የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 4፣ ጳጉሜ 5፣ 1966
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ሁለት አበይት የሚላቸውን የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ጉዳዮች አንስቶ ያብራራል። በመጀመሪያ፣ የየካቲቱ ትግል 7ኛ ወሩን እንደያዘ በማሳሰብ፤ ወታደራዊ ደርግ ደግሞ በሦስት ወራት እድሜው ውስጥ ምንም አይነት ግልጽ የሆነ አጠቃላይ የለውጥ ፖለቲካዊ ፕሮግራም ወይም መመሪያ ለሕዝብ ማቅረብ እንዳልቻለ ይገልጻል።አገሪቱን እንደግል ንብረታቸው ይዘው የነበሩትን አጼ ኃይለ ሥላሴን እያወገዘ መግለጫ ቢያወጣም ቅሉ፤ በንጉሥ ነገሥቱ ምትክ ባስቸኳይ ከሕዝብ የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት እና አያይዞም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንዲቋቋም ይጠይቃል። በሁለተኛም ደረጃ፣ በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ፤ የሕዝባዊ ለውጡን ሂደት እና የአገሪቱን ብሔራዊ ነጻነት አደጋ ላይ ሊጥል ከሚችለው የምዕራብውያን በተለይ የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም በንቃት መጠበቅና መቋቋም የግዴታ እንደሆነ ያሳስባል። ለዚህም ጊዜያዊ ስጋት፣ በሌሎች አገሮች እንደታየው የቅርብ ታሪክ ውስጥ፤ በሲ.አይ.ኤ. በምስጢር የተከናወኑት የመንግሥት ግልበጣዎችና ግድያዎች ለጉዳዩ አሳሳቢነት በቂ ማስራጃዎች እንደሆኑ ያረጋግጣል።
የሰፊው ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ ሰባተኛ ወሩን᎓ ሦስተኛው የወታደር ዙር ሦስተኛ ወሩን ጀምሮአል። ታድያ ደርጉ አሁንም ትክክለኛ አቋሙን አልገለጸም፤ ጠቅላላ ፕሮግራሙን ግልጽ አድርጎ ለሕዝብ አላስታወቀም። እነእንዳልካቸው ለማጭበርበርያ አውጥተውት የነበረውን መምሪያ ግን ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ የጣለው መሆኑን በማያዳግም መልክ ገልጦታል። ይህ ከሆነ᎓ ታዲያ ደርጉ ለምንድን ነው አቋሙን ለሕዝብ የማይገልጠው? ጠቅላላ ፕሮግራም ሳይወጣ እንዴት ይህን ያህል ጊዜ መቆየት ይቻላል? ከሕዝብ ወገኖች ይህ እንዲሆን ብዙ ጊዜ ተጠይቆ እስካሁን ድረስ ምንም የለም። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ መቼ ድረስ ነው ይህን ሁኔታ በአርምሞ የሚመለከተው? የሕዝቡ ትዕግስት ወሰን ያለው መሆኑን ሌላው ቢቀር ከአሁኑ ታሪካችን ለመረዳት አይቻልም ይሆን?
ሰሞኑን በአጤ ኃይለሥላሴ ላይ የተጀመረው የማጋለጥ ዘመቻ ሊደገፍ የሚገባው ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ይህ አይደለም። ኃይለሥላሴና ቤተሰቦቹ አሁንም እንደቀለዱ ናቸው፤ የጭቆናውና የብዝበዛው መሳሪያና ግብረአበሩ የነበሩት ከስልጣን ለጊዜው ገለል ቢሉም ጨርሰው አልተነሱም፤ ከፀረሕዝብ ድርጊታቸው ጨርሰው አልተወገዱም። በዚህ ረገድ የተደረገው መደረግ ከሚገባው ጋር ሲተያይ ኢምንት ነው። አጤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ባሪያ፤ አገሪቷን እንደግል ንብረታቸው አድርገው በአምባገነንነት ሲጨፍሩበት የኖሩ ስለሆነ አንዳንድ ወንጀሎችን እየነጣጠሉ በቁጥ ቁጥ ለሕዝብ እንደብርቅ በማቅረብ ጊዜ መፍጀቱ ትክክለኛው የአሰራር ዘዴ ነው ወይ?
ከአሥር ዓመታት በፊት ጀምረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር አሁን እንደ አዲስ ነገር የሚቀርበውን የአጤ ኃይለሥላሴን የግፍና የብዝበዛ አስተዳደር ሲያወግዙ፡ ሲኮንኑና ሲያጋልጡ ቆይተዋል። ባለፈው ግንቦት ወር የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብና በበሽታ ቸነፈር ሲያልቅ ምንም አይነት በቂ እርዳታ ባለመደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ በገጠር ተሰማርተው ወገናቸውን እንዲረዱ ጠይቀው ነበር። ደርጉ ባለፈው ሳምንት ስለ ገጠር ዘመቻ ያወጣው ሃሳብ በመሰረቱ ከተማሪዎች ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው። የተማሪዎችን ሃሳብ ተቀብሎ ከሥራ ላይ ለመዋል ማቀዱ ጥሩና የሚደገፍ ሲሆን፤ ከዚያ በፊት ግን በቅድሚያ መፈጸም ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። በዚህ ወረቀት ውስጥ በሌላ ስፍራ ዘርዘር ብለው የተመለከቱ ቢሆንም ምንም አይነት ነገር ከመደረጉ በፊት የሚከተሉት ዓበይት ጉዳዮች በቅድሚያ መፈፀም አለባቸው።
- አጤ ኃይለሥላሴ ውሎ ሳያድር ከስልጣን ወርደው ከነቤተሰባቸውና ከቀንዳም ግብረ አበሮቻቸው ጋር አንዲታሰሩ᎓ ለፍርድ እንዲቀርቡና አሁኑኑ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ /የሕዝብ መንግሥት/ እንዲታወጅ፣
- ከሰፊው ሕዝብ ልዩ ልዩ ክፍሎች በምርጫ የተውጣጡ አባሎች ያሉበት ጊዜያዊ መንግሥት አሁኑኑ ተቋቁሞ᎓ እስከ ሦስት ወር ድረስ የተሟላ ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት እንዲታወጅ የሚደረግ መሆኑ በማያጠራጥር አኳኋን ለሕዝብ እንዲገለጥ፣
- መሰረታዊ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶችና ነፃነቶች፤ በተለይ የንግግር የጋዜጣ የማህበር ነጻነት፤ ካሁን ጀምሮ ያላንዳች ገደብ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያስፈልጋል።
ደርጉ ይህን ትክክለኛ መንገድ በመከተል ፋንታ፤ የሕዝቡን ጥያቄዎች አልመልስም፤ በሰፊው ሕዝብ ፍላጐት አልመራም፣ ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ፣ ወዘተ. በማለት የነአጤን መንገድ ለመከተል የሞከረ እንደሆነ በታሪክና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ተጠያቂነቱ የማይቀር ነው። ከሰፊው ሕዝብ ፊት ማንም ሊቆም አይችልም። እንኳን የወላለቀ ኢምፔሪያሊስት መሳሪያ ቀርቶ ኒውክሌር ቦምብም የሕዝብን እንቅስቃሴ ሊደመስሰው አይችልም። ታሪክ ይመሰክራልና።
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የኢትዮጵያ
ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ሁለት ዓበይትና ቀንዳም ጠላቶች አሉት። እነዚህም በመንኮታኮት ላይ ያለው ባላባታዊ የአገዛዝ ሥርአትና ኢምፔሪያሊዝም በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ናቸው እነዚህ ሁለቱ ጭራቆች በመተባበርና በመደጋገፍ ለብዙ ዓመታት ሰፊውን የኢትዮጵያ ሠርቶአደርሕዝብ ሲዘርፉት᎓ ሲበዘብዙት᎓ ሲጨቁኑት ኖረዋል፣ ደሙን መጥጠው፣ ስጋውን አንክተው አጥንቱን ብቻ አስቀርተውታል። ባለፈው የካቲት የፈነዳውን የትግል እሳተጎሞራ ወደ ትክክለኛ ግቡ ለማምራት፣ እነዚህን በዝባዞችና ጨቋኞች ለመደመሰስና ለማውደም፣ለሰፊው ሕዝብ᎓ ሰብአዊ መብቶቹንና ነጻነቶቹን መልሶ በማጎናፀፍ ኑሮው እንዲሻሻልና እንዲያድግ ለማድረግ የሚያስችል ᎓ ሙሉ ዋስት የሚሰጥ በሕዝብ የተመረጠ ᎓ ለሕዝብ የሚያገለግል᎓ የሕዝብ መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል።
ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዋናና አንደኛ ጠላት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው። በበሰበሰውና በአድሃሪው ፊውዳል ሥርአተመንግሥት ላይ ብዙ ድሎችን በመቀዳጀት ወደፊት በመገስገስ ላይ ያለውን የሰፊውን ሕዝብ የመሰረታዊ ለውጥ እንቅስቃሴ አድብቶ እንዳያጨናግፈውና ወደኋላ እንዳይመልሰው ዛሬ በኃይል የሚያስፈራው ተንኮለኛውና አረመኔው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው።
ለመሆኑ ኢምፔሪያሊዝም የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? የኢምፔሪያሊዝም ᎓ በተለይ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ᎓ አይነተኛ ጠባይ ምንድነው? ኢምፔሪያሊዝም ᎓ ጭቆና ብዝበዛ ዘረፋ ምዝበራ ወዘተ. ማለት ነው። በሃይል᎓ በመደለል᎓ በተንኮል᎓ በመሸንገል᎓ በማባበል᎓ የሕዝብ መንግሥቶችን በቀጥታና /በኃይል/ በዘወርዋራ መንገድ ማስገልበጥና ማስወገድ᎓ በእነርሱ ስፍራ ጥገኛ ቡችላና አሻንጉሊት መንግሥት በማቋቋም ሌላውን አገርና ሕዝብ መበዝበዝና መጨቆን ነው። ኢምፔሪያሊዝም የአድሃሪ ባላባቶችና መሳፍንት ደጋፊ ᎓ የስግብግብ ከበርቴዎች መሳሪያ ᎓ የሰፊው ሠርቶአደር ሕዝብ ደም መጣጭ ነው።
ኢምፔሪያሊስት አገሮች /አሜሪካ፣ ምዕራብ አውሮፓ፣ ጃፓን፣ እስራኤልና መሰሎቻቸው/ በቀጥታና በዘወርዋራ መንገድ የአፍሪካን፣ የእስያንና የላቲን አሜሪካን አገሮችና ሕዝቦች ለብዙ ዘመናት ሲበዘብዙና ሲጨቁኑ ቆይተዋል፤ አሁንም በልዩ ልዩ ዓይነት ዘዴና ተንኮል፣ በወዳጅነት እርዳታ፡ ንግድ፡ ባህል፡ ወዘተ. በማለት አብዛኛውን የሦስተኛውን ዓለም ህዝቦች በመበዝበዝና በመጨቆን ላይ ናቸው። በቀኝ እጃቸው አንድ ሲሰጡ፣ በግራው እጃቸው አምስት ይነጥቃሉ፣ ከባድ አወናባጆች፣ ተመሳሳይ የሌላቸው አጭበርባሪዎች ናቸው።
የኢምፔሪያሊስት አገሮች ቀንደኛ መሪና በማደግ ላይ ያሉት አገሮችና ሕዝቦች አብይ ጠላት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፤ በመልማት ላይ ያሉትን አገሮች ሃብት የሚመዘብረውና የሚዘርፈው በልዩ ልዩ አይነት መንገድና ዘዴ ነው። እርዳታ /የኢኮኖሚ ወታደራዊ የባህል/ አስባችኋለሁ በማለት አማካሪዎቹን /ሰላዮቹን/ በብዛት በመላክ የመንግሥቱን ዋና ዋና ክፍሎች /መከላከያ᎓ ጸጥታ᎓ ውጭ ጉዳይ᎓ ማስታወቂያ᎓ ትምህርት᎓ ኢኮኖሚ᎓ ልማት ወዘተ. / በቁጥጥሩ ስር ያደርጋል። መሪዎቹንና ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን በገንዘብና በጥቅም ያስራቸዋል። አንዳንድ አገር ወዳድ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች እንዳሉና እንቅፋት የሚሆኑት ከሆነ በተንኰልና በሴራ ያስወግዳቸዋል። መንግሥቱ የሕዝብ ከሆነ መሪዎቹም የሕዝብ ወገኖችና ተራማጆች ከሆኑ በዚያም በዚህ ብሎ ሲአይኤ የሚባለው የስለላ ድርጅቱ ያስገለብጣቸዋል፤ቡችሎቹን አዘጋጅቶ ስልጣን ኮልቻ ላይ ያወጣቸዋል።
በእንደዚህ አይነት ተንኮል ኢምፔሪያሊዝም በተለይ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በዓለም ሕዝቦች ላይ በተለይ በሶስተኛ ዓለም ሕዝቦች ላይ ይህ ነው የማይባል ወንጀል ፈጽሟል፤አሁንም በመፈጸም ላይ ነው። በየጊዜው ቁጥራቸው በርከት ያለ የሕዝብ መንግሥታት አስገልብቷል፤ብዙ የሕዝብ ወገን መሪዎች ከስልጣን አስወግዷል፣ አስገድሏል። ፓትሪስ ሉሙምባን ከነጓደኞቹ በቡችላው በሞቡቱ አማካይነት አሰቃይቶ ያስገደለው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው፤ የጋናውን ክዋሜ ንክሩማህን ከስልጣን ያስወገደም እርሱ ነው፣ እነቼ ጌቫራን የመሰሉ የሕዝብ ወገን ታጋዮች አሳድኖ ያስገደለው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው፤ በላቲን አሜሪካ ለብዝበዛና ለዘረፋ ሲል ከኩባ በስተቀር /ለዚያውም በስንት መስዋዕትነት/ ቡችሎቹንና አሻንጉሊቶቹን ስልጣን ላይ አስቀምጧል። በቪየትናም፣ በካምቦዲያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪቃ፣ በዓለም በሞላ የሚበጠብጥና ሰላም የሚነሳ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው። በቀጥታና በዘወርዋራ መንገድ ጦርነት የሚጭረው፣ ሕዝቦችን የሚያጋጨውና የሚያፋጀው፣ የሕዝብ መንግሥታትን የሚያስገለብጠው ፀረሕዝብ መንግሥታትን ደግፎ የሚይዘው አገርወዳዶችንና ተራማጅ መሪዎችን የሚያስገድለውና የሚያሳድደው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ነው። ሃጢአቱ ወንጀሉ ይህ ነው አይባልም፤ በጣም ብዙ ነው።
ከአድሃሪው የኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር በመተባበርና በመመሳጠር የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ለብዙ ዓመታት ሲዘርፍና ሲጨቁን መቆየቱ የታወቀ ነው። ወንጀሉን ሕጋዊ ለማስመሰል ከፊውዶቡርዧው መንግሥት ጋር ቁጥራቸው በርከት ያለ ስምምነቶች ተፈራርሟል። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ዋና መሳሪያ የሆነው ፀረሕዝቡ ሲአይኤ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የበሰበሰውን የኃይለሥላሴ መንግሥት ለመጠበቅና በስልጣን ላይ ለማቆየት ስሩን የሰደደ መሆኑ አያጠራጥርም። በሁሉም ውስጥ ገብቷል፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች በሲቪል በወታደር በፖሊስ ይበልጡኑ በልዩ ልዩ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ስር በመስደድ ብዙ ቡችሎች አሰማርቷል። ይህን የሚጠራጠር ያለ አይመስለንም።
ከየካቲት ወዲህ ባላባታዊው ሥርአት በመንኮታኮት ላይ በመሆኑ አሁን የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዋናና አንደኛ ጠላት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መሆኑን ከፍ ብለን አመልክተናል። ኃይለሥላሴ የሚወክለው ሥርዓት በሰፊው ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ በኃይል በመጠቃቱ ለመውደቅ በመንገዳገድ ላይ ሲሆን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ግን በመሳሪያው በሲአይኤ ውስጥ ውስጡን በማጠናከር ላይ መሆኑ ከዚህ በፊት ተጠቁሟል። ምርጥ የሆኑትን ተናካሽ ቡችሎቹን በብዛት ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል። አሁንም በመግባትና በልዩ ልዩ አቅጣጫ በመሰማራት ላይ ናቸው። እንደ ልማዳቸው የመንግሥት ስልጣን ለመያዝና የሕዝብን ወገን ለማድከም ሰፊና ብርቱ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው።
ከታወቁት ቀንደኛ የሲአይኤ ቡችሎች መካከል ‘የፖለቲካ ስደተኛ ነኝ’ በማለት የሚያወናብደውን አቶ ስዩም ስብሃትን መጥቀስ ይቻላል። ስለዚህ አደገኛ ቡችላ ካነሳን ዘንድ ‘የፖለቲካው ስደተኛ’ በሚል ርእስ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚባለው ጋዜጣ ከአንድ ሁለት ወይም ሦስት ሳምንታት በፊት ለታተመው የማይታመን የሲኒማ ታሪክ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር። ‘እውነት ትገለጥ የጋዜጣ ነጻነት አለ’ ከተባለ እውነቱ ይውጣ በማለት የቀረበው ጽሑፍ ሳይታተም የቀረው ለምን ይሆን? /ለአዲስ ዘመንና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ጽሑፉ ተልዕኮ ነበር።/
በነበአሉ ግርማና በነአጥናፍሰገድ የተቀበረው ይህ ጽሑፍ በአጭሩ የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ያነሳል። ስዩም ስብሀት ሞስኮ በነበረበት ጊዜ የመጀመሪያዋ የሶሻሊስት ሀገር በሆነችው በሶቪየት ህብረት ላይ ሶሻሊዝምን የሚያወግዝ ካፒታሊዝምን የሚያሞግስ ጽሑፍ ፓስት በሚባለው በአሜሪካን መጽሄት ውስጥ ያሳተመ መሆኑንና ይህንንም ያደረገው በሲአይኤ አነሳሽነት እና አበረታችነት እንደሆነ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ‘ሶሻሊስት ነኝ፣ የአሁኑን መንግሥት እቃወማለሁ’ ወዘተ. በማለት ብዙ አገር ወዳዶችንና ተራማጅ ምሁራንን ወጥመድ ውስጥ እያስገባ ማሳሰሩንና ከዚያም አልፎ ማስገደሉን፤ /ፊታውራሪ ሃይሉ ክብረት፣ ናደው ፈጠነ፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደሃዋርያት፣ ለምሳሌ ያህል/ ለሁለተኛ ጊዜ አውሮፓ በሄደበት ወቅት/ የፖለቲካ ስደተኛ ነኝ በማለት/ በአገር ወዳድና ተራማጅ ተማሪዎች ላይ በመሰለል እርስ በእርሳቸው በማጣላትና በመከፋፈል ከፍ ያለ የከሃዲነት ሥራ ይሰራ እንደነበር፤ በመጨረሻም ካርቱም መጥቶ በሱዳን ለአሜሪካን፣ ለእስራኤልና ለኢትዮጵያ መንግሥታት ሲሰልል በሱዳን የፀጥታ ሠራተኞቸ ተደርሶበት 4 ወራት ያህል ከታሰረ በኋላ የሲአይኤ ባልደረባ አለቃው ግሪንፊልድ የሚባለው መጥቶ አስፈትቶት ወደ ጋና የወሰደው መሆኑንና ሌሎችንም ያጭበርበራቸውን ነገሮች ለሕዝብ የሚያጋልጥ ነበር። እነአጥናፍሰገድ ይልማና እነበአሉ ግርማ ምነው ጉዳዩን አፍነው ጭጭ ለማድረግ ሞከሩ?
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የስለላ ድርጅቱ ሲአይኤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ቡችሎች አሳድገዋል። በፊይውዶቡርዧው ቢሮክራሲ ውስጥ ከላይ እስከታች አሰማርቶአቸዋል። በግል ድርጅቶች፣ በንግድ በፋብሪካውና በሌላውም ክፍል ቁልፍ ቁልፍ በሆኑት ስፍራዎች ላይ ቡችሎቹን አስቀምጧል።
አሁንም አድብተው ስልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ለማለት በደርጉ አካባቢ የሚሰበሰቡ ብዙ ቡችሎች መኖራቸው የተደረሰበት ጉዳይ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ከዚህ በፊት በሕዝብ ወገኖች፣ በሲአይኤ ጠላቶች በመደጋገም የተጋለጠው ሳሙኤል አለማየሁ /አአድ/ ይገኝባቸዋል። ይህ አወናባጅ ‘ማናቸውንም የማንቀሳቅሰው እኔ ነኝ፤ ሁሉም የኔ ጭፍሮች ናቸው’ እያለ በየቦታው እንደሚደነፋ ከመታወቁም በላይ አሉሚናይ የሚባለውንም የዩኒቨርስቲ የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ከዚህ በፊት ለብዙ ዓመታት ለዚህ ለርካሽ ተግባሩ ሲጠቀምበት ቆይቷል። ባለፈው ሳምንትም በዚሁ ማህበር በኩል ሲያወናብድ ነበር። የነዚህ የሲአይኤ ቡችሎችና የሀቀኛው ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ አላማ ፍጹም ተቃራኒ እንደመሆናቸው መጠን በጣም የሚገርመን ጉዳዩ በቅድሚያ የሚመለከታቸው /ደርጉ/ እስካሁን ድረስ እነዚህን ከሀዲዎች አለማራቁ ነው። አርምሞው ለምን ይሆን? ማናቸውንም እውነተኛ የሕዝብ ወገን ራሱን ደጋግሞ መጠየቅ የሚገባው ጉዳይ ነው። ጉዳዩ በዚህ ብቻ የሚሸኝ ሳይሆን የሕዝብ ወገን የሆነ ሁሉ ባለው አቅም ከአሁኑ ጀምሮ ሊቋቋማው የሚገባ ብርቱና አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንደኛ ጠላት መሆኑ ከዚህ በላይ የተጠቀሰ ነው። ሲአይኤ ምርጥ ቡችሎቹን ወደዚህ በመላክ ዛሬ ላይ ታች፣ግራ ቀኝ በማለት የሚራወጥበት ዋና አላማ በየካቲት ወር የፈነዳውን የሰፊውን ሕዝብ ትግል እንቅስቃሴ እውነተኛውን ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ለመደምሰስና ድሉን ለማክሸፍ መሆኑ በደንብ መታወቅ አለበት። ከላይ እንደተመለከተው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ዋና ጥረት በከበርቴዎቹ አማካይነት የኢትዮጵያን ሃብት ለመዝረፍና ሠራተኛውን ለመበዝበዝ ነው። ብዝበዛውንና ጭቆናውን ለመቀጠልና ለማስፋፋት በማለት ነው የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚጥረው። ዋናው ጥረቱ የኢትዮጵያን ተበዝባዥ ሕዝብ ባለበት ለማስቀረት፣ ከባርነት ከብዝበዛ ከበሽታ ከድንቁርና ሲኦል ውስጥ ሲማቅቅ እንዲኖር ለማድረግ ነው። ዋናው ፍላጎቱ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የጅአዙር ቅኝ ግዛት መሆኗን እንዳታቋርጥ ነው። የጅአዙር ቅኝ ግዛትነቷን ካቋረጠች፤ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የሕዝቡን ብዝበዛ የሚቃወም፣ አገሪቱ በባእዳን ከበርቴዎች እንዳትበዘብዝ የሚቆጣጠር፣ በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተና ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅም ብሔራዊ ኢኮኖሚና ከኢምፒሪያሊስት ተዕእኖ ነፃ የሆነ ፖለቲካ የሚከተል ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ከተመሠረተ ኢምፔሪያሊስቶች አገሪቱን መበዝበዝ አይችሉም፤ የእነርሱ ቅርንጫፍ ኩባንያዎች የፈለጉትን ጥርቃሞ ዕቃ በፈለጉት ዋጋ መሸጥ አይችሉም። በጠቅላላው ኢኮኖሚያቸው ይነካል፣ ብዝበዛቸው ይቀንሳል።
ይህ እንዳይሆን ኢምፔሪያሊስቶች አጥብቀው እየታገሉ ናቸው። ከላይ እንደጠቀስነው ብዙ ሰላዮች አሰማርተዋል። ከዓለም ባንክና ከተቀሩት የአሜሪካን ባንኮች ተፈቅደው የነበሩትን ብድሮች ለመቀነስ እያስፈራሩ ናቸው። ከሁሉ ይበልጥ ግን በአገራችን ውስጥ የሚገኙ የኢምፔሪያሊዝም አቀባይ ነጋዴዎችና ውጭ ያሉት ደንበኞቻቸው በቅድሚያ ካልተከፈለን በሚል ፈሊጥ የሕዝቡን ትግል ለማክሸፍ ሲሉ ብቻ ከውጪ ዕቃ ማስገባትን አቁመዋል። ወደ ውጪም የሚላከው ዕቃ ተመሳሳይ ችግር ይደርሶበታል። ይህ በነጋና በነኩባና በሌሎችም አገሮች ኢኮኖሚን በማድከም ተራማጅ መንግሥታትን ለመጣል፣ የሕዝቡን ትግል ለማክሻፍ ኢምፔሪያሊስቶች የተጠቀሙበት ዘዴ ነው።
የአንዳንድ የውጭ አገር ከበርቴዎች ገንዘብ ማሸሽ ጉዳይ በጋዜጦች ተደጋግሞ ተገልጧል። ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማዳከሚያ፣ የሕዝቡን ትግል ማክሸፊያ አንድ ዘዴ ነው። ኢምፔሪያሊዝም እንደዚህ አይነቱን ሴራ የሚያላላው አዲሱ መንግሥት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር የገባና የእርሱ መሳሪያ ለመሆን የተስማማ እንደሆነ ብቻ ነው።
ስለዚህ ኢትዮጵያ በእርግጥ ነፃ የምትወጣው ብዝበዛን ማቆምና የሰፊውን ሕዝብ ደህንነት መጠበቅ የሚቻለው፣ ትግላችን ድልን መጎናፀፍ የሚችለው፤ በኢምፔሪያሊዝም ላይም የማያወላውል እርምጃ ስንወስድ ብቻ ነው። በወዲያ በወዲህ ብለው፣ አስፈራርተው፣ በሳቦታዥም በምንም ለጊዜው ሊያዳክሙን ቢችሉም ቆርጠን ከታገልን እናሸንፋቸውለን። በዚህ ከባድና መራራ ትግል የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በተለይ ግንባር ቀደም ተራማጆች አይናቸውን ከፍተው በንቃት መጠባበቅ ይኖርባቸዋል። ደርጉ ከማናቸውም ይበልጥ ሲአይኤን በንቃት መጠባበቅ አለበት። ይህን የምንለው ለጊዜው ስልጣን በዚያ አካባቢ ስለሆነ ሲአይኤ ቡችሎቹን ከስልጣን ኮርቻ ላይ ለማስቀመጥ ደርጉን በልዩ ልዩ ዘዴና ተንኮል ሊሸነግለው ሊደልለው፣ ወደ ውስጡ ሰርጎ በመግባት ከግቡ ሊደርስ ይችላል። በሌሎች አገሮች፤ በሳይፕረስ፣ በግሪክ፣ በሱዳን፣ በቬትናም፣ በታይላንድ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአጭሩ በዓለም ያደረገውንና የሚያደርገውን ማጥናትና መረዳት ያስፈልጋል። ሲአይኤ በቀላሉ የሚገመት ባለጋራ አይደለም። ለዚህ ነው የደርጉ ሰዎች በኃይል መጠንቀቅና አይናቸውን ከፍተው መጠባበቅ የሚኖርባቸው። ሲአይኤን ድል ለመምታት የሚቻልበት ዋናውና ትክክለኛው መንገድ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ማዋሃድ፣ አብሮ መሰለፍ፣ በሕዝቡ ላይ እምነት ማሳደር፣ ሕዝቡ በትግሉ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። ደርጉ ይህን ካላደረገ ታሪክ ከትዝብት ላይ ይጥለዋል። እውነተኛውና የመጨረሻው መድህን የሰፊው ሕዝብ ኃይል መሆኑን ቶሎ ተረድቶ ይህን ጠንቀኛ ጠላት በአንድነት መቋቋም ነው። የሚያዋጣው ይህ ብቻ ነው።
የእንቅስቃሴው ባለቤት፣ አንቀሳቃሹ፣ ፈጣሪው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ደርጉ ይኸንን እውነትና ሃቅ መቀበልና … ፍላጎት ማሟላት አለበት። ይህን ዘንግቶ ወይም ችላ ብሎ፣ የእንቅስቃሴው መሪ እኔ ነኝ፤ አልፋውና ኦሜጋው፣ የጀመርኩትና የምጨርሰውም እኔው ነኝ፣ እናንተ ምን ታውቃላችሁ፣ ዝምብላችሁ መመልከትና መታዘዝ ነው ወዘተ. የሚል ከሆነ ከከባድ ውድቀት ላይ እንደሚደርስ ትንሽ እንኳን አያጠራጥርም። ከሕዝቡ ተነጥሎ ከሄደ ትንሽ ቀናት ውሎ ይደር እንጅ ተንኮታክቶ መውደቁ አይቀርም። በመጨረሻ ግን ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው። ይህ የታሪክ እውነትነት ነው። ደርጉ ወደፊት ለመራመድ የሚችለውና ጠላቶቹን ድል ለመንሳት፣ ሲአይኤን ለማሸነፍ የሚችለው ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ሙሉ በሙሉ እንዲካፈል ሲሆን ብቻ ነው። እስከተቻለንና ሁኔታው እስከፈቀደልን ድረስ ይህንን ነገር ደጋግመን ከማንሳት ከቶ ፍንክች አንልም። ጊዜው የሚያዋዛ፣ ፋታ የሚሰጥ፤ በቀላሉ ችላ የሚባል አይደለም። ሰፊው ሕዝብ በንቃት ይህንን መርዘኛ ጠላቱን መቋቋምና ድል ማድረግ አለበት። የወደፊት እድሉና የኑሮ መሻሻል ተስፋ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነውና።
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና ሲአይኤ ይውደሙ፣
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ወይስ
የወታደር መንግሥት?
ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ አሁንም እልባት አላገኘም። ጨቋኝ መሳፍንት፣ መኳንንትና ከፍተኛ ባለስልጣኖች በከፊል ቢታሰሩና የአንድ ሁለት አፈንጋጮች ንብረትና ሃብት ቢወረስም ጨቋኙና በዝባዡ ስርዓት ገና አልተነካም፤ አቋሙም ሰዎቹም እንዳሉ ናቸው። ለሰፊው ሕዝብ ወስፋት ማስታገሻ፣ እምባ ማድረቂያ የሚሆን ነገር ከተስፋነት አልፎ በእውን ገና አልተገኘም። አሁንም ዋና የጊዜው ጥያቄ የትግሉ እንቅስቃሴ ወዴት ነው የሚያመራው? ምን አይነት ስርዓተ መንግሥት ነው ከሁኔታው የሚወጣው? የሚለው ነው።
የፈላጭ ቆራጭ ባላባታዊ አገዛዝ ብኩንነት ዛሬ ለሁሉም ግልጥ ብሎ በመታየት ላይ ነው። ታሪካዊ ተፈላጊነቱ ካከተመ ቆይቷል። በስራቸው ሳይሆን ባጥንታቸው ‘ጥራት’ ብቻ ተቀምጠው የሚበሉ ትኋኖችን የሚፈልግ የለም። የመሳፍንትና የባላባት አገዛዝ የኢትዮጵያን ሰፊ ሠርቶአደር ሕዝብ ከመጠን በላይ ያንገሸገሸው ስለሆነ እንኳን በውኑ በህልሙም ሊያየው አይፈልግም። የአሁኑን አምባገነን ባለአባታዊ ስርዓት በምን እንተካው ለሚለው ጥያቄ ሁለት አማራጭ ጎዳናዎች ከፊታችን ይታያሉ።
- ሰፊውን ሕዝብ የሚወክል ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ወይም
- በጥቂት ‘ምርጥ’ ወታደሮች የሚመራ ወታደራዊ አገዛዝ
አሁን እንደሚታየው ከሆነ ምርጫው ከሁለቱ ተቃራኒ መንግታዊ ስርዓቶች አንዱ የሚሆን ይመስላል። የፊተኛውንም ሆነ የኋለኛውን አማራጭ በቀላሉ ልንመለከተው የሚገባ አይደለም። ለእያንዳንዱ አማራጭ የራሱ ጽኑ ደጋፊዎች አሉት። ዛሬ ለውጥን አጥብቀው የሚቃወሙ የሥርዓቱ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች መሳፍንት መኳንንትና ጥቂት ቡችሎቻቸው ናቸው። የቀረው ብዙው ለውጥን ይደግፋል። ግን አላማቸው ለየቅሉና ተቃራኒ ነው። የበሰበሰው ባላባታዊ ስርዓት የበላይ ጠባቂና ጥቅም ተካፋይ የሆነው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እንኳን ቢሆን ለውጡን ሙሉ በሙሉ አይቃወመውም። እንዲያውም እርሱን ወደሚጠቅመው አቅጣጫ እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ስለዚህ ለውጡ ሕዝባዊም ፀረሕዝብ የሆኑም ደጋፊዎች አሉት። እነዚህ ደጋፊዎች ትግሉ በሚወስደው አቅጣጫ ላይ ይለያሉ። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶቹን ሊያጎናጽፈው የሚችለውን ዲሞክራሲያዊ ሪፑበሊክን /የሕዝብ መንግሥት/ይመርጣል፣ኢምፔሪያሊዝም በተለይ አሜሪካና የዲሞክራሲ ጠላቶች ግን የወታደር አገዛዝን ይፈቅዳሉ። የጥቅም ተቃራኒዎች ናቸውና።
ባሁኑ ጊዜ የወታደር አገዛዝ በኢኮኖሚ ወደኋላ በቀሩ በብዙ አገሮች /ተበዝባዥ አገሮች/ውስጥ ሰፍኖ ይታያል። ምንም እንኳን የገዥው መደብ መሳሪያ ቢሆን ወታደር ከሰፊው ሕዝብ የወጣ በመሆኑ በታጠቀው መሳሪያ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ጨቋኞችንና በዝባዦችን ሊደመስስ ይችላል። መሳሪያ ካለና ለበጎ ተግባር ሊያውሉት የሚፈልጉ ከተገኙ ጥቂት የሕዝብ ጠላቶችን ከስልጣን ኮርቻ ማውረድ ከባድ አይደለም። ዋና ከባዱ ነገር የሰፊው ሕዝብ ኑሮ ከፍ እንዲልና ሰብአዊና ብሄራዊ መብቹና ነፃነቶቹ እንዲከበሩና ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉ ነው። በመሠረቱ አንዳንድ ቀንደኛ የሕዝብ ጠላቶች ከስልጣን ስለታገዱ ብቻ አገሪቱ አትበለጽግም፣ የሰፊው ሕዝብ ኑሮ አይሻሻልም። አገሪቱ የምትበለጽገው የሰፊው ሕዝብ ኑሮ የሚሻሻለው ህዝቡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመመስረት ዋና ዋናዎቹን የሃብት ምንጮች በእጁ አድርጎ ለጋራ ጥቅምና ብልጽግና በህብረት ታጥቆ ሲሰራ ብቻ ነው።
በጥቂት ወታደሮች መሪነት የሚቋቋም ወታደራዊ አገዛዝ ሰፊውን ሕዝብ ከልቡ ታጥቆ እንዲሠራና ኑሮውን ለማሻሻል እንዲችል አያደርገውም። በመጀመሪያ ላይ የወታደር መንግሥት የዲሞክራሲን ስነስርኣት አይከተልም። ደርግ ከኋላው ኖረም አልኖረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሰው ጎልቶ ይወጣል፤ ደርጉን ወደዚያ አስፈንጥሮ ከፍተኛውን ስልጣን ይጨብጣል፤ ለአገሩ አሳቢ መሆኑንና አገሩ ከወደቀችበት የችግር አዘቅት ሊያወጣት የመጣ ቤዛ ወይም መሲህ መሆኑን ይናገራል፤ የሰፊውን ሕዝብ አስቸኳይና መሰረታዊ ጥያቄዎች አንዳቸውንም ሳይፈጽምና ሳያሟላ፣ ታገሡኝ፣ ፋታ ስጡኝ፣ አትቸኩሉ፣ በቅድሚያ ሕግና ሥርዓት ይከበር፣ ወዘተ. ማለት ይጀምራል። አጣዳፊ የሆኑትን የመሬት፣ የሥራ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የአስተዳደር፣ የሰብአዊና ብሔራዊ መብቶች ጥያቄዎች ባለመመለሱና ባለማሟላቱ የሚቀርቡበትን ትችቶች ሂሶች ነቀፌታዎች፣ ሠፊው ሕዝብ የሚያሰማውን ማጉረምረምና መበሳጨት በኃይል ለመቋቋም ይነሳል። ለችግሩ ማቃለያና መፍቻ ሊውል የሚገባውን ገንዘብና ሃብት ሕዝቡን ሰጥ-ለጥ አድርጎ ለማስበዝበዝ ያባክነዋል። ቀስበቀስ መንግሥቱ የበለጠ ፋሺስታዊና ፍፁም ፀረሕዝብ እየሆነ ይሄዳል። የሕዝቡም ተቃውሞና ትግል ወደ ውስጥ እየገባ እየተጠናከረ ይቀጥላል። ወታደራዊ መንግሥት የሕዝቡን ትግል ለመግታት ከፍ ያለ የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ ከኢምፔሪያሊዝም ለመጠየቅ ይገደዳል። ውሎ አድሮ ፍጹም የኢምፔሪያሊዝም ቡችላ ይሆናል ማለት ነው። በደቡብ አሜሪካ በነጓቴማላ፣ ሳንቶ ዶሚኒጎ፣ በአፍሪካ በኮንጎ /ዛየር/፣ ሱዳን፣ በእስያ ቬትናም፣ ካምቦዲያ ወዘተ. እንደታየው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አሻንጉሊቶቹን ባለው አቅም ሁሉ ለመደገፍና የአገሩን ሃብት ለመዝረፍ ትልቅ ተጋድሎ ያደርጋል። የሰፊው ሕዝብ ትግል በመጨረሻው፣ በተለይ በቪየትናም ውስጥ በማያጠራጥር ሁኔታ እንደታየው ድሉን ይቀዳጃል፣ ወታደራዊው አሻንጉሊት መንግሥትና ግብረ አበሩና ጠባቂው ኢምፔሪያሊዝም በሕዝባዊ ትግል ድምጥማጣቸው ይጠፋል፣ ይወድማሉ።
የታሪክን ትክክለኛ ጎዳና መከተል ከብዙ ስህተት ያድናል፤ የጥቂት ጨቋኞችን ደም አናፍስስ ስንል በደም ባህር ውስጥ እንዳንሰጥም ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ‘ኢትዮጵያ የተለየች ናት፣ታሪካችን ከሌላው አይገጥምም፣ እኛም አገራችንም ልዩ ነን’ ወዘተ. በማለት ከትልቅ ስህተትና አደጋ ላይ እንዳንወድቅ። ትላንት ቬየትናም፣ ዛሬ ካምቦድያ ውስጥ የደረሰውና በመድረስ ላይ ያለው ነገ እዚህም ሊደርስ ይችላል። የዋህነት አናብዛ፣ ማር እንኳን ሲበዛ ይመራል እንደሚባለው የዋህነቱም በጣም ሲበዛ ጉዳቱ በዚያው መጠን ይሆናል።
ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ሌላው አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ /የሕዝብ መንግሥት/ ሙሉ ሰብአዊና ብሄራዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚያጎናጽፍ፣ የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ የሚያሻሽል መንግሥት ማቋቋም ነው። ለአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚያዋጠው ሰፊው ሕዝብ የጠየቃቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊያሟላ የሚችለው ሕዝቡ የሚሳተፍበትና የሚቆጣጠረው የሕዝብ መንግሥት ነው። ለብዙ ዘመናት ሲጨቆንና ሲበዘበዝ የኖረው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በየካቲት ወር የትግሉን እንቅስቃሴ በሰፊው የጀመረው ከዚህ ሁሉ እፎይ ብሎ ለመተንፈስ ነው እንጅ ከአንድ አይነት ጭቆና ወደ ሌላው፣ ከፈላጭ ቆራጭ ነጋሲ ወደ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ አገዛዝ ለመዞር አይደለም። ይህ ደህና ተደርጎ መታወቅ አለበት። የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት በመዘንጋት፣ ወይም ደህና አድርገን ባለመረዳት ከባሰ ውድቀትና ልንወጣ ከማንችልበት አዘቅት ልንቀረቀር እንችላለን። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ደህና አድርገው ያስቡበት እንላለን።
ዲሞክራሲ በሕዝቡ ዘንድ በተሻለ መንገድ ሊሰፍን የሚችለውና የሕዝቡ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው፣ የሕዝቡ ትጋትና የሥራ መንፈስ የሚቀሰቀሰው፣ ሕዝቡ ራሱ የሚያዝበት፣ የኔ ነው የሚለው በልዩ ልዩ መንገድ ሊቆጣጠረው የሚችል ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሲመሰረት ብቻ ነው። ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ ያለበት ከላይ እስከታች ድረስ ያሉትን አስተዳዳሪዎች በሙሉ የሚመርጠው ሕዝቡ ራሱ መሆን አለበት። እንደዚህ አይነቱን አስተዳደር ለመመስረት ሕዝቡ ካሁን ጀምሮ በያለበት በፖለቲካ ረገድ እንዲደራጅ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ማህበሮችን ለማቋቋም መከልከል የለበትም። በመብቶቹ እንዲጠቀም ማበረታታት እንጅ መከልከል ትክክል አይደለም። ሰፊውን ሕዝብ ሊወክል የሚችል እውነተኛና ባለሙሉ ስልጣን ፓርላማ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለምንም ገደብ ሊመርጥና ሊመረጥ የሚችልበት ፓርላማ እንዲቋቋም ያስፈልጋል።
የዲሞክራሲ ሪፐብሊክ መንግሥት ሕዝብን የሚፈራ አይደለም፣ የሕዝብን መብቶች ያከብራል በሕዝብ ሀሳብና ፍላጎት ይመራል። ዋና ዋና የሆኑት ያገሪቱን ሃብቶች፣ የዘራፊውን መንግሥት ገዥ መደብ አባሎች፣ በጠቅላላው መሳፍንትና መኳንንት ሳይሠሩ ይጠቀሙበት የነበረውን ሃብትና ንብረት ሁሉ ወርሶ በጠቅላላ መልክ ለሕዝቡ አገልግሎት እንዲውል ያደርጋል። ሕዝቡ ላይ የሥራ መንፈስ፣ የኃላፊነት መንፈስ ይፈጥራል። ለሕዝቡ የመኖር ዋስትና ይሰጣል።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ገና ጉሽ ጠላ ነው። የጠላትም የወዳጅም ልብ እንደቆመ ነው። አሁን ካለው ሁኔታ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፓርላማ ወደሚመረጥ መንግሥት ለማምራት አንዳንድ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ። ከወታደሩና በየመስኩ ከተሰማራው ሲቪል /ከገበሬው ከኢንዱስትሪና ከመንግሥት ሰራተኛ፣ ከተማሪው ካስተማሪው ወዘተ./ የተውጣጣ የወታደሩንና የሲቪሉን ጥረትና ፍላጎት የሚያጣምር አጠቃላይ የተራማጅ ደርግ መመስረት ያስፈልጋል። ይህ አጠቃላይ ተራማጅ ደርግ ንጉሡን ባለፈው ጥፋታቸውና ውንብድናቸው እንዲጠየቁ አድርጎ ለጊዜው ስልጣንን በጊዜያዊ መልክ መያዝ ይኖርበታል። ይህ ጊዜያዊ መንግሥት ግልጽ የሆነ የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም የሚጠብቅ ፕሮግራም አዘጋጅቶ በርሱ እየተመራ፣ አንዳንድ አስቸኳይና አስፈላጊ ስራዎችን እያከናወነ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቋቋም መፍቀድና ማበረታታት ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የሚያጠቃልል፣ ለሰፊው ሕዝብ የሰርቶመኖር ዋስትና የሚሰጥ ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት አርቅቆ ሕዝቡ ማቅረብ አሁን ያለውን ፓርላማ ዘግቶ ሕዝቡ ያለ ምንም ገደብ፣ ያለምንም የሃብት ተጽዕኖ መምረጥና መመረጥ በሚለው ፍልስፍና በመመራት እውነተኛ ወኪሎቹን አዲስ ለሚከፈተው ፓርላማ እንዲልክ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሕዝቡ ፓርቲዎችን የማቋቋም መብቱን ካገኘ፣ የራሱን ጥቅም የሚጠብቅለት የፖለቲካ ድርጅት እያቋቋመ ትልቅ የፖለቲካ ትግል በማድረግ ለራሱ የሚጠቅመውን ዲሞክራሲያዊ የሪፐብሊክ መንግሥት ሊመሰረት ይችላል። ስልጣንን ከጥቂት ሰዎች ይልቅ ወደ ብዙሃኑ እጅ ማግባት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው።
እንግዲህ ሁለቱን አማራጭ ሀሳቦች አየን። የሚሻለውን፣ ለሰፊው ሕዝብ የሚበጀውን አቅጣጫ አመለከትን። ታዲያ ወደዚሁ አቅጣጫ ለማምራት የሚቻለው እንዴት ነው?
የወታደሮቹ ደርግ ጉዳዩን በጥሞና እንዲመረምረውና እንዲያስብበት ያስፈልጋል። በዚህ ጥያቄ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድ ይኖርበታል። አሁን እንደምናየው ከካቢኔው ጋር የሥራ ግንኙነት በማድረግ ብቻ ብዙ መሄድ አይቻልም። በደርጉ አካባቢ አንዳንድ ግለሰቦች እየጎሉ መታየት የጀመሩ ይመስላል። የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መፈለግና መቻላቸውን እንጠራጠራለን። ከኢምፔሪያሊስት አገሮች በተለይም ከአሜሪካ መሣሪያ ተጠይቆ በመግባት ላይ እንደሆነ የታወቀ ነው። የፀረህዝቡ የሲአይኤ ቡችሎች በአገሪቱ ውስጥ ፀረሕዝብ መረባቸውን ይበልጥ እየዘረጉና አሳፋሪ ተግባራቸውን በማስፋፋት ላይ መሆናቸው ተደርሶበታል። ሁኔታው በዚህ አቅጣጫ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ መውጣቱ ቀርቶ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን የጅአዙር ቅኝግዛት ቀንበር እንደተሸከመ ይቀራል። ወደ ወታደር አገዛዝ /ፀረዲሞክራሲ/ እንዳንሄድ የሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም። ከዚህ በላይ ከፍ ብሎ የተመለከተው እንዳይደርስ ያሰጋል።
ይህን አደጋ ለማስወገድ፣ እንደዚህ ያለውን አስጊ ሁኔታ ለመቋቋም ሰፊው ሕዝብ በንቃት ሁኔታውን መከታተልና መስራት አለበት፣ መደራጀት አለበት። የሰፊውን ሕዝብ ትግል የሚያስተባብር ደርግ በቶሎ መቋቋም ይኖርበታል። ይህ ደርግ የወታደሮቹን ደርግ በሚወስዳቸው ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ያበረታታዋል፣ የሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚጠበቅበትን የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት የሚያሟላ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በተቻለ ፍጥነት እንዲመሰረት ባለ አቅሙ ይጥራል።