ሰሕድ ቁ. 1

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 1፣    ነሐሴ 14፣ 1966

በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እትሙ ውስጥ መኢሶን፣ ታሪክ የመደብ ትግል እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ሕዝቡ ወዙን አንጠፍጥፎ የፈጠረውን ሃብት በመጨረሻ ጥቂት ባለሃብቶች  እንደሚቀሙት ያስረዳል። ከትውልድ ትውልድ የሚጻፈውም ታሪክ፣ የነገሥታት ውዳሴ አይነት ብቻ ስለሆነ፤ የተጨቆነው ሰፊው ሕዝብ ምንም የታሪክ ድርሻ እንደሌለው ተደርጎ ታሪኩንም ይቀማል። ከየካቲት 1966 ወዲህ ግን፤ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ማለትም ሠራተኞች፣ ድሃውና ጢሰኛ ገበሬዎች፣ ዝቅተኛ ነጋዴዎች፣ ጠቢቡና ባለእጁ፣ ዝቅተኛ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወታደሮች፣ የቀን ሠራተኞችና ሥራ አጦች፣ ተማሪዎችና ምሁራን ሁሉ  ትግሉን በማፋፋም ላይ እንደሚገኙ ይዘረዝራል። ሆኖም፣ የጋራ ሕዝባዊ ትግላቸውን የሚያስተባብርላቸውና የሚመራቸው ግንባር ቀደም ድርጅት ለመመሥረት ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅ በአጽንኦት ያሳስባል። በዚህም መሪ የፖለቲካ ድርጅት እጦት ምክንያት የወታደሩ ክፍልን የሚውክለው ደርግ፣ ትግሉን ቀደም እያለ ለመምራት ሲጣጣር እንደሚታይ ይገልጻል።

ወታደሮች ከሕዝብ አብራክ የተገኙ በመሆናቸው ገና ከጅምሩ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘታቸው ባያጠያይቅም፤ ከአንድ ማኀበራዊ ክፍል ብቻ የተውጣጡ በመሆናቸው እንደ መንግሥት፤ የሰፊውን ሕዝብ ጥቅሞችና ፍላጎቶች አሟልተው ለመጠበቅ አይችሉም። በቅርቡ በሰፊው የተነሱትንም መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ አልሞከሩምም፤ አልቻሉምም። ስለዚህም፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የወደፊት እድሉን በገዛ እጁ ለማስገባት በትግሉ ውስጥ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባው የሚጠቁም ሰድስት ነጥቦች ያቀርባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 ቁጥር 1                                                                       ቀን 14/12/66

 

 የእንቅስቃሴው ባለቤት ሰፊው ህዝብ ነው

የሰው ልጅ ታሪክ የትግል ውጤት ነው። ትግሉ ከፍጥረት ጋር ነው። ሰው ራሱ የፍጥረት ክፍል ሆኖ ከፍጥረት ጋር ዝንትዓለም የማያቋርጥ ትግል ያደርጋል።— የማደግና የመሻሻል መሰረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት ሲል መለወጥ ፍጥረትን መለወጥ ግዴታ ነው። ዋናውና እውነተኛው የሰው ልጅ ታሪክ ይሄ ሲሆን፣ ታሪክ በመባል የሚታወቀውና በታሪክ መጽሐፍት ውስጥ የምናነበው ግን የታሪኩን አንድ ትንሽ ክፍል ነው። ለዚያውም በተዛባ መንገድ የቀረበ የመደቦች ታሪክ ነው። አንደኛው መደብ ወጥቶ ወርዶ ወዙን አንጠፍጥፎ የፈጠረውን ሃብት፣ ሌላው መደብ በኃይል በመጨቆን ይቀማዋል። የላቡን ፍሬ ይበዘብዘዋል። ይዘርፈዋል። አሁን ታሪክ በመባል የሚወራው የሰው ልጅ ርስበርሱ በሚያደርገው የመደቦች ትግል ነው። በኢትዮጵያም ታሪክ የሚባለው በአድርባዮች የተፃፈ የጨቋኝና የበዝባዥ ነገሥታት ውዳሴ አንጂ የመደቦች ትግል፣ የህዝብ ታሪክ ባለመሆኑ በእውነተኛው የሰው ልጅ ታሪክ ምን ያህል ርቀት እንደምንገኝ ለመገመት የሚያዳግት አይመስልም።

ታሪኩ በትክክል ባይፃፈም የኢትዮጵያ እንደማንኛውም የአለም ህዝብ ታሪክ አለው በጨቋኝና በተጨቆኝ፣ በበዝባዥና በተበዝባዥ፣—በሃብት ፈጣሪዎች መካከል ከባድ ትግል ሲካሄድ ቆይቷል። ብልጭ ድርግም ብቅ ጥልቅ ቦግ ድብዝዝ የሚለው በአንድ በኩል ሲግል በሌላ በኩል የቀዘቀዘ በመምሰል ውስጥ ውስጡን እንደ እሳተ ጎሞራ የሚንቦገቦገው የመደቦች ትግል ካለፈው  የካቲት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን በመላ በማናወጽ ላይ ይገኛል።

ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ- የሰራተኛው፣ ደሀውና ጢሰኛው ገበሬ፣ ዝቅተኛው ነጋዴ፣ — ዝቅተኛው የመንግስት ሰራተኛ፣ ወታደሩ፣ የቀን ሠራተኛው እና ኩሊው፣ ስራአጡ፣ ተማሪው ምሁሩ ወዘተ – ትግሉን በማፋፋም ላይ ይገኛል። ጨቋኞች እና በዝባዥች- ንጉሳውያን ቤተሰብ፣ መሳፍንት እና ታላላቅ ባላባቶች፣ ባለ ብዙ መሬቶች እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች፣ የጦር አለቆች፣ የውጭ አና የአገር ውጭ ከበርቴዎች፣ የነዚህ አጫፋሪዎች እና ደላላዎች ወዘተ – በህዝቡ እንቅስቃሴ በመወገር ላይ ናቸው። ሰፊው ህዝብ ጠላቶቹን በኃይል አጥቅቶ ወደ ኋላ እንዲያፈገፈጉ ቢያደርጓቸው ድምጥማጣቸውን በማጥፋት ዋናውን ድል ገና አልተቀዳጀም።

ታፍኖ፣ መተንፈሻ አጥቶ፣ ተጨቁኖ ተይዞ ስለነበረ ሰፊው ህዝብ ደንበኛና አጠቃላይ የትግል ድርጅት ለማቋቋም አልቻለም። አሁንም በዚያም በዚህም በልዩ ልዩ ለመደራጀት ትልቅ መፍጨርጨር በማድረግ ላይ ቢሆንም ትግሉን በግንባር ቀደምነት የሚመራ ተራማጅ የሆነ ጠንካራ ድርጅት ለመመስረት ብርቱ ጥረት ይጠበቃል። ከባድ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል። የድርጅቱ አስፈላጊነት የማያጠራጥር እና የማያከረክር ነው። ሰፊው ህዝብ ጠላቶቹን ሙሉ በሙሉ ደምስሶ የመንግስቱን ስልጣን ለመቀዳጀት ያልቻለው እንደዚህ አይነት ድርጅት በማጣቱ ነው። ለዚህም ምክንያት ሳይሆን ይቀራል በአሁኑ ጊዜ ወታደሩ ቅድሚያውን ይዞ የሚገኘው?

ወታደር ከህዝብ አብራክ የወጣ፣ የህዝብ አባል፣ በተመደበበት ሥራ በሚለብሰው ዩኒፎርም እና በሚይዘው መሳሪያ አንድ ከሌላ ሁሉ ከሰርቶ አደሩና ከአርሶ አደሩ እና ከሌላው የሰፊው ሀዝብ ክፍሎች በምንም አይለይም። አባቱ እናቱ ወንድሙ እህቱ ሚስቱ ልጁ አጎቱ አክስቱ እነዚህ ሁሉ ግማሹ ሰራተኛ እና፣ ግማሹ ገበሬ,፣ግማሹ ተማሪ፣ ግማሹ ነግዶ አዳሪ፣ አጠቃላይ የሰፊው ህዝብ ክፍል ናቸው። ከነዚህ ከቤተሰቦቹ ጋር የተጨቆነ የተበደለ ግፍ የተሰራበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ወታደር በሰፊው ሕዝብ እንቅስቃሴ ውስጥ ክሕዝብ ከወገን በመሆን ተሳትፎዋል። የሰፊውን ህዝብ ትግል አቀናብሮ የሚመራው አጠቃላይ እና ጠንካራ ድርጅት ባለመኖሩ ለጊዜው ይህ ቀንበር በወታደሩ ተከሻ ላይ እንዲወድቅ ሆነ።

የህዝቡን ፍላጎት እና ጥያቄ በመከተል ወታደሩ እነ እክሊሉ ሃብተውልድን እነ እንዳለካችው ምኮንን እነ አሰራት ካሳን— ሰፊውን ሕዝብ በመጨቆን እና በመበዝበዝ ቀንደኞች የነበሩትን ይዞ አሰረ። የነዚህ ሁሉ በላይ እና ቁንጮ የሆኑትን አጼ ኃይለሥላሴንም የፈላጭ ቆራጭ ስልጣናቸውን ቆራርሶ፣ የሰይጣናዊ ድርጊታቸው መሳሪያ የሆኑትን ባለሟሎቻቸውን ለይቶ ብቻቸውን አስቀምጧቸዋል። በህዝቡ ላይ የደረሰውን ግፍ እና በደል የተፈጸመውን ጭቆና እና ብዝበዛ በሬድዮ በጋዜጣ እና በሌሎችም የዜና ማሰራጫ መሳሪያዎች በማብራራት እና በመዘርዘር ብዙ — እነዚህ እና ሌሎች በህዝብ ፍላጎት እና ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ ድርጊቶች የሚደገፉ ናቸው። በየቦታው የሚጎርፈው ህዝብ የተባባሪነቱ ድጋፍ የማያጠራጥር ምስክር ነው።

ወታደሩ የህዝቡን  ፈቃድ እንዲፈጽም /ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከውስጥ መርጦ ያቋቋመው ደርግ/ ግን ገና ወደ ፍሬ ነገሩ አልገባም። ከዚህ በላይ የተመለከቱት እና እስካሁን በመፈጸም ላይ ያሉ በቅድሚያ መደረግ ከሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።  ዋናዎቹ እና አጣዳፊዎቹ የህዝብ ጥያቄዎች ገና ምንም አልተነኩም።  እንዳሉ ናቸው።  ጢሰኛና ባለ መሬት፣ ሰራተኛ እና አሰሪ፣ ሰፊው ሕዝብና ገዢው መደብ አሁንም እንደ ተፋጠጡ ናቸው።

ደርጉ ለምን እስካሁን ወደ ፍሬ ነገሩ አልገባም? አጣዳፊ ዋና ዋና እና መሰረታዊ የሆኑትን ጉዳዮች ለምን ችላ አላቸው? ምንድነው የሚጠብቀው? ችግሩ ምንድነው? ሶስተኛ ዙር ከተጀመረ ወደ ሁለት ወር ያህል ቢሆነው እስካሁን ድረስ ባለስልጣኖችን ከመያዝ እምብዛም አልፎ ያልሄደው በምን ምክንያት ነው? ይህን ያህል ዝግታው መጎተቱ መወንዛቱ መንዛዛቱ ለምን ይሆን? ” ደም እንዲፈስ” ለማለት ይሁን? የማን “ደም”? የሰፊው ሕዝብ ደም ሁል ጊዜ ይፈስስ የለ? በጥንቃቄ፣ በትዕግስት፣ በአስተዋይነት፣ በብልህነት አርአያ ለመሆን ” የአለምን አድናቆት” ለማግኘት ይሆን? የቱ ነው የሚቀድመው? መቅደም የሚገባው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጨባጭ ችግር ነው ወይስ ” አለም በብልህነቱ በአስተዋይነቱ” ያደንቀኛል፣ ምሳሌ ያደርገኛል የሚለው ከንቱ መመጻደቅ፣ የቅዠት ዓለም የቅዠት ዓለም? ደርጉ ለነዚህ እና ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምን መልስ እንዳለው አናውቅም ሰፊው ሕዝብ ወታደሩ ጭምር በጉዳዩ ላይ በጣም ማተኮር ያለበት ይመስለናል።

ከዚህ በላይ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ደርጉ አንዳንድ ደህና፣ ከሕዝብ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ ነገሮች ቢያደርግም፣ አንዳንድ አድሃሪ እና ፀረ ህዝብ ድርጊቶችን ፈጽሟል። በአንድ በኩል የፖለቲካ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ተደረገ፤ መልካም ነው ሁሉም ተደሰተ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ተራማጆችን የህዝብ ወገኖችን በመካከል ጭምር አሰሩ፣ በጭቆና ምክንያት ትግል የጀመሩት ኤርትራውያን እና ሌሎች ግን “ሀገር ለመከፋፈል “በሚል ዘይቤ እንዳይፈቱ ተደረገ። የሚያሳዝን ትልቅ የፖለቲካ ስህተት ነው። 20 የሚሆኑ ኤርትራዊያን የፓርላማ አባሎች ስራቸውን ለቀቁ። እውነተኛ ነጻነትን ፈላጊዎች ከእስር ቤት ወጥተው ሳያልቁ እንዲያውም እንዳይወጡ ተከልክለው እያሉ የአሜሪካ ኢንፔሪያሊዝም፣ የሲአይኤ  ባልደረባ የሆነው አወናዋጁን  በላይ ስዩም — በራዲዮ እና በጋዜጣ ህዝቡን እንዲያወናብድ ፈቅዶለታል።

የደርጉ አሰራር በፍጹም የተማታ ነው። በአንድ በኩል እነ አክሊሉ እና እንዳልካቸውን ከስልጣን አስወግዶ ቀንደኛ የሆኑ ግብረ አበሮቻቸው ጋር ማረፊያ ቤት በማስገባቱ የሰፊውን ህዝብ ድጋፍ ሲያገኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመሳፍንት ወገን የሆነውን እዚህ ግባ የማይባለውን

ሚካኤል እምሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አደረገ። ሌሎችም በህዝብ ላይ ብዙ በደል እና ግፍ የፈጸሙ ባለስልጣናት አሁንም በስልጣን ላይ ናቸው። በየጠቅላይ ግዛቱ፣ በየሚኒስቴሩ ልዩ ልዩ መንግስታዊ ድርጅቶች ብዙ ብዙ በስልጣን የባለጉ በማረፊያ ቤት የሚገኙ ባለስልጣኖች ግብረ አበሮች አሁንም እንዳሉ ናቸው። በማስታወቂያ ሚኒስቴር ዜና አሰራር አሰራጮች በተለይ ጋዜጠኞች — የማወናበድ እና ፀረ ህዝብ ስራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው.

በአንድ በኩል “ኢትዮጵያ ትቅደም ” ማለት የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ይቅደም ማለት ነው ” መሬት ለአራሹ ” እያለ የሚያስተጋባው ጢሰኛና ደሀ ገበሬ መሬት እንዲያገኝ ይሆናል፣ ስራ አጥቶ የሚንከራተተው ሁሉ ስራ ይሰጠዋል፣ ሰራተኛው ደንበኛውን የሥራውን ዋጋ እንዲያገኝ ይደረጋል፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በእኩልነት ሰብአዊና ብሔራዊ መብታቸውን ተጎናጽፈው እየሰሩ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ይደረጋል ወዘተ ማለት ነው ተብሎ በመተርጎሙ ሰፊው ህዝብ ተደስቶ መዝሙሩን አብሮ ያስተጋባል። በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን ድረስ እነዚህን ስራ ላይ ለማዋል ምንም አይነት ፕሮግራም አላወጣም። ከህዝቡ በኩል በርከት ያሉ —, ፕሮግራሙ ንጥፎች እና ረቂቆች መቅረባቸው አያጠራጥርም። ቢሆንም ደርጉ የእንዳልካቸውን አጭበርባሪ እና ፀረ ህዝብ መመርያ ከአድሃሪው ከሚካኤል ጋር አንድነት በአቋቋሙ ኮሚቴ ስራ ላይ ለማዋል — ይመስላል።

ባንድ በኩል የህዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ አለባቸው፣ ደርጉ ይህንን ለመፈጸም ነው የተቋቋመው ይላሉ። በሌላ በኩል ግን ሰላማዊ ሰልፍ ክልክል ነው። ማህበራችሁን አፍርሱ፣ አፋችሁን ዝጉ፣ እንቅስቃሴያቹን አቁሞ ማለት ደርጉ የሚያደርገው ማስፈራራት እና ዛቻ ፍጹም ፀረ- ህዝብና ጸረ-ዲሞክራሲያዊ ነው። በጦሩም ውስጥ የደርጉ አባሎች በመጀመሪያ ባልተጣራ እና በቸኮላ ተመርጠው የመጡ በመሆናቸው ተግባራቸውን በሚገባ አልፈጸሙም። እያንዳንዱ ክፍል ወኪሎቹን እንደገና እየመረጠ ይላክ, በማለት የቀረበውን ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ” ሚስጥር አውጥተዋል የስራ ልምድ አግኝቶአል” ወዘተ በማለት የቀረበው የስልጣን ጉጉት መጋረጃ — ምክንያት ነው።

ደርጉ እነዚህን የመሳሰሉ, እርስ በእርሳቸው — የተጭበረበሩ ድርጊቶችን መፈጸሙ ከትልቅ ጥርጣሬ ላይ ሳይጠለው አይቀርም።የኮንጎ ዘማቾች ቤቶች / ሲያስፈራራ / ደርጉ ” እኛ ከሌለን የሀገሪቷ ደህንነት የለም ” ምን ማለት ይሆን ” ደርጉ ኢትዮጵያ ነው፣ ኢትዮጵያም ደርጉ ነች” ማለቱ ከሆነ ቶሎ መታረም የሚገባው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያ የጥቂት ሰዎች ሞኖፖል ሆና ቆይታለች አሁን ግን ሰፊው ህዝብ ” በቃ አቁም፣ ኢትዮጵያ የሰፊው ህዝብ ጭምር ናት። እኛም ኢትዮጵያዊያን ነን፣ ሁላችንም በደስታ ሆነ በችግሯ ለመካፈል፣ ለህዝቡ የሚስማማውን አስተዳደር እና ሌላም ነገር ለማሰብ እና በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ መብት አለን፣ እዚህ ረገድ ማንም ከማን አይበልጥም” ብሏል።

መውደቅ ላይ ያለው የመሳፍንት እና የባለ አባት መንግስት የበላይ ጠባቂ  እና ደጋፊ የሆነው የአሜሪካን ኢንፔሪያሊዝም የሰፊውን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ ትልቅ ሴራ በመጠንሰስ ላይ ነው በአሁኑ ጊዜ አንደኛው ቀንደኛ የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ጠላት የአብዛኛው የአብዛኛውን የአለም ታዳጊ ህዝቦችን ደም የሚመጥጠው አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መሆኑ አያጠራጥርም።

ሲአይኤ የሚባለው የአሜሪካን ኢንፔሪያሊዝም ስለላ ድርጅት በሀገራችን ውስጥ ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ መልምሎ ያስተማራቸው ሰላዮች ቁጥር በጣም ብዙ ነው። አማካሪዎች፣ አዋቂዎች አስተማሪዎች ” የሰላም ጓድ” የሠራተኞች ወዘተ በማለት በየመንግስቱ መስሪያ ቤትና በየድርጅቱ ብዙ የስለላ ሠራዊት አሰማርቶ ብዙዎችን የሀገር ተወላጆች በገዛ ሀገራቸው እና ህዝባቸው ላይ እንዲሰልሉ በገንዘብ ገዝቶአቸዋል። እንደ ስዩም ሰብሃት፣ ሳሙኤል አለማየሁ /አአድ/ እና ሌሎችም አለን የሚሉ አደርባዮች የፀረ ህዝቡ የሲአይኤ ቡችሎች መሆናቸውን በማያጠራጥር አኩዋሃን የህዝብ ወገኖች ደርሰውባቸዋል። ከየካቲት ወዲህ የሰፊው ሕዝብ እንቅስቃሴ የማጨናገፍ እና ፍፁም የአሜሪካን ኢንፔሪያሊዝም ጥገኛ የሆነ መንግስት ለማቋቋም፣ ቡችሎችን ስልጣን ላይ ለማውጣት ምርጥ ሰላይዎችን ወደዚህ በመላክ ከባድ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። አንዳንዶች ደርጉ ውስጥ እና በደርጉ አካባቢ የሚያጨበጭቡ እና እምቢልታቸውን የሚነፉትም የሲአይኤ አሻንጉሊቶች መሆናቸው አያጠራጥርም ሌሎችም  በስልጣን እርካብ …ላይ አንዳንድ አገራቸውን …ወዲያ ወዲህ

በመመልከት ላይ — ከጥቂት ቀናት በኋላ ኮረቻው ላይ ለመውጣት መሞከራቸው አይቀርም። የሲአይኤ መርዝ ስር ሰዶአል።

በእንደዚህ ያለው ሁኔታ አዲስ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ  ምን ማድረግ አለበት

  1. አይንን ከፍቶ በንቃት መከታተል፣ በልዩ ልዩ መንገድ በትግሉ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ፣
  2. መሀበር፣ እድር ወዘተ… የመሳሰሉትን የህብረትና የአንድነት መሠረቶች በየመስሪያ ቤቱና በየሰፈሩ ማቋቋሙን መቀጠል ጠላቶቹን የመቋቋም — ተንኮላቸውን የሚያከሽፍበትን ዘዴ በአንድነት መፈለግ፣
  3. በቀበሌ በወረዳ በአውራጃ በጠቅላይ ግዛት፣ በሙያ ወዘተ ደረጃ አጠቃላይ የህብረት እና የአንድነት ማህበሮችን እና ድርጅቶችን ማቋቋም፣ ያሉትንም ማጠንከር፣
  4. ቶሎ ብሎ አንድ ሁሉንም የሚያጠቃልል ብሔራዊ ግንባር ቀደም የትግል ድርጅት ማቋቋም፣
  5. በልዩ ልዩ የሰፊው ህዝብ ክፍሎች ተወክለው …በቁጥጥራቸው ስር ሆኖ የህዝብን አጣዳፊ ጉዳዮች እያከናወነ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲቋቋም የሚሠራ አንድ ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም መታገል፣
  6. እስከዚያው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሲቪሎች እና ወታደሮች ያሉበት አንድ ደርግ ውሎ ሳያደር ተቋቁሞ በቁጥር አምስት ስር የተመለከተውን እንዲያስፈጽም አጥብቆ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወቱን እና እድሉን ለማንም አሳልፎ መስጠት አይገባውም። በአንዳንድ ጥቃቅን ድርጊቶች እና በከንቱ የቃላት ተስፋ መርካት የለበትም። ሙሉ መብቱንና ነጻነቱን ለማግኘት፣ ጥቅሙን ለማስጠበቅ፣  የጥያቄዎቹን እና ፍላጎቶቹ እንዲሟሉ ለማድረግ ታጥቆ  በአንድነት እና በቆራጥነት በመደራጀት ትግሉን መቀጠል አለበት። የአሜሪካን ኢንፔሪያሊዝም እና የሃገር ውስጥ ቡችሎች በቀላል የማይመለሱ ጠላቶቹ መሆናቸውን ተረድቶ በንቃት እንዲጠብቃቸው፣ ሴራቸውንም እንዲያከሽፍ ያስፈልጋል።

እድላችንን በእጃችን እናስገባ
በትግሉ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንሳተፍ
የፈላጭ ቆራጭ ነጋሴ የ57 ዓመት ግፍ

“እባብ ግደል ከነበትሩ ገደል” በሚል አርዕስት ከማርቆስ መንክር የተዘጋጀው የሃይለስላሴ አጭር የህይወት ታሪክ እንደሚያስረዳን አፄ ” ራሳቸውን በጣም የሚያፈቅሩ የራሳቸውን ከንቱ ስራ በሚከፍሉአቸው ጋዜጠኞች እና ታሪክ ጸሐፊዎች በጎ አስመስለው እያፃፉ የሚኖሩ፣ ስማቸው በኢትዮጵያ እንደ አምላክ፣  ከነገስታቶች ስም በላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚጥሩ ሰው ናቸው ” ይለናል በስማቸው የሰየሙት መንገድ፣ አደባባይ፣ ሲኒማ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ከተማና ድርጅት ቁጥር ራስ ወዳድነታቸውን በግልጽ ያሳያል። ራሳቸውን በጣም አድርገው የሚወድዱ ስግብግብ ሰው ናቸው። ከራሳቸው እኩል የሚያፈቅሩት ነገር ቢኖር ምናልባት ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲያከማቹት የቆዩትን ገንዘብ ይሆናል። ምናልባት በሦስተኛ ደረጃ በልጅነታቸው ያሳደጓቸውን ዛሬም የሚደግፏቸውን ለአልጋወራሽነትና ለንጉስነት ያበቋቸውን የፈረንሳይ የእንግሊዝን ኢምፔሪያሊስቶች ሳይሆን አይቀርም። አፄ ኃይለላሴ በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን ማተሚያ ቤት፣ ጋዜጣ፣ ሆስፒታል በማቋቋም ንግድ ጀመሩ። በሀገሪቱ ውስጥ ያለአግባብ በመበልፀግ የመጀመሪያ በመሆን የልዩ ልዩ ሸቀጦችን ንግድ በሞኖፖል ከበአድና ከአገር ውስጥ ከበርቴዎች ጋር በማሻረክ ጀመሩ። ክብሪት፣ አልኮል፣ ጋዝ፣ አሞሌ ጨው፣ ሆቴል ታክሲ ጭምር የእርሳቸው ሞኖፖል ሆነ። ሚስታቸው ከዋና መኳንንቶቻቸው ጋር በዚህ ንግድ ተሳታፊ ሆኑ። የሀገር ነጋዴዎችን አቆርቁዘው በውጭ ነጋዴዎች ሀገሪቷን አስያዙ። ከ1920 ዓ.ም. ጀምሮ የ ” ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ” ባለቤት ሆኑ። ሸሽተው ውጭ ሀገር በነበሩበት ዘመን የሀገሩን ሃብት ለግላቸው ማዋል አለማቆማቸውን የማርቆስ መንክር ጽሑፍ ያስረዳናል። የእየሩሳሌምን ገዳም ለመሸጥ መዋዋላቸውን በእንግሊዞች ተገልጿል። እንግሊዞችን ከመለሱዋቸው በኋላ የአዶላን ወርቅ በመዝረፍ የህዝቡን መሬት— ብለው በማቋቋም ለልጆቻቸው እና — የህዝቡን መሬት በመከፋፈል, ጣሊያን የሰራውን መንግስት የነበረውን ንብረት በቅድምያ ለራሳቸው ከዛም ለልጆቻቸው፣ በተለይ የእርሳቸውን የነዋይ ፍቅር ለወረሳቸው ለተናኘወርቅ አከፋፍለው የተረፈውንም ለመኳንንቶቻች ረጭተዋል። ደሀውን መንግስት እያደህዩ ራሳቸውንና አሽከሮቻቸው እንዲከብሩ አድርገዋል። በቅርቡም አልፈው ተርፈው ደኑን እና መንግት ያለማውን ሸለቆ ለልጆቻቸው ለአማቶቻቸው አድለዋል።ጥቅምት 1948 ዓ.ም ይህን ዘረፋ ህገ መንግስት አወጣው ብለው የሀገሪቱዋን ሃብት ለማደል መብት ለንጉሡ ሰጥተዋል። ሞኖፖል እያደረጉ መያዝን ቀደም ባለው ጊዜ እንደተውት ሁሉ ህዝብን ንብረት መቀማትንም ከታህሳስ ወዲ በይፋ ማድረጋቸውን ለመኳንንቶቻቸው የተዉ ይመስላል። ታዲያ ህገወጥ ንግድ መተዋቸው ሳይሆን ንብረታቸውን ወደ ውጭ ስለ አሻገሩ ፋብሪካ ባለቤት በመሆናቸው ነው። እርሳቸው ታዲያ በሀገር ውስጥ የተጠቀሙት በእጅ አዙር ጉቦ ነበር ።  አልባሹ፣ ነብስ አባቱ፣ እቁባቶቹ፣ እልፍኝ አስከልካዩ፣ የገቢ ሚኒስቴሩና፣ የጽህፈት ሚኒስቴሩ ዋና ስራቸው የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ከበርቴ ፋብሪካ ሲያቋቁም ለአፄ የሚገባው ጉቦ እንዲከፈል ማድረግ ሆነ። ማስረጃ ይባል ይሆናል። ማስረጃውን በመርዝ ተገድለው ታለቁት ባለመዋሎች የተረፉት አራተኛ ክፍለ ጦርን ያጣበቡት ባለመዋሎች ያቅርቡ። አፄ ለጉቦ ደረሰኝ አይቀበሉም። ደረሰኝ ያለው ቢኖር ለሰማኒያ ዓመት የልደት በዓላቸው የተሰበሰበው ወርቅ ብቻ ነው። በዚህ ዘረፋና ለውጭ ንግዳቸው ዛሬ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት አፍርተዋል። ይህንን ውንብድናቸውን የተቃወሙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን። ባይቃወሙ ታዝበው ከዘረፋው ያልተካፈሉት በመርዝ በጥይት ተጨረሱ። በግዞት ተንገላቱ። እስር ቤት ማቀቁ። ተክለ ወልደሃዋርያት፣ ሎሬንዞ ትዕዛዝ፣ መኮንን ደስታ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ ዮሃንስ ረምሃ፣ አግዋለ ኃይሉ፣ ክብረት፣ ማሞ መዘምር፣ ጥላሁን ግዛው… ኧረ ስንቱ በእንደዚህ አለቁ። በዘወርዋራ መንገድ በነ ፀሃዩ እንቁስላሴ፣ በአባ ሐና ጅማ፣ አሉላ በቀለ፣ አፋኝ ጓዶች ብዙ ሰዎች ተፈጁ።ቁጥራቸው ገና ያልታወቀ ብዙ ሀገር ወዳጆች አለቁ። የየካቲት እንቅስቃሴ ያወጣቸው እነ አሊያ ፈጠነ ብዙ ይነግሩን ይሆናል.

በሀገር ውስጥ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ ህዝብን በመርዝና በጥይት መጨረስ፣ በእስራት እና በግዞት መፍጀት — የአስተዳደራቸው መሣሪያ ቢያደርጉ በውጭ ፖለቲካ ደግሞ ሳያቋርጡ የምዕራባውያንን የባርነት — መሣሪያቸው አደረጉ። የአፄን አስተዳደግ የጻፉ አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር እንደገለጹት ፈረንሳዮች በሐረር በነበርዋቸው ሚሲዮናውያን በኩል የአውሮፓ የመንፈስ ተጓዥ እንዲሆኑ አድርገው አሳደጓቸው ብለዋል። እንግሊዞችና ፈረንሳዮችም በመተባበር ልጅ እያሱ ወደ ጀርመን እና ቱርክ መንፈሳቸው ስላመራ / ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራረጡ ቢባልም / እኛኛውን ፈንቅለው አንህኛውም እንዲያነግሱ የሸዋን መኳንንት በገንዘብ ገዙ። አፄም እንግሊዝ አገር እስከ ሂዱበትም ጊዜ ድረስ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ ጋር የግል ንግዳቸውን እና የሀገሪቱዋን ፖለቲካ አስተባበሩ። የሌላ ሀገር መሪዎች የመሳሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ስንት የለፉ ሲሆን አፄ ኃይለላሴ ያቋቋመት የግላቸው የሆነ የቢራ ፋብሪካ ብቻ ነው። ለሃገሪቷ በጣም አስፈላጊ የነበረው የጦር መሳሪያ በግዥም ሳያስመጡ ማይጨው ደረሰ። ማይጨውም ላይ ህዝቡ እንዳይዘጋጅ መሳሪያ ለማግኘት ባለመቻሉ በጣሊያን ጦር ተጨፈጨፈ። የጣሊያኑ ጀነራል ባዶሊዮ እንደገለፀው ” የሃበሻን ጦር ለብዙ ዓመታት መዋጋት ይኖርብናል ብለን ተዘጋጅተን ነበር። ነገር ግን ተፈሪ ጦሩን ሳያዘጋጅ በመቆየቱ እና ስንቅ ከልክሎ እንዲራብ በማድረጉ፣ የተማሩ ወጣቶች የደፈጣ ጦርነት ይደረግ ያሉትን — የመሳፍንትን አሮጌ ሃሳብ በመከተሉ የጦር አዛዥነት ችሎታ የሌለው በመሆኑ ጦር መሪ አሳጣው ስለዚህም በቀላሉ ፈታነው” ብለዋል።

አፄ ኃይለሥላሴ ባልነበሩበት በተምቤንና በደቡብ ግንባር ብቻ ውጊያ ተድርጎ ላይ ማይጨው ላይ ህዝቡ ለመከላከል ሳይችል — በማንም ሀገር በጦር ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ በደል ያኔ ፈጽመዋል። / በ1943 እነ ቢትወደድ ነጋሽ፣ እነ አለቃ ፈጠነ፣ — አንደኛው ምክንያት ለምን ሳንዋጋ በቀላሉ ተሸነፍን በማለት— ይዞ ለጦር ፍርድ ቤት ለማቅረብና ለመቅጣት ነበር። በመቶ አለቃ በቀለ — በቀደም ለት በራድዮ በተናገሩት ጊዜ ይህንን ነው ያሰሙት። /አጼ ለምን አልተዋጉም? ምክንያቱም በፈረንጆች ስለሚያመልኩ ከመዝምታቸው በፊት እንሸነፋለን የሚል እምነት ስላደረባቸው እና ስለፈሩ ለመከላከልም ፍቃደኛ አልነበሩም። በቅርቡ የተከፈተው የእንግሊዝ መንግስት —- እንደገለፀው እርሳቸው በዚያን ጊዜ ከእንግሊዝ ጋር እባካችሁ በቀኝ ግዛት ጥገኝነት / ፕሮቴክቶሬት/ ያዙን እያሉ ይላላኩ ነበር። እርሳቸው ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ስር ብትወድቅ አልቸግራቸውም። ያንን መከረኛ ዘውድ ካልወሰዱባቸው ለሌላው ምን ግድ ኖሯቸው? ጣሊያን ድል በሆነም ጊዜ እንግሊዝ እና የደቡብ አፍሪቃ ጦር ኢትዮጵያን ይዞ አለቅ ሲል አፄ ሃይለስላሴ ተስማምተው ነበር። እንዲወጡ ያደረጉት አርበኞች ናቸው። ጣሊያን የተከላቸው ፋብሪካዎች እንግሊዝ እየነጠቀ ብያግዝ ሃገር ወዳድ የሆኑ ሰዎች ቢቃወሙ ንጉሶ ተከታታይ እየላኩ አስፈራርተዋቸዋል።  እንግሊዝ እንደፈለገ እንዲያደርግ እርሳቸው አበረታትቸዋል። በምስራቅ ኢትዮጵያም በኖሩበት ጊዜ ነጭና ጥቁር ለምን ይለያል ብለው የተቃወሙ ሃገር ወዳጆች በአጼ ኃይለስላሴ ፖለቲካ አበላሻችሁ እየተባሉ ማስፈራሪያ ይሰጣቸው ነበር። ኤርትራንም ከእንግሊዝ ነጻ ለማውጣት የታገሉትን አገር ወዳጆች አፄ እያስለቀሙ ወደ ግዞት አስልከዋል። በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ባንዳ የነበሩትን እነ አበበ ገመዳን፣ እነ መኮንን ደነቀን፣ እና ብላታ አድማሱን እንዳስጠጉ ሁሉ በኤርትራ የእንግሊዝ ወገን የነበሩትን እነ ተስፋ ዮሐንስን ሾመዋል። አርበኞቹን አርቀዋል ። ዛሬ እንኳን በጅቡቲ ወደብ ጉዳይ ከፈረንሳይ ጋር የሚያደርጉት የስውር ስምምነት የዚሁ የቀኝ ገዢዎች ጋር መስማማት ውጤት ነው። እንደ እ.አ መስከረም 7/51 ጥር 16/51 ግንቦት 22/53 ሚያዚያ 25/57 አፄ ኃይለ ላሴና አክሊሉ ሀብተወልድ ከአሜሪካን ጋር የተፈረሟቸው የጦር ስምምነቶች ኢትዮጵያን ላይ አሜሪካን ኢንፔሪያሊዝም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በማድረግ የጦር መሳሪያ አድርገዋታል። ማዕድን ዋና እና ማንኛውንም ሃብቷን ያለምንም ገደብ የአሜሪካን የጦር ስንቅ እና መጠቀሚያ አድርገውታል። እነዚህ ስምምነቶች የአፄ ኃይለስላሴ የ57 ዓመት የቅኝ ገዢዎች እና የኢምፔሪያሊስቶች መሳሪያነት በይፋ እንዲታወቅ አድርገዋል። ያለ አግባብ መበልፀግ ጀማሪ እና አስጀማሪው አፄ ራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው ህጉን አስተዳደሩን የራሳቸው የራሳቸውን ስም ማጋነኛ የራሳቸውን ንብረት ማዳበሪያ አድርገው ኖሩ። ከፍ ያለ የአስተዳደር በደል በህዝቡ ላይ አደረሱ። የኢትዮጵያውያን ላብ ያፈራውን ንብረት በውጭ ሀገር አስቀመጡ። ለጣሊያን ለፈረንሳይ ለእንግሊዝ ይበልጡን ደግሞ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶች አገሪቷን ሸጡ። ማስረጃ ሞልቷል። ምስክሩ ተርፋል። የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ይፋረዳቸዋል።

 
ድሉ የሰፊው ህዝብ ነው
Scroll to Top