሆኑን አምኖ መቀበል፣ ጣቢያዎቹን መዝጋት፣ ዘማቾችን ወደየመጡበት . . . . መመለስ፣ መምሪያውን ማፍረስ። ይህንን እምቢ ማለት የሰፊውን ሕዝብ ታሪካዊ ፍርድ ለመቀበል መዘጋጀት” ነው ይላሉ። 

ነገሩ ግልጽ ነው። ይህ አቋም ለየትኛው የህብረተሰብ ክፍል እንደሚጠቅም ግልጽ ነው። ዘመቻው በቂ ጥናት ኖረውም አልኖረውም፣ በዘማቾች ላይ ጉዳት ደረሰም አልደረሰ የዘመቻው መፈታት የሚጠቅመው ለፀረአብዮት ኃይሎች ነው። ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ይሸከማል እንደሚባለው ሆኖ ነው እንጂ ተራማጅ ዘማቾች ዋናውን የዘመቱበትን ተግባር የሚስቱት አይመስለንም። ብዙ ችግሮች ቢኖሩባቸውም በትግል ይወጧቸዋል። አንድ “ከዘማቾች ለዘማቾች” የሚል ወረቀት የጊዜውን የትግል ዘዴዎች በትክክል እንዳበሰረው ሁሉ፣ በዛሬው ወቅት ዋናው ተግባር ጥያቄዎችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ በየቦታው በጥያቄዎቹ አካባቢ በጥንቃቄ መደራጀት፣ ሰፊው ሕዝብ በሚገኝበት ቦታ ተገኝቶ ሰፊውን ሕዝብ ማደራጀትና ከርሱው ጋር ሆኖ መታገል ነው።

–  የጊዜው አንዱ ዋና ጥያቄ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ ነው። ዲሞክራሲያዊ መብቶች በትግል እንጂ በስጦታ አይገኙም። ሰፊውን ሕዝብ ለህዝባዊ ዲሞክራሲ መቀስቀስ፣ ማስተማርና ማደራጀት አለብን።

–  ሌላው ዋና ጥያቄ የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ ነው። ትጥቅም በልመና አይገኝም። የአድሃሪውን ትጥቅ ለማስፈታትም ሆነ ሰፊውን ሕዝብ በህጋዊም ሆነ ከህግ ውጭ በሆኑ መንገዶች ለማስታጠቅ በጥንቃቄ መሥራት አለብን። 

–  የመሬቱን አዋጅ በሥራ ላይ ሲያውሉ የታሰሩት ዘማቾች ብቻ ሳይሆኑ፣ የገበሬ ማህበራት መሪዎች፣ የመሬት ይዞታ ሠራተኞች ፣ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችና ለሰፊው ሕዝብ የቆሙ ተራማጆችም በሙሉ መለቀቅ አለባቸው።

–  በወረዳው የሚቋቋሙት “አብዮታዊ” ኮሚቴዎች ሁሉ የመጀመሪያው የሥራ አጀንዳቸው የሚያደርጉት አንዱ ዋና ተግባር እነዚህ የትግል ጓዶችን ማስፈታት መሆን አለበት። 

–  አድሃሪ የመምሪያ ባለስልጣኖች፣ አድሃሪ አስተዳዳሪዎች፣ አድሃሪ ትእዛዞች እንዲነሱና አድሃሪ የደርግ አባላት በየክፍለ ሀገሩ የሚያደርጉት የፀረአብዮትና የጭፍጨፋ ጉዞ በአስቸኳይ እንዲቆምና እስካሁን ባደረጉት ፋሽታዊ ጭፍጨፋ (ወላሞ፣ አሚባራ፣ ድሬዳዋ፣ ሲዳሞ . . . ) ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።

–  በመጨረሻም፣ ዘመቻው በእርግጥ ለአብዮቱ ይበጅ ዘንድ የዘማቾች ብሄራዊ ጉባዔ እንዲጠራ፣ ዘማቾች እንዲደራጁ፣ የዘማቾች አጠቃላይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ያስፈልጋል። የዘማቾች የፖለቲካ ትምህርት ማግኘት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።

ዘመቻው ይለምልም።
አድሃሪዎችና አወናባጆች ይውደሙ።
Scroll to Top