ሰሕድ ቁ. 35

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 35፣    ታሕሣሥ 25፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ አሳሳችና አዘናጊ የሆነው የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጥሪ አሁንም “ዲሞክራሲያ” በተሰኘው ጋዜጣ ላይ እየተራገበ እንደሚገኝ ይጠቁማል። በዚህም መፈክር ዙሪያ ወታደራዊውን መንግሥት ለመቃወምና ለመታገል የተደራጁት ኃይሎች፣ ሰልፋቸውን ከቀድሞ መሳፍንት ከእነአስፋ ወሰንና መንገሻ ሥዩም ጋር ማድረጋቸውን ያጋልጣል። የመሳፍንታዊ ኃይሎችም በቅርቡ በበተኑት ወረቀት፤ “ሕዝቡን ከጉግ ማንጉግ ደርግ” ነጻ ለማውጣት፤ በአስቸኳይ በምርጫ የሲቪል መንግሥት እንዲቋቋም ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውሶ፣ እነዚህ መሳፍንት፣ “ሕዝባዊ መንግሥት” ሲሉ የቀድሞ የፊውዳል መንግሥታቸውን ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት እንደሆነ አያጠያይቅም ይላል። አያይዞም፣ ለኢሕአፓ “ጊዜያዊ” መንግሥት ሰፊ ምላሽ ሲሰጥ፣ የአዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮታዊ መንግሥት አንድ ወጥና ቀጣይ እንጂ “ጊዜያዊ” የሚባል መወጣጫ እርከን የለውም በማለት ያብራራል።           

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 35                                                                      ቀን 25/4/68

 

ለ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት”

ወይንስ

ለነቃ፣ ለተደራጀና ለተጠቃ የሕዝብ ትግል

የየካቲት 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችን አብዮታዊ የትግል ትጥቅ ለማስፈታት ፊውዳሊስቶችና ኢምፔሪያሊስቶች እስካሁን ድረስ ያልገለበጡት ድንጋይ፣ ያልጠነሰሱት ሴራ የለም። እነዚህን ልዩ ልዩ ሴራዎችና ተንኮሎች እያከሸፈ፣ የጭቆኖች ትግል አገሪቱን ቢያጥለቀልቅም፣ አድሃሪ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ትጥቅ ለማስፈታት፣ ወይ ደግሞ እነሱ እያሉ በሁለተኛ ደረጃ በሚታዩ ጠላቶች ላይ በማስነሳት ትግሉን ለማዳከም፣ ተራማጆችን ለመከፋፈል፣ ከማሴር አልተቆጠቡም። ነገሩ የመደቦች ትግል ነውና ባገኙት ዘዴ ሕዝቡን ለማዳከም፣ ትግሉን ለማቀዝቀዝ፣ ወይም የተሳሳተ አቅጣጫ ለመስጠት ቢሞክሩ አይገርመንም።

የኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ግን የፊውዳሊስቶችንና የነሲአይኤን ሴራ ተራ በተራ እያከሸፈ ይወጣቸዋል። ዞሮ ዞሮም በጠላቶቹ ላይ ሙሉ ድልን ይጐናፀፋል። በዚህ ትግል ውስጥም ፀረሕዝብ ኃይሎች የተራማጅ ካባ ደርበው፣ እንዲያውም አልፈው ተርፈው በገናናዎቹ በነሌኒንና በነማርክስ ስም እየማሉና እየተገዘቱ፣ ለማወናበድ ይሞክሩ ይሆናል። ግን ሃቀኛ ማርክሲሲቶች ደግሞ ሞልተዋል። ስለዚህ በአብዮት ስም አብዮቱን ለማጨናገፍ የሚሞክሩ አወናባጆችም ትግሉ እየተፋፋመ ሲሄድ እየተጋለጡ እንደሚሄዱ ግልጽ ነው።

በኢትዮጵያ ተራማጆች መሃከል መከፋፈልን ለማጠንከር፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ዋና ጠላቶቻቸውን ችላ እያሉ ባልሆነ አቅጣጫ እንዲታገሉ፣ የድላቸውን ጐዳና እየተው በሌላ በማይገኝ አቋራጭ እንዲባክኑ፣ የጨለማው ዘመን እንዲራዘም የሚፍጨረጨሩ የንኡስ ከበርቴዎች ደንፊዎች ልሳን የሆነው “ዲሞክራሲያ” የሚነዛውን መርዝ መዋጋት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘነው ለዚህ ነው። ፀረዲሞክራቲኩን የደርግ አገዛዝ እንደ ጊዜው ዋና ጠላት በመቁጠር የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝቦች የደም እንባ ሲያስለቅሷቸው የነበሩትንና አሁንም የሚያስለቅሷቸውን ፊውዳሊስቶችና ኢምፔሪያሊስቶች እኩል እንዲዋጉ የሚጋብዛቸውን የዚህን ጋዜጣ ቁጥር 23 በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 33 ተችተንበት የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ፀረዲሞክራቲኩን ደርግ እየተዋጉ፣ የሱንም ፀረዲሞክራቲክ አገዛዝ እየታገሉ፣ አመዛኝ ጉልበታቸውንና ኃይላቸውን ዋና ጠላታቸው ላይ እንደሚያውሉት፣ ማዋልም እንዳለባቸው አብራርተናል። ይህንን አዳሀሪ ጉራም እንደማንሰማ ገልፀናል።

በዚህ ቁጥራችን፣ እነዚህ በነማርክስና በነሌኒን ስም የተደባለቁንን ንዑስ ከበርቴ ደንፊዎች የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችን የትግል ትጥቅ ለማስፈታት እንደ በግ ላት አንጠልጥለው የያዙትን የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸውን ጉዳይ አንስተን እንተቻለን። አድርባዮቹ የዲሞክራሲያ አዘጋጆች፣ የልባቸውን በኤክስሬ ተመልክተን “ተራማጅነታቸውን” ካላረጋገጥን በስተቀር በዚህ ጉዳይ ጨርሰው ከአስፋወሰን – መንገሻ ሥዩም፣ ከነሲአይኤ ጋር እንደተሰለፈ እናሳያለን። ከዚህም አልፈን እንሄዳለን። አድር ባዮቹ ለዚህ ጊዜአዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጉዳይ አንድ ሙሉ ቁጥር አውለዋል። በዚህ ቁጥራቸው ላይ ሰልፋቸው ከፀረሕዝብ ኃይሎች ጋር እንዳይደለ ለማሳየት በሩሲያ አብዮት ጊዜ እነሌሊን የወሰዱት አቋም ልክ እንደኛው ነበር እያሉ ለርኩስ አላማቸው የገናናዎቹን ቦልቪሺኮች ስም ለመበከል ሞክረዋል። ስለዚህ እኛም ወደ ታሪክ ተመልሰን የዚህን አድርባዮች የትንተና ችሎታ ዜሮነትና፣ የማወናበድና የማጭበርበር ልቅነታቸውን ለአንባቢ እያሳየን እናጋልጣቸዋለን።

ዛሬ በኢትዮጵያ ይህ የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ጉዳይ ብዙ ሃቀኛ ተራማጆችን ያወናበደ ጉዳይ ነው። በዚያው ልክ ደሞ አድሃሪ ተብሎ፣ ፀረሕዝብ ተብሎ፣ አወናባጅ ተብሎ ምርጫ እንዲደረግና ፀረዲሞክራቲኩ ደርግ ተወግዶ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም የማይጠይቅ የለም።ባለፈው በህዳር ወር ከነአስፋወሰን – መንገሻ ሥዩም በስተቀኝ አለሁ የምትል አንዲት. “ፀረ ደርግ ገሽጋስ ንቅናቄ ኢትዮጵያን ከጉግማንጉግ ለማዳን” የተባለች የደንቆሮ ፊውዳሊስቶች ንቅናቄ በበተነችው ወረቀት ላይ ጉግማንጉግ ደርግ ተወግዶ ሕዝቡ በሚመርጣቸው ሲቪሎች እንዲተዳደር ትጠይቃለች። ይህ ጥያቄ ግን የሷ ብቻ አይደለም።

“አንድ የእድገት ደረጃ እንደተደረሰ፣ የቀድሞው ሥርዓት መዋቅር ፋይዳቢስነት ለሁሉም ግልጽ ይሆናል። ሁሉም አብዮት ይላል። በዚህ ጊዜ ያለው ተግባር ይህንን አዲስ መዋቅር የትኞቹ መደቦች እንደሚገነቡትና እንዴት እንደሚገነቡት መግለጥ ነው። ይህ ካልተደረገ፣ “አብዮት” የሚለው መፈክር በአሁኑ ጊዜ ትርጉም አይኖረውም።” /ሌኒን ቮል.9 ገጽ 128/

ዛሬም በአገራችን ይኸው ነው። የዚህን ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የመደብ ይዘት በደንብ መግለጥ ያስፈልጋል። እንዴት እንደሚመጣም መግለጥ ያስፈልጋል። ይህ በትክክል ካልተደረገ፣ ማንም ተራማጅ ነኝ የሚል ሰው አውቆም ሆነ ሳያውቅ፣ ከአድሃሪዎች ጋር መሰለፉ ግልጽ ነው።

በባሪያ ዘመን “ሕዝብ” የሚለው ፊሊጥ የሚያመለክተው የባርያ ገዥዎችን መደብ ነበር። በዚያን ጊዜ ለምሳሌ ግሪኮች ያቋቁሙ የነበረው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት “ሕዝባዊ” ነኝ ቢልም የመምረጥና የመመረጥ መብት የነበራቸው ባርያ ገዥዎች ነበሩ። በፊውዳሉ ሥርዓት እነአፄ ኃይለሥላሴ “ሕዝብ” ሲሉ የመሳፍንቱንና የባላባቱን መደብ አባሎች ለመጥቀም ነበር። ዛሬም እነአስፋወሰን ሕዝባዊ መንግሥት ሲሉ፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ፣ የፊውዳሉን መደብ አባሎች ነው። በከበርቴ ሥርዓት ሕዝባዊ መንግሥት ሲባል “ሕዝብ” ተብሎ የሚቆጠረው የከበርቴው መደብ ነው። በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ባለዉ አዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮት ደግሞ ሕዝባዊ መንግሥት ሲባል፣ ሕዝብ የሚለው ክልል ውስጥ ወዝአደሩ፣ አርሶበሌው፣ ንኡስ ከበርቴውና ሌሎችም ፀረፊውዳል፣ ፀረኢምፔሪያሊስት የሆኑ ኃይሎች ሁሉ ይጠቀለላሉ። በተራማጅ ስም የሚፎልሉ የዲሞክራሲያ አድርባዩች በያዝነው ዘመን እውነተኛው ሕዝባዊ መንግሥት የመደብ ይዘቱ እንዲህ መሆኑን አይስቱትም። ስለዚህ እነዚህ መደቦች ተደራጅተውና ታጥቀው ጠላቶቻቸውን ሳይደመስሱ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ተመርጠን እናቋቁማለን ሲሉ፣ ለጊዜው የተደራጀው ንኡስ ከበርቴ መደብ ብቻውን ስልጣን ይያዝ ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። በንኡስ ከበርቴ ደንፊዎች በኩል እንግዲህ ይህ መፈክር ሲወረወር “ግፋ ቢል” ንኡስ ከበርቴው “ለጊዜው” የኢትዮጵያ “ሕዝብ” እኔ ልሁን ብሎ ለማቋቋም የሚታገለው የንኡስ ከበርቴ አምባገነንነት የሚፀድቅበት መንግሥት ነው ማለት ነው። ይኸ ደግሞ ቢበዛ “የጊዜያዊ” ሕዝብ መንግሥት ይባል እንደሆነ እንጂ የአዲሱ ዲሞክራቲክ አብዮት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የሚባልበት ምንም ፈሊጥ የለም።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ተራማጆች የሚታገሉለት ሕዝባዊ መንግሥት በመደብ ይዘቱ የሰፊው ሕዝብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ነው። በአመጣጡ ደግሞ፣ “በዲሞክራሲያዊ ምርጫ” ሳይሆን ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን የሚደመስስ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝብ አብዮታዊ አመጽን ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ተጋድሎ የሚመጣውን ፈተናና ችግር ተወጥቶ አልፎ የሚሄድበት ጐዳና፣ በአድሃሪ ኃይሎች ላይ ወሳኝ ድልን ተጐናጽፎ የሚጓዝበት ጐዳና ይህ ብቻ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ይምጣ የሚባለው መንግሥት “ሕዝባዊ መንግሥት” እንደሆነ “ፀረጉግማንጉጓ” ገስጋሽ ንቅናቄ ትስማማለች፤ አስፋወሰን/መንገሻም ይስማማሉ፤ የነሲአይኤ ፍጡሮች የሆኑት እነ “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረትም” ይስማማሉ፤ እነዲሞክራሲያም ይስማማሉ። ሃቀኛ ተራማጆች ትግላቸው ትንንቃቸው ለዚሁ ለሕዝባዊ መንግሥት ነው። ነገር ግን ሃቀኛ ተራማጆች ይህ ሕዝባዊ መንግሥት ሊመጣ የሚቻልበትን አብዮታዊ የትጥቅ ትግል ጐዳና ለጭቁኖች ሳይታክቱ እያሳዩ መራራ ትግላቸውን ያካሂዳሉ። ከፀረጉግማጉግ ንቅናቄ አንስተን “ወደግራ” እየተጓዝን እስከ ንኡስ ከበርቴ ደንፊዋ እስከ ዲሞክራሲያ ድረስ ያለዉ የፀረሕዝብና የፀረአብዮት ጥርቃሞ ደግሞ ለማወናበድና ሁሉም የበኩሉን የመደቡን የፀረሕዝብ አምባገነን አገዛዝ ለማንገስ የሚሞክረው ይህንን አብዮታዊ ጐዳና እያጭበረበረ ነው።

ዛሬ ይህ የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መፈክር ይህንን አብዮታዊ የትግል ጐዳና ለማመልከት እስካልተገደዱ ድረስ የሕዝቡን ትጥቅ ለማስፈታትና አብዮቱን ለመቀልበስ የሚዘጋጁ የጥፋት ኃይሎች ሁሉ የሚቀበሉትና የሚታገሉለት መፈክር ነው።

ሁሉም ይህንን መንግሥት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እናመጣዋለን ይላሉ። ሁሉም የትግሉን መገፋት፣ የሕዝቡን መደራጀትና መታጠቅ አጥብቀው ይፈራሉ። እነአፋውሰን- መንገሻ ሥዩም ይህንን አፍረጥርጠው ይናገራሉ። የመንገሻ ሥዩም የማርች 30 1974 መግለጫ “ስልጣን ከምርጫ ሳጥን እንጂ ከጠመንጃ አፈሙዝ መውጣት የለበትም”  ያለው ይህንኑ የሕዝቡን መታጠቅ የሚፈራ መደባዊ አቋሙን ሲያስተጋባ ነው። የዲሞክራሲያ አድርባዩችም የትጥቁን ነገር ለማምለጥ የሚሞክሩት እሱን ችላ በማለትና የምርጫውን ነገር አጥብቀው በመያዝ ነው።

የነሲአይኤና የነአስፋውን የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መፈክር ሌላ አላማው ነገሩ አለቅጥ ሳይዘገይ ሕዝቡ ትጥቁን ፈትቶ ወደምርጫ እንዲሄድ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ሕዝቡ በንቃቱ፣ በድርጅቱ፣ በትጥቁ እየገፋ ከሄደና እነሱ ተደቁሰው ካለቁ በኋላ ምርጫ ቢደረግ እውነትም ሕዝባዊ ምርጫ እንደሚሆን ያውቃሉ። ስለዚህ አላማቸው ትግሉ ሳይገፋ ለማቀዝቀዝ ነው። ይህ ትግሉ ይብረድ የሚለው ቅዥታቸው ራሱ ለመንግሥታቸው በሚሰጡት ስም ላይ ተለጥፎ ያጋልጣቸዋል። የመንገሻ ሥዩም የማርች 30 መግለጫ ይህንን ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥቱን “የብሄራዊ እርቅና የሃገር መገንባት ዲሞክራሲያዊ መንግሥት” /ዲሞክራቲክ ገቨርንመንት ኦፍ ናሽናል ሪኮንስትራክሽን ኤንድ ሪኮንሲሊዩሽን/ ይለዋል። መልእክቱ ግልጽ ነው። ትግሉን ተውት፣ እንታረቅ፣ ነው የሚለው። የዲሞክራሲያ አድርባይ ምሁራንም በወፍ ቋንቋ አድበስብሰው ያቅርቡት እንጂ ከአቀራረባቸው የሕዝቡ ትግል እንኳ መታጠቁን ይቅርና በወጉ ስር ሰድዶ መደራጀቱን ይፈራሉ። በምርጫ ተውጣጥቶ ይቁም የሚሉት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የሚውጣጣው “አሁን ካሉት፣ ከፈረሱትና፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊቋቋሙ ከሚችሉት ሕዝባዊ ድርጅቶችና . . . ፖርቲዎች” ነው ብለው እንመራረጥ ነው የሚሉት። ከእንዲያውም እስቲ ወደዚህ ወደጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥታቸው አመጣጥ ጉዳይ ጠለቅ ብለን እንግባ።

መጀመሪያ ነገር የአድርባዮቹ ውዥንብር የሚጀምረው ገና “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለው ቃል ላይ ነው። እነሌኒን “ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት” ሲሉና አድርባዮች “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ሲሉ በአብዮትና በፀረአብዮት፣ በብርሃንና በጨለማ፣ በጥራትና በውዥንብር መሃከል ያለው ልዩነት እንዳለ መመልከት ያስፈልጋል። “ሕዝባዊ” መንግሥት የሚባለው መላው ሕዝብ ተሳትፎበት ከተካሄደ ነፃ፣ ምስጢርና ቀጥታ ከሆነ ጠቅላላ ምርጫ የሚወጣ መንግሥት ለማለት ነው። የሚገዛውም በፀደቁ፣ ባሉ፣ ሁሉ በሚያውቃቸው ህግጋትና የስልጣን ክፍፍሎች ላይ የተመረኮዘ የተረጋጋ መንግሥት ለመጠቆም ነው። አብዮታዊ መንግሥት ግን በጠቅላላ ምርጫ ሳይሆን፣ በአብዮታዊ ትግል በደመሰሰው መንግሥት ተተክቶ፣ በቆዩና በተደነገጉ በተረጋጉ ህግጋትና የስልጣን ክፍፍሎች ላይ ሳይሆን ለትግሉ መግፋትና ለፀረአብዮት ኃይሎች መደምሰስ አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች ሁሉ እየወሰደ፣ አዲስ ሥርዓት መልክ ባለው ሁኔታ እስካቋቋመ ድረስ የሚሰራ የመሸጋገሪያ መንግሥት ነው። እንዲህ አይነቱ ስልጣን በአብዮቱ አፍላ ጊዜ የሚቋቋምና በሌኒን አነጋገር “ምንም ሌላ ስልጣን የማያውቅ፣ ያወጣ ባለስልጣን ቢያወጣቸው ምንም ህግጋት፣ ምንም ደንቦችና ወጐች የማያዙት፣ ወሰን የሌለው፣ ከህግ ውጭ የሆነና በቀጥታ በኃይል ላይ የተመሰረተ” መንግሥት ማለት ነው።

እንዲያውም እነሌኒን እንዲህ አይነቱን “ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት” የጠየቁት ዝቅ ብለን እንደምናየው፣ አንዱ አላማው ጠቅላላ መርጫው በመላው ሕዝብ፣ በቀጥታ በሙሉ ነፃነትና በምስጢር ለማስደረግና ሕዝባዊ ሬፐብሊክን የሚያቋቁም ባለሙሉ ስልጣን የእንደራሴዎች ሸንጐ ለማስመረጥ ነው። በነሌኒን እምነት ይህ ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ሊቋቋምና ነፃ ምርጫውን ሊያካሂድ የሚችለው በፀረሕዝብ ኃይሎች ላይ የተሳካ ሕዝባዊ አመጽ አድርጐ ስልጣን ሲጨብጥ ብቻ ነው። ጀግኖቹ የቪየትናም አርበኞች በትግል ውስጥ ባሉበት ጊዜ ብዙ ግዛቶችን ከቁጥራቸው ስር ካደረጉ በኋላ በምርጫ ሳይሆን በአብዮታዊ አመፃቸው ላይ ተመርኩዘው ያቋቋሙት መንግሥት ጊዜያዊ አብዮታዊ እንጂ ጊዜያዊ ሕዝባዊ ያልተባለው ለዚህ ነው።

እንግዲህ አንድ ሕዝባዊ መንግሥት ጊዜያዊ ይባላል ቋሚ ከመላው ሕዝብ ምርጫ የሚፈልቅ መንግሥት ነው። አብዮቱ ተሳክቶ ፀረሕዝብ ኃይሎች ተደምስሰው፣ ወይም ከቁጥጥር ስር ውለው ነፃ ምርጫ ተደረገ አንበል። ይህ ከሆነ ከዚህ ነፃ ምርጫ የሚወጣው መንግሥት በርግጥም ሕዝባዊ የሆነ መንግሥት ለምን ጊዜያዊ እንደሚባል ጨርሶ ምስጢረስላሴ ይሆንብናል። በሌላ በኩል ደግሞ ፀረአብዮት ኃይሎች አይለው ሕዝቡ በሙሉ ነፃነት ምርጫውን እንዲያካሂድ ከከለከሉት፣ ወይም አድሃሪ ተጽኗቸውን ካሳደሩበት ይህ “ጊዜያዊ” ጉድ በምን ፈሊጥ “ሕዝባዊ” ሊባል እንደሚችል አሁንም ከምስጢረስላሴ የረቀቀ ምስጢር ይሆንብናል። ባጭሩ አድርባዩቹ እናመጣዋለን የሚሉት መንግሥት በርግፅ ሕዝባዊ ከሆነ ጊዜያዊ መሆኑ አይታየንም። “ሕዝባዊ” ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በትግላቸው ገፍተው ነፃ ይወጣሉ እንጂ “ለጊዜውም” ቢሆን የምትጭኑባቸውን ባርነት አይቀበሉም። “ጊዜያዊ” እና “ሕዝባዊ” አንድ ላይ የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም። እሳትና ጭድ ናቸው። ብቻ ገና ስንት የተደገሰለትን አንባቢ በእንደዚህ አይነቱ “ፀጉር መሰንጠቅ” አናድክመውና ወደሌላ እንቀጥል።

የዲሞክራሲያ አዘጋጆች በዚሁ ጉዳይ ላይ ከነአስፋው ወሰንና ከነመንገሻ ስዩም ጋር ቆመው ሲያራግቡ የሚያዙት ስለዚህ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥታቸው” መተቸት ሲጀምሩ ነው። በነሱ ግምት የዚህ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” አመጣጥና ቅደም ተከተል እንደሚከተለው ነው።

– “ ለሃቀኛ አብዮታውያን የትግል መሳሪያ የሆኑት የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የመደራጀት ሰብአዊ መብቶች ያለምንም ገደብ መልቀቅ፣

– አሁን ካሉት፣ ከፈረሱትና በአጭር ጊዜ ለመቋቋም ከሚችሉት ሕዝባዊ ድርጅቶችና (የገበሬ ማህበራት፣የንኡስ ከበርቴ የሙያ ማህበራት፣የሴቶች ማህበራት፣ የሠራተኛ ማህበራት፣ የመመህራን ማህበራት፣ ሰፊው ወታደር … ) ፖርቲዎች በምርጫ የሚውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ ሸንጐ ማቋቋም፣

– በዚህም ጊዜያዊ ሕዝባዊ ሸንጎ የሚመረጥ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መመስረት ያስፈልጋል።”

ለምን እንደዚህ በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች እንባና መከራ ታላግጣላችሁ? አሁን ማን ይሙት የኢትዮጵያ ጭቁኖች “በነፃ” ስለተናገሩ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ስላደረጉ . . . ብቻ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በንግግርና በሰላማዊ ሰልፍ ብርታት ተንኮታኩተው ይወድቁ መስሏችሁ ይሆን? የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥያቄ በዚህ ብቻ እስከወሰናችሁት ድረስ እነሲአይኤም አብረዋችሁ ይሰለፋሉ። ይህንንማ እነአስፋወሰን- መንገሻ እስከነስሙ “የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት” ብለው በሰየሙት ድርጅታቸው ኘሮግራም ላይ በሙሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ “ጠይቀውለታል”። ነገር ግን የኢትዮጲያ ጭቁኖች በነዚህ መብቶች ላይ በተጨማሪ፣ የነአስፋውወሰን- መንገሻን፣ የኢምፔሪያሊስቶችን አመፅ ለመመከት፣ በገዛ ሀገራቸው በሰላም ለመስራትና ለመኖር እንዲችሉ ከታወጀባቸው የርስ በርስ ጦርነት በድል አድራጊነት ለመውጣት የመታጠቅ መብታቸው ይጠይቃሉ። ይህማ ከሌላ ያየነው ነው። ሚሊዮን የመናገር መብት ቢኖራቸውም፣ ባዶ እጃቸውን እንከሆኑ ድረስ የታጠቀ አድሀሪ አያናግራቸውም። ሚሊዮን የመደራጀት መብት ቢታወቅላቸው የታጠቀ አድሀሪ ይበትናቸዋል። ዛሬ አብዮታዊ ዘማቾች በጥይት እየተቆሉ፣ በእሳት እየተጠበሱ መስዋትነትን ተጋፍጠው በመታገል ላይ ናቸው። ድሀ ገበሬዎችና የመሬት ይዞታ ሠራተኞች የአድሀሪዎች ጥይት ራት እየሆኑ በመተናነቅ ላይ ናቸው። ይህ ሁሉ የሚወርድባቸው የአድሃሪዎች አመጽ እስከዚህም የመደራጀት መብት በመነፈጉ ሳይሆን፣ በፀረዲሞክራቲኩ የደርግ አገዛዝ የመታጠቅ መብቱን በመነፈጉ ነው። ይህ አልገባችሁ እንደሆነ ስለኢትዮጵያ አብዮት የገባችሁ ሳንቲም ነገር የለም ማለት ነው።

አድርባዮቹ የጭቁን ሕዝቦችን መታጠቅ በጣም ይፈራሉ። ስለዚህ ይህንን ሳያነሱ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸው እንዴት ሊቋቋም እንደሚችል ለመጠቆም ሲሞክሩ ጨርሰው ትርምስ ውስጥ ነው የሚገቡት።

በመጀመሪያ ነገር ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸውን ከነሌኒን ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ጋር የግድ ለማዛመድ ቢሞክሩም የአድርባዩቹ መንግሥት አቋቋም ቅደም ተከተል ሲታይ ከአብዮታዊ ጊዜያዊ መንግሥት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ግልጽ ይሆናል። እንደዲሞክራሲያ አባባል ከሆነ በመጀመሪያ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ ሸንጐ “ከምርጫ ይውጣጣና ከዚያ በኋላ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይመረጣል። በጣም ጥሩ! የነሌኒን ደግሞ የተገላቢጦሽ ነው! የእነሱ ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ከምርጫ ተውጣጥቶ ሳይሆን ከተሳካ ሕዝባዊ አመጽ ይወለዳል። ከዚህ በኋላ ጠቅላላው ሕዝብ ነፃ፣ ቀጥታና ምስጢር በሆነ ምርጫ ተሳትፎ ሕዝባዊ የመማክርት ሸንጐ ያቋቁማል። ይህ ባለሙሉ ስልጣን የሆነ የሕዝብ እንደራሲዎች ሸንጐ ሕዝባዊ መንግሥት ያቋቁማል።

የትጥቅን ነገር ፈጽሞ አረሳስታችሁ፣ በምርጫ እናመጣዋለን የምትሉት የመንግሥት እንኳን ከነሌኒን አብዮታዊ መንግሥት ጋር አንድ ሊሆን ይቅርና የሱ ተቃራኒ እንደሆነ ግልጽ ነው። አድርባዩቹ ግን ይህን አድሃሪ መፈክራቸውን በገናናዎቹ በነሌኒን ስም ሸፋፍነው ለማሳለፍ “የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን ጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ታሪካዊ ሃቆች አሉን(?)” በሚል አርእስት ስር የሩስያን ቦልሼቪኮች ታሪክ ምሳሌነት እየጠሩ ይተነተናሉ። የዲሞክራሲያን ቁጥር 24 ይህንን የመጨረሻ ክፍል ስናይ ለኢትዮጵያ ተራማጆች ገና ለረጅም ጊዜ ሲያሳፍረን የሚኖረውን የክርክርና የአጠቃቀስ ዘዴ ታዝበን አዘን። ይህንን ዝቅ ብለን እንመጣበታለን።

በዚህ በጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቦልሼቪኮችና በሜንሼቪኮች መሃከል ብዙ ሌሎች ልዩነቶች ነበሩ። በጠቅላላው ግን የልዩነታቸው መሰረት እነሌሊንና አድርባዩቹ ስለጠቅላላው የሩስያ አብዮት የተለያየ አስተሳሰብ ስለነበራቸው ነው። በ1905 ዓ.ም. የንጉሱ አገዛዝ በሕዝብ ትግል ተወጥሮ ተይዞ ሳለ እየተጋጋለ የሚሄደው አብዮት እንዴት እንደሚገፉ በተደረገው ውይይት ሁለቱ ቡድኖች የተለያየ ታክቲክ ለመከተል ወሰኑ።

እነሌኒን ይህ አብዮት፣ ምንም እንኳን የከበርቴ አብዮት ቢሆን ቅሉ፣ ከበርቴው እጅግ ወላዋይ በመሆኑ ከንጉሱ ጋር ተዋውሎ አንድ አይነት ቅይጥ መንግሥት ያመጣ እንደሆነ እንጂ፣ በእርግጥ ዲሞክራሲያዊ ሬፕብሊክን ሊያመጣ አይችልም። ይህንን ዲሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ ለማምጣት የሚችለው ወዝአደሩ ከአርሶአደሩ ጋር ተባብሮ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ዲሞክራሲያዊ የወዝአደርና የገበሬ መንግሥት ለመመስረት በመሪነት ሲታገል ነው እያሉ ይከራከሩ ነበር። ይህንንም የወዝአደርና አርሶአደር አምባገነን መንግሥት፣ ይህንን ዲሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ ለማቋቋም አንድ ባለሙሉ ስልጣን የሆነ የሕዝብ እንደራሴዎች ሸንጐ ማስመረጥ ያስፈልጋል። ይህ ሸንጐ በርግጥ ባለሙሉ ስልጣን እንዲሆን፣ በርግጥ የሕዝብ እንደራሴዎች ሸንጐ እንዲሆን ከተፈለገ ይህንን ምርጫ ሊያካሄድ የሚችለው በተሳካ ሕዝባዊ አመጽ አድሃሪዎችን ደምስሶ የሚቋቋም ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እነሌኒን ደግመው ደጋግመው ያስረዱ ነበር።

አድርባዮቹ ሜንሼቪኮችስ? ሜንሼቪኮች ይህ አብዮት የከበርቴ አብዮት እንደመሆኑ መጠን ሊመራው የሚችለው ለዘብተኛው /ሊበራሉ/ ከበርቴ እንጂ ወዝአደሩ እመራለሁ ብሎ ከበርቴውን ማስደንገጥ የለበትም ይሉ ነበር። ከዚህም አልፎ ተርፎ ወዝአደሩ ከገበሬው ጋር አንድነቱን ማጠንከሩን ትቶ ትብብሩን ከዚህ ከለዘብተኛው ከበርቴ ጋር ያድርግና ንጉሱን ለመጣል በሚያደርገው ትግል ይርዳው ይሉ ነበር።

ከበርቴው “ተደናግጦ አብዮቱን እንዳይተወው” ወዝአደሩ የዚህን መንግሥት እንኳን አመራሩን ይቅርና ተሳትፎ እንኳን መጠየቅ የለበትም የሚል አቋም ነበራቸው። የንጉሱን አገዛዝም ለመደምሰስ እንግዲህ እነሌኒን የትጥቅ ትግልና እሱ ሲሳካ ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት፣ ከዚያም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሲሉ አድርባዩቹ ወይ የተሳካ ሕዝባዊ አመጽ ተደርጐ ወይም ደግሞ ሕዝቡ የእንደራሴዎች ሸንጐ እንዲጠራ አስጨንቆ ይዞ ምርጫ እንዲደረግ ቢያስወስን ወሳኝ የሆነ ድል /ዲሳይሲቨ ቪክትሪ/ ይገኛል ብለው ይቃዡ ነበር።

ሌኒን ይህ ድል ሊገኝ የሚችለው ከተሳካ ሕዝባዊ አመጽ ብቻ ሊወጣ በሚችለው ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ብቻ እንደሆነና ፀረሕዝብ ኃይሎች ሳይደመሰሱ ወይም ሳይዳከሙ ምርጫ ቢደረግ በምንም አይነት እንደድል ሊቆጠር እንደማይችል ሲያስረዳ የሶስተኛውን የፖርቲውን ጉባዔ ውሳኔ እየተቸ እንዲህ ይላል።

 “የጉባዔው ውሳኔ እንደሚያመለክተው የቅስቀሳ ሙሉ ነፃነትን አረጋግጦ፣ በእውነት ይህ የሕዝቡን ፍላጐት ለማንፀባረቅ የሚችል ባለሙሉ ስልጣን የእንደራሴዎች ሸንጐ ለማስመረጥ የሚችለው፣ የተሳካ ሕዝባዊ አመጽ መሳሪያ የሆነው ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ብቻ ነው። ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነው ወይ? እቃወማለሁ የሚል ካለ የንጉሱ መንግሥት ለአድሃሪዎች እጁን ላይዘረጋ ይችላል፣ በምርጫው ውስጥ ገለልተኛ መሆን ይችላል፣ ሕዝቡ በእውነት ፍላጐቱን እንዲገልጽ ይፈልጋል ብሎ መከራከር ይኖርበታል። እነዚህ አስተሳሰቦች እጅግ አስቂኝ ከመሆናቸው የተነሳ (አድርባዩች አዳምጡት ሌኒንን! ሰ. ህ. ድ.) ማንም ቢሆን በግልጽ ሊቆምላቸው አይችልም።”

በነገራችን ላይ አድርባዩቹ (የኛን ማለታችን ነው) ይህ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸው ምን አይነት ድል እንደሆነ ራሳቸው እርግጠኛ አይደሉም። ስለዚህ መንግሥት ምንነት ብዙ ከተናገሩ በኋላ ገጽ 5 ላይ ይህ የፊውዳሊስቶቹና የነሲአይኤ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት በምርጫ ተውጣጥቶ ቢቋቋምም የተገኘው የውሸት ድል ፀረሕዝብ ድል እንጂ ሌላ ምንም ነገር እንዳይደለ ሲያምኑልን ይህ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት “ወደሃቀኛ ሕዝባዊ ድልም የሚመራ የትግል መሳሪያም ነው” ብለው ቁጭ ይላሉ። ብቻ ይህንን እንተወውና ወደሌላው “ትንተናቸው” ገብተን እንዳክር።

እንግዲህ የነሌኒንና የነሜንሼቪኮች ልዩነት ባጭሩ በነዚህ ነጥቦች ላይ ነበር። ከላይ ስንጽፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የኛ አድርባዩች እነሌኒንም አንደኛው በምርጫ የተውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ነበር የሚጠይቁት፣ እኛ በተነሳው ክርክር በቦልቬቪኮች በኩል ነበርን፣ ታሪክ ይደግፈናል ለማለት ያቀረቡትን ጥቅስና የሰሩትን ማጭበርበር ስናይ ለኢትዮጵያ ተራማጆች አፈርን ብለን [የአዘጋጆች እርማት] ነበር። ለአንባቢም ጉዱን እናሳየውና ሃፍረት አይሰማው እንደሁ እንይ።

ስለአብዮታዊ አመጽ፣ ስለሚቋቋመው የመንግሥት አይነት (የመደብ ይዘት)፣ ስለ ነበሩት ልዩነቶች ሳንቲም ሳያወሩ፣ ቃል ሳይተነፍሱ “በዛሩ መንግሥት ቦታ ስለሚቋቋመው/!?/ ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ላብአደሩም ስለሚኖረው ተሳትፎ ማርክሲስቶቹ ቦልሼቪኮችና አድርባዩቹ ማንሼሺኮች የተለያዩ አቋሞች ወስደው ነበር” ይሉናል። አንኳን የልዩነቱን ታሪክ በሚገባ የሚያውቅ ሰው ይቅርና ከላይ የሰጠነውን ትንተና የተመለከተ አንባቢ “እንዴት በዚህ ብቻ ነው ልዩነቱ?” ብሎ መገረም ይጀምራል። ከዚያ “የቦልቬቪኮቹ መሪ የነበረው ሌኒን፣ ሁኔታውን እንደሚቀጥለው በመመልከት” ይሉና ሌኒንን የጠቀሱ መስለው እንደሚከተለው ይጽፋሉ

​“. . . የሚቋቋመው ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት ተግባር የአብዮቱን ድል ማጠናከር፣ ፀረአብዮታዊ እንቅስቃሴውን መደምሰስና የሶሻልዲሞክራቲኩን ሌበር ፖርቲ ዝቅተኛ ኘሮግራም በሥራ ላይ ማዋል ይሆናል። እነዚህ ተግባራት ካልተከናወኑ በስተቀር በዛሩ ላይ የተሟላ ድል ሊገኝ አይችልም። እነዚህን ተግባራት በሥራ ለማዋልና በዛሬ ላይ ሙሉ ድል ለመቀዳጀት ደግሞ ጊዜያዊው አብዮታዊ መንግሥት እንደማንኛውም ተራ አይነት መንግሥት ሳይሆን የላብአደሩና የአፈርገፊው አምባገነን መንግሥት መሆን አለበት።. . . . . ላብአደሩ በጊዜያዊው አብዮታዊ መንግሥት ተሳትፎ አብዮቱን መመራት አለበት። አ. . . ”

አንድ የመጀመሪያ ነገር። እዚህ ላይ አድርባዩች ሌኒንን አሳይተው የሚጠቅሱት ስታሊንን ነው። ሌኒን እነዚህን አሳቦች አልሰነዘረም ለማለት አይደለም እዚህ ላይ ፀጉር እንሰንጥቅ የምንለው። አድርባዩቹ ነገሩ እንዲህ በመጐማመዱ አንባቢ ድንገት ግራ ተጋብቶ እስኪ ላጣራ ቢል እንዳይጋለጡ አስበው ነው።ይህንን የጠቀሱት ከሰታሊን “ሂስትሪ ኦፍ ኮሙኒስት ፖርቲ ኦፍ ሶቨየት ዩኒየን” ከተባለው መጽሃፍ ገጽ 64 እንደሆነ ይሸሸጉን። ይብላን ለአወናባጆች እኛስ ደረስንበት!!

የነሌኒንን ጊዜያዊ መንግሥት አድርባያቹ እናቋቁም ከሚሉት፣ በምርጫ አውጣጥተን እናምጣ ከሚሉት መንግሥት ጋር አንድ ለማስመሰል የሚቻልበት ጥቅስ አይደለም። የነሌኒን የነስታሊንን አስተሳሰብ አረፍተ ነገሮችን እየጐመዱ ለማጣመም ካልተሞከረ በስተቀር ቃላትን ሳይቀር ከጀመሩ በኋላ እየተደናገጡ እርግፍ አድርጐ ካልተተወ በስተቀር። የጠቀሱት ጥቅስ ላይ “የሚቋቋመው ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት” ከሚለው አረፍተነገር በፊት ሌላ የሸሸጉን አረፍተነገር አለ። እሱም የሚለው እንደሚከተለው ነው።

“ሌኒን ከተሳካ ሕዝባዊ አመጽ በኋላ የዛሩ መንግሥት በጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት መተካት አለበት እያለ ይከራከር ነበር። የሚቋቋመው ጊዜያዊ አብዮታዊ መንግሥት . . .”

እያለ ነው ስታሊን የሚቀጥለው። ከዚያ አድርባዩቹ “ይህ መንግሥት . . . የላብአደሩና የአፈርገፊው አምባገነን መንግሥት መሆን አለበት”… ብለው አረፍተ ነገሩ ሳያልቅ ጨለማ ውስጥ ጥለው ሲለዩን ስታሊን  “የወዝአደሩና  የአርሶአደሩ አብዮታዊ ፈላጭ አገዛዝ መሆን አለበት” ብሎ እቅጩን ይነግረናል።

አድርባዩቹ ከዚህ አልፈው “ወደ ተሳትፎ” ጥቅሳቸው የሚሄዱት ገጽ ዘለው ነው። ግን ስታሊን ስለዚህ መንግሥት አምባገነንነትንና አብዮታዊነት ምን አውርቶ ነው አወናባጆቹ ነጥብ ነጥብ አድርገው ያለፉት? ያቺ “እ . . .” ብለው የጀመሯት ቃል ምን ትሆን? ይቺን ለመረዳትና አንባቢ በነዚህ አደርባዩች አንጀቱ እንዲቆርጥ ስታሊን ከዚህ አስከትሎ የዚህን በዛሩ ላይ የሚገኝ የተሟላ ድል ይዞት የዚህን ጊዜያዊ መንግሥት አብዮታዊነት ለማስረዳት ይጠቅሰውና ይህ አድርባዮቹ ሊያዘልሉን የፈለጉትን ከጦር የሚፈሩትን የትጥቅ ጉዳይ ቁልጭ አድርጐ ያመጣላቸውና ጨርሶ ያጋልጣቸዋል። በኛ ግምት “እ . . ” ብለው የጀመሩት፣ ተጐርዳ የቀረችው ጥቅስ እነሆ፡-

“እንደዚህ አይነቱ ድል ደግሞ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እንጂ ሌላ አይደለም። ይህም ማለት የግድ በጦር ኃይል ላይ፣ በሰፊው ሕዝብ መታጠቅ ላይ የሚመረኮዝ አገዛዝ እንጂ በዚህ ወይም በዚያ አይነት በህግ በታወቁ፣ በሰላማዊ መንገድ በተቋቋሙ ድርጅቶች /ኢንስቲቱሽንስ/ ላይ የሚመረኮዝ አገዛዝ አይደለም። የግድ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መሆን አለበት። ምክንያቱም ለወዝአደሩ፣ ለአርሶአደሩ በአስቸኳይና በግድ የሚያስፈልጓቸው ለውጦች የመሬት ከበርቴዎች፣ የከፍተኛ ቡርዥዋ መደብና የንጉሳዊው አገዛዝ ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል።”

ግልጽ ነው። ወንድሞቻችን የቆሙላት “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” እነሱ ለእንደሚሉት “በታሪካዊ ሃቅ” አልተደገፈችም። “ታሪካዊ ሃቅ” የሚመሰከረው ጉዳይ ቢኖር

1ኛ/ ወንድሞቻችን ከቦልሼቪኮች ጋር እንዳልሆኑ፣

2ኛ/ ሜንሼሺኮች እንኳን ከአቅማቸው አጥብቀው አይያዙት እንጂ የትጥቁን ጉዳይ አልፎ አልፎ ጠይቀዋል።

ነገር ግን ድል የሚገኘው “ወይ በትጥቅ ትግል ወይ በምርጫ” በሚለው ፈሊጣቸው “በወዝአደሩ ህሊና ውዥንብር ይነዛሉ” ብሎ ሌኒን ተቃውሟቸው ነበር። በዲሞክራሲያ አስተሳሰብ ግን ምንም ውዥንብር የለም። የድል ጐዳና ብላችሁ የምታሳዩት የቅድመ-አብዮት ሩስያ ለዘብተኛ ከበርቴን የምርጫ መንገድ ብቻ፣ የነአስፋውወሰን/መንገሻን የምርጫ መንገድ ብቻ ስለሆነ አስተሳሰባችሁ አድሃሪ ጥራት አለው። እንደዚህም በመሆኑ የዴሞክራሲያ አዘጋጆች ሚልዮን ጊዜ ተንጠራሩ እንጂ አሰላለፋቸሁ እንኳን ከቦልሼቪኮች ጋር ሊሆን ይቅርና ከሩሲያ ሜንሼቪኮች በስተቀኝ እንደነበረና በዚያን ጊዜ እንደእናንተው የትጥቁን ጉዳይ ሳያነሱ ምርጫ ይደረግ ከሚሉት ከሩሲያ መሳፍንት ጎን እንደሆነ ግልፅ ነው።

“የለም ቆይ! የኛ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ከምርጫ የተውጣጣ ነው አልን እንጂ የነ አሰፋወሰን/መንገሻ መንግሥት አይደለም። እንዲያውም እነሱን የሚቃወም እነሱም የሚቃወሙት መንግሥት ነው!” እያሉ አድርባዮች ከወንበራቸው ብድግ ሲሉ ይታዩናል። መውጫ ቀዳዳ የተገኘ መስሏቸው ይችው ዲሞክራሲያ ቁጥር 24 “የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ተቃዋሚዎች እነማን ናቸው”

በሚል የተተቸውን ጠቁመው ለማምለጥ ይሞክራሉ። እውነትም ለጠላት ስም የሚሰጠውን ዝርዝር የተመለከተና፣ ያስጨበጡትን የምርጫ ተስፋ የሙጥኝ ብሎ ያነቀ የዋህ ይህንን ሊሲት ሲመለከት ጨርሶ ሊደናገጥ ይችላል። አብዮታዊያን ግን ይህንን ሊስት ሲመለከቱ የዲሞክራሲያን አዘጋጆችና የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸውን ማንነትና፣ በሊበራል ከበርቴ ቅዠት ተወጦ የሚዋዥቀውን የፖለቲካ መስመራቸውን ኪሳራ ጥልቀት ከመቸውም ይበልጥ ይረዱና ይቆርጥላቸዋል። እንደ ዲሞክራሲያ አባባል፡-

​  “የዚህ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ተቋዋሚዎች እነማን ናቸው?

“በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስልጣን የጠማውና በሕዝቡ ብሶትና ጭንቀት ተንሰራፍቶ ለመቆየት የሚፍጨረጨረው የምርጥ መኮንኖች መንግሥት የዚህ ጊዜያዊ ሕዝባዊ  መንግሥት አይነተኛ ተቃዋሚ ነው።

“በየቦታው ሕዝቡን እያወናበዱ እንደገና የፌውዳሉ ሥርዓት ትንሳኤ እንዲያደርግ የሚጥሩት መሳፍንቶችና ባላባቶች የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ተፃራሪዎች ናቸው።

“ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም የብዝበዛ የግምታቸውን የሚሰባብርባቸው የቢሮ ከበርቴዎችና አቀባባይ ከበርቴዎች የሕዝባዊውን መንግሥት መቋቋም ለማክሸፍ አይመለሱም።

“በተራማጅ ለምድ ተሸፋፍነው የሕዝቡን አብዮታዊ የትግል ግለት ለማቀዝቀዝና አቅጣጫውን ለማስቀየር የሚቅበዘበዙት ሶሻል ሾቪኒስቶችና ሶሻል ፋሺስቶች ሌሎችም የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ፅኑ ተቋዋሚ ናቸው።  ​

“የሀገሪቱን የሰው ጉልበትና ጥሬ ሀብት በርካሽ ዋጋ እያንጋፈፉ በሌላ በኩል የፋብሪካዎቻቸውን ግሳንግስ በእጥፍ ድርብ ዋጋ እያራገፉ ሕዝቡን የሚበዘብዙትና የሚያልቡት አለማቀፍ ባለወረቶች ጊዜያዊው ሕዝባዊው መንግሥት እነዚህን የትርፍ ትርፍ ምንጫቸውን ስለሚደፍንባቸው መቋቋሙን አጥብቀው ይቋወማሉ። ከስልጣን ላይ ካለው የምርጥ መኮንኖች አቀባባይ ከበርቴዎች ጋር በመመሳጠረ ልዩ ልዩ ወጥመዶች ይዘረጋሉ”

ምስኪን ዲሞክራሲያ! የኔ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ተቃዋሚው ብዙ ነው ብላ ጠላቶችዋን እንደአሸዋ እየቆለለች ስትደነፋ፣ በዚህ ብቻ ይህ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አብዮታውያን አንደሚሉት በታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ እንጂ አሷ እንደምትለው “ከምርጫ በማውጣጣት” ለማቋቋም እንደማይቻል ወለል አድርጋ አምናልን ራሷን በጥፊ መታችና ቁጭ አለች።

እዚህ ላይ መቼስ ቢያንስ ቢያንስ ተራ ሊበራል ከበርቴ እንደመሆናችሁ ብታምኑልን ይሻላችኋል። አለበለዚያ የባሰ ጉድ ነው።

መቼም አንድ ሰው አድርባይም ሆኖ ተራ ሎጂክ ሊገባው ይችላልና እናንተም የሚከተለውን ልብ እንድትሉ እንጠይቃችኋለን። ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታችን እነዚህ ሁሉ ጠላቶች አሉበት ስትሉ “አይነተኛ ተቃዎሚው” “ጽኑ ተቃዋሚው” “የዚህን መንግሥት መቋቋም ለማክሸፍ የማይመለሰው” “ተፃራሪው” አልፎ ተርፎም ይህ ሁሉ የፀረ ሕዝብ ጥርቅም “እየተመሳጠረ ልዩ ልዩ ወጥመዶችን እየዘረጋ” ያስቸግራል ስትሉ ይህንን መንግሥት ለማቋቋም ኃይለኛ ተጋድሎ እንደሚያስፈልግ ታምናላችሁ ማለት ነው። ይህን ሁሉ ተቃውሞ ማሸነፍ አለበት ማለት ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የረዥም ጊዜ የተወሳሰበ የፖለቲካና የጦር ትግል አያስፈልጋቸውም ትሉ እንደሆነ፣ በምርጫ በመውጣታችን ብቻ ተደናግጠው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላቶች ከታሪክ መድረክ ይወርዳሉ ትሉ እንደሆነ መቼስ ከሊበራል ከበርቴ ቅዠታችሁ እንድትነቁ ከመፀለይ ሌላ የምናደርግላችሁ ነገር የለም። ግን ከፍ ብለን እንዳልነው ይህንን ብታምኑልን ይሻላል። አለበለዚያማ አላማችን ከነዚህ “እንመራረጥ” ከሚሉ ፊውዳሊስቶችና አቀባባዩች ሁሉ ጋር ሆነን፣ ፀረደርግ የሆነ “ዲሞክራሲያዊ” መንግሥት ለማቋቋም ነው የሚል ጨርሶ አድሃሪ የሆነ አቋም ወስዳችሁ መጋለጥ ይሆንባችኋል። ነው ወይስ አቋማችሁ ይኸ ይሆን? እስቲ አንባቢ ይህንን የጠላቶች ዝርዝር እንደ ገና ይመልከተውና እኛ የታዘብነውን ሌላ ጉድ ይታዘብ!

“በመጀመሪያ ደረጃ” የዚህ መንግስታቸው “አይነተኛ” ተቃዎሚ ደርጉ መሆኑን ይነግሩናል። ታዲያ በዚህ የሚያሳዩን ምንድነው? በዚህ ቅደም ተከተላቸው የሚያምኑልን ይህ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስታቸው” “በመጀመሪያ ደረጃ ፀረ ደርግ መፈክር መሆኑን ነው። በዚህ ጥቅሳቸው ከምርጫ የሚወጣው ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊስት መፈክር እንዳልሆነ ማመናቸውን አድርባዩቹ ጨርሶ ልብ አላሉትም። የአስፋወሰን /መንገሻ ዲሞክራቲክ ህብረት ንቅናቄ ጊዜያዊ መንግሥት የጠየቀው ባስቸኳይ “የማይገባውን ስልጣን እጁ ያስገባውን፣ አገሪቱን በፋሺስታዊ አመጽ ጨብጦ የያዘውን ፋሽስታዊ ደርግ” ለመጣል እንደሆነ በኦክቶበር 8 ቀን መግለጫው አስታውቋል። አድርባዩቹ ደግሞ ይህንን መንግሥት የሚጠይቁት

 ራሱን የቻለ የመንግሥት ሥርዓት ሳይሆን እየተጠናከረ የሚሄደውን ወታደራዊ የፋሽስት መንግሥት በአጭር ለመቅጨት . . .

እንደሆነ ሲያስታውቁን ቀጥታ ከሞናርኪስቶቹና ከነሲአይኤ ጋር መቆማቸውን አልተረዱት እንደሆነ በኢትዮጵያ አብዮት፣ በ1968 ዓ.ም ያለው የመደቦች አሰላለፍ ጨርሶ አልገባቸውም ማለት ነው።

እኛ ግን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የመደቦች አሰላለፍ ጠንቅቆ ገብቶናል። ዋና ጠላቶቻችን ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ናቸው። የምንታገልለትና የምንሰዋለት ጊዜያዊ መንግሥት ቢኖር በነሱ መቃብር ላይ በሕዝባዊ አመጽ ተጠንስሶ፣ በሕዝባዊ አመጽ ተመርኩዞ የሚገዛው የጭቁን ሕዝቦች ፈላጭ ቆራጭ አብዮታዊ መንግሥት ብቻ ነው።

ለዚህም የምንከተለውን ጐዳና “አብዮቱ እንዲገፋ” በሚል ትንተናችን /ሰ.ህ.ድ. ቁጥር 25/ ግልጥልጥ አድርገን አሳይተናል። በመጀመሪያ “መሬት ላራሹ” በሚለው አብዮታዊ መፈክር ስር የተሰለፉት የኢትዮጵያ ገበሬዎች መሬትን እጃቸው ለማስገባት አስፈላጊ ሆኖ ላገኙት ለነፃነታቸው ከፀረሕዝብ ኃይሎች ጋር የሞት ወይም የሽረት ትንንቅ በማድረግ ላይ ናቸው። መሬትን እጃቸው ለማስገባት ከፈለጉ በየደረጃው ፖሊሱን፣ ዳኛውን፣ አስተዳዳሪውን፣ ባጭሩ የቀድሞውን ሥርዓት የመንግሥት አውታሮች እየደመሰሱ ስልጣንን እጃቸው ማስገባት እንዳለባቸው ከገዛ እለታዊ ትግላቸው ተምረዋል። ለዚህም ተግባርና መሳፍንቱና ኤምፔሪያሊስቶች ያወጁባቸውን የርስ በርስ ጦርነት ለመመከት “አስታጥቁን” እያሉ በመጮህ ላይ ናቸው። ፀረዲሞክራቲኩ የደርግ አገዛዝ “ማስታጠቅ ማጫረስ ነው” በሚል ፈሊጥ የሕዝቡን ጥያቄ አፍኖ ለመያዝ በመሞከሩ ድሃ ገበሬዎችን፣ ዘማቾችን፣ተራማጅ የመሬት ይዞታ ወኪሎችን በማስጨረስ ላይ ይገኛል።

ነገር ግን ይህ የጭቁኖች እሮሮ አልተሰማምና አብዮታችንን ከመገስገስ፣ ጭቁኖችን ከማሸነፍ የሚያግዳቸው ከእንግዲህ ምንም አይነት ኃይል የለም። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ባላቸው አቅም፣ እስከፀጉራቸው የታጠቁትን አድሃሪዎች አመጽ እየመከቱ ከፍተኛ ትምህርት በመቅሰም ላይ ናቸው። ከራሳቸው ሌላ የሚተማመኑበት ምንም ኃይል እንደሌለ ገብቷቸዋል። ስለዚህም በዚህ በያዙት አብዮታዊ ትንንቅ ገፍተው፣ ድርጅቶቻቸውንም አጠንክረው፣ የሚያስፈልጋቸውንም ትጥቅ “ከደርጉም ሆነ ከደርጉ ውጭ” ፈልገው በአብዮታዊ አመጽ የመንግሥትን ስልጣን እጃቸው ያስገባሉ።

እንኳን የትጥቁን ነገር አንስተው ይቅርና፣ ድርጅቶቻቸውን እንኳን ያጠናክሩ ስንል “አሁን ካሉትና በአጭር ጊዜ ሊቋቋሙ ከሚችሉት” ድርጅቶች በአስቸኳይ እንመራረጥ እያላችሁ ለምትለፍፉት አድርባዩች ይህ ጐዳና ረዥም ይመስላችሁ ይሆናል። ግን ለአብዮታዊ ድል ያለውን መንገድ ይኸው ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ጭቁኖችም፣ ችግራቸውንና ብሶታቸውን ብቻ ሳይሆን የታጠቁ አድሃሪዎችን እብሪትና አመጽ ከጭቁኖች ጐን ሆነው በመከራ በመክፈል ላይ ያሉት ዘማቾችም ተራማጆችም ይህንን ሁሉ ሃቅ ተገንዝበውታል። ከአዲስ አበባ ሚልዩን አብዮታዊ አዋጅ ቢወጣ ስራ ላይ ይውላል ማለት አይደለም። ሥራ ላይ የመዋሉ ጉዳይ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ከነሱም ጋር በሺህ የጥቅም ክሮች የተሳሰረውን የአስተዳደር አውታር በጭቁን ሕዝቦች አመጽ በየመንደሩና በየስርቻው መደምሰስን ይጠይቃል። እነዚህ ፀረሕዝቦች እስካልተደመሰሱ ድረስ “በዲሞክራሲያዊ ምርጫ” ወኪሎቻችሁን ምረጡና ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አቋቁመን፣ በመንደራችሁ መደምሰስ ያቃታችሁን ጠላት እኛ ከሬዲዮ አዲስ አበባ እንደመስሰላችኋለን እያሉ ከትግል ሊያዘናጓቸው የሚፈልጉትን አወናባጆች ከእንግዲህ አያዳምጧቸዉም። የኢትዮጵያ ጭቁኖች በመንደራቸው ጣፊያ እየተነሱ፣ ከአዲስ አበባ ታናሽና ታላቅ ስደድልን ብለው ወኪል የሚልኩበት ምንም ምክንያት የላቸውም።

ሁኔታው እንደዚህ ሆኖ ሳለ፣ የመታጠቅና በአብዮታዊ አመጽ ፀረሕዝቦችን ደምስሶ አብዮታዊ መንግሥትን የማቋቀሙ ተግባር ከፊታችን  ተደቅኖ ሳለ፣ የታጠቁ አድሃሪዎችና ፖሊሶች በድሃው ገበሬ፣ በዘማቹ፣ በተራማጁ ላይ መረን ተለቅቀው እንዳበደች ውሻ በሚናከሱበት በአሁኑ ጊዜ፣ ይህንን አንገብጋቢውን የትጥቅ ጉዳይ ችላ ብላችሁ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለውን አድሃሪ መፈክር በአንቀልባ አዝላችሁ ማላዘን ትችላላችሁ።

እኛ ግን፣ ለኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ወዝአደሮችና ጭቁን ሕዝቦች፣ ያለአንዳች እወደድባይነትና አድርባይነት ተጋድሏችን የአንድን ሕዝብ ነፃነት ለመሰለ ቁም ነገር የሚደረግ ታሪካዊ ተጋድሎ በመሆኑ ረዥምና የተወሳሰበ እንደሆነ ያለመታከት እናስገነዝባለን። እስከዚያው ግን አድርባዩችና አወናባጆች አንድ ነገር ልብ በሉ። አሁን በምትነዙት ውዥንብር ታግዘው መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ኢምፔሪያሊስቶች የሚጠነስሱት ሴራ ተሳክቶ፣ ሕዝቡም ከትጥቁ ትግል አይኑ ወደምርጫ ተስቦ፣ የናንተን ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት “ይመርጥላችሁ” ይሆናል። ነገር ግን ይህንን ሴራ እንደሕዝባዊ ድል ቆጥረንላችሁ፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች የትግል ትጥቃችንን አንፈታም። ሕዝቡ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ የምናደርገውን ቅስቀሳና ትግል ፋታ ሳንሰጣችሁ እንቀጥለዋለን። የምትጭኑብንን “ዲሞክራሲያዊ” መንግስታችሁን በአብዮታዊ ሕዝባዊ አመጽ ተቋቁመን፣ የኢትዮጵያን ጭቈን ሕዝቦች ፈላጭቆራጭና አብዮታዊ አገዛዝ በሕዝብ ጠላቶች መቃብር ላይ እንመሰርታለን። አድሃሪዎችም አድርባዩችም ለዚህ ጥርጥር አይግባችሁ።

በመጨረሻ ላይ ለአንባቢዎቻችን ልናስገነዝብ የምንፈልገው አንድ ነገር አለ። “የሰፊው ሕዝብ ድምጽ” የጊዜው ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም እንደሆነና ዋናውም ቅራኔ በነዚህና በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መካከል እንደሆነ አመልክቷል። በነዚህ ዋና ጠላቶች ላይ የሚነሱ ኃይሎች በሙሉ በትግል ሊተባበሩ እንደሚችሉና መተባበርም እንዳለባቸው ያምናል። የተራማጆችም ተግባር እርስ በራሳቸው መነካከስ ሳይሆን እነዚህን ዋና ጠላቶች በተባበረ ኃይል ለመደምሰስ ሰፊውን ሕዝብ ማደራጀትና ማዘጋጀት እንደሆነ ግልጽ ነው። ለመተባበርና የትግል አንድነት ለመመስረት ግን ውዠንብርን አስወግዶ የተጣራ የፖለቲካ መስመር መቀየስ እጅግ አስፈላጊ ነው። ውዠንብር ነዥዎችንም ማጋለጥና መታገል የሚያስፈልገው ለዚሁ ነው። በ“ዲሞክራሲ” ላይም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ቡድኖች ላይ የምናቀርበው ሂስና ማጋለጥ የ“ዲሞክራሲያ” አዘጋጆች እንደሚያደርጉት፣ ተራማጆችን ለመከፋፈል፣ የሕዝቡን ትግል ለማዳከም፣ ተራማጆችን በስም እየጠሩ ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ይሆን፣ በ“ዲሞክራሲያ” ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ካሉት ሃቀኛ ተራማጆች ጋር የትግል አንድነት ለመመስረት ነው። ዛሬ ይህን ባናደርግ ወደፊት በአብዮቱ ላይ ለሚፈጠረው ተጨማሪ ችግር ተጠያቂዎች መሆናችን አይቀርም። በ“ዲሞክራሲያ” ውስጥ ያሉ ሃቀኛ ተራማጆች ጋዜጣቸው የሚነዛውን ውዥንብር ማስወገድ አለባቸው። አብዮታዊ ግዴታቸው ነው።

አድሃሪዎችም፣ አድርባዩችም በሕዝባዊ አመጽ ይወድማሉ
የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ያሸንፋሉ።
አቅማችን የተወሰነ በመሆኑ ብዙ ቅጂዎችን
አላሰራጨንምና በይዘቱ የምትስማሙ አንባብያን
በሙሉ አንብባችሁ ላላነበቡ ብታስተላልፉ፣
ከተቻለም ጋዜጣው የሚበራከትበትን
ዘዴ በየፊናችሁ ብትፈልጉ ለትግላችን ይበጃል።
Scroll to Top